የአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተዳደር ከጀመረ ስምንተኛ ወሩን ሊያስቆጥር ነው፤ ክስተቱም የሰዎችን እንቅስቃሴ ገድቧል:: አገልግሎት ፈላጊዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በፈለጉት ጊዜ እንዳይገናኙ አድርጓል:: የእንቅስቃሴ ገደቡ ደግሞ የክልሉን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አዳክሞታል::
ለአብነትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ አድርጓል፤ የጤና ተቋማት ወድመዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግጭቱ በውይይት እንዲፈታ በተደጋጋሚ ተጠይቋል፤ አሁንም እየተጠየቀም ነው:: ዳሩ ግን እስካሁን ጠብ ያለ ሥራ ባለመሠራቱ የሰላም በሮች አልተከፈቱም፤ ግጭቱም እንደቀጠለ ነው::
ከሰሞኑ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ ግጭት ተከስቶ ንጹሃን ተገድለዋል፤ በርካቶችም ተፈናቅለዋል:: በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች ቀጥለው ሰብዓዊ ጉዳት እየደረሰ ነው::
የግጭቱን መቀጠል ተከትሎ ታዲያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) ጨምሮ በርካታ ተቋማት እና ሀገራት ስጋታቸውን ገልጸዋል፤ የሰላም በሮች ተከፍተው ችግሩ በውይይት እልባት እንዲያገኝ እየተጠየቀ ይገኛል::
ለአብነትም በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት እንደሚያሳስባት በተደጋጋሚ ስታስታውቅ የቆየችው አሜሪካ፣ ከሰሞኑ በክልሉ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈፀሙ ጥቃቶች እንዳሳሰባት ገልጻለች:: በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ “የትኛውም የግጭት ተዋናይ ሁከትን በመጠቀም ሰዎችን ከቤታቸው ማፈናቀል የለበትም” ሲሉ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የግጭቶች መስፋፋት የሰዎች እገታ ድርጊትንም እያስፋፋ ይገኛል፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሰሞኑ እንዳስታወቀው ዓለም አቀፍ የመብት ድንጋጌዎች እና ሕጎች አለመከበራቸዉ በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀሎች እንዲበራከቱ አድርጓል::
የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ እንደተናገሩት በሃገሪቱ ያሉ ግጭቶች እንዲሁም የሥራ አጥ ቁጥር መበራከት የዜጎች እገታ ከቀን ወደ ቀን እንዲበራከት አድርጓል፤ ወጣቶች እንደ ሥራ እድል እንዲጠቀሙበት እያደረገ መሆኑንንም ገልጸዋል:: ችግሩ በዚህ ከቀጠለ ሃገርን ለከፍተኛ ችግር እንደሚዳርግ እና የሙስና ተጋላጭነትም እንደሚሰፋ ጠቁመዋል::
ይህን ድርጊት በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) “በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዜጎች ላይ በታጠቁ ቡድኖች እየተፈጸመ ያለው እገታ እና ግድያ መንግሥት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ እየተባባሰ ነው” ብሏል:: ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ እና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያስከተለ መሆኑን አክሏል።
ከችግሩ መውጫ መንገድ ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑን ያነሳው መግለጫው፣ ዘላቂ ሠላም እንዲመጣ በተለያዩ ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ሠላማዊ መንገድን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርቧል። መንግሥትም የሚጠበቅበትን ሁሉ ሊፈጽም እንደሚገባ አሳስቧል።
በተመሳሳይ ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስራት ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል።
ኢሰመኮ ባለፉት አምስት ዓመታት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እንዲሁም በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የአቤቱታ መቀበያ መድረኮችን አካሂዶ ባሰባሰባቸው ማስረጃዎች አስገድዶ መሰወርን ጨምሮ “ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ” ብሏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች የሚጣሱባቸውን ዐውዶች በመመርመር፣ የጥሰት መንስኤዎችን እልባት ለመስጠት፣ ጥሰቶችን ለማስቆም፣ በጥሰቶች ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እና ለተጎጂዎች ተገቢ የሆነውን የካሳ ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ይህንኑ በሥራ ላይ ለማዋል የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።
በሌላ መረጃ የሰሜኑ ጦርነት የብዙ ሺዎችን ሕይወት ከነጠቀ፣ መጠነ ሰፊ ቁሳዊ ውድመት ካስከተለ በኋላ በውይይት እልባት ማግኘቱ ይታወቃል፤ እንደ ሀገር ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው ጦርነቱ ለአብነትም አማራ ክልል ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ውድመት እንደደረሰበት በአማራ ክልል በጦርቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል::
ከዚህ ችግር ሳያገግም ክልሉ በግጭት አዙሪት ውስጥ መግባቱ ታዲያ ችግሩን የከፋ አድርጎታል:: የአማራ ክልል መንግሥት ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል:: ይሁን እንጂ እስካሁን የተገኘ ውጤት የለም።
በሌላ በኩል ዋና መንቀሳቀሻውን በኦሮሚያ ክልል ካደረገው ኦነግ ሸኔ ጋር መንግሥት ድርድር መጀመሩ ይታወሳል፤ ድርድሩ ወደ ውጤት ባይቀየርም የሁለቱም አካላት ተወካዮች በታንዛኒያ በተደጋጋሚ ተገናኝተው የሰላም ውይይት አካሂደዋል:: ይሁን እንጂ ውይይቱ ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም:: ለዚህ ደግሞ አንዱ ሌላውን አካል ተጠያቂ አድርገዋል::
በሰላም ውይይቱ መሳተፏን ያስታወቀችው አሜሪካ፣ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ እንደማይሆን አመላክታለች፤ ውይይት እና ድርድር አዋጩ መፍትሔ ነው ብላለች:: የሚጠበቅባትን ድጋፍ እንደምታደርግም ነው የገለጸችው።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮ
በርካታ የዓለም ሀገራት በጦርነት ታሪክ የተቃኙ ናቸው፤ ጦርነቱን የፈቱት ደግሞ ሁሉንም አሸናፊ ባደረገ መልኩ በይቅርታ ነው፤ ለአብነትም ደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው::
በደቡብ አፍሪካ በነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ ጥቁሮች በነጮቹ አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ከዚያም በነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ መሪነት የጥቁሮቹ የነፃነት ትግል ፍሬ አፍርቶ የሥልጣን መንበሩን ተረክበዋል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የደረሰባቸውን ግፍ አስታውሰው የበቀል ዱላን አላነሱም። ይልቁንም የተፈጸመባቸውን ግፍ በይቅርታ አልፈውት ሀገራቸውን ከበለጸጉ ሀገራት መካከል እንድትሆን አድርገዋታል።
በተመሳሳይ በአንድ ጀንበር አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሩዋንዳዊያን ያለቁበት ብሔር የወለደው ጭፍጨፋ በይቅርታ እንዲሽር ተደርጎ በአሁኑ ወቅት በዕድገት ጎዳና ላይ ይገኛሉ።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም