“የእኔም ድምጽ በሬዲዮ ቢሰማ እል ነበር”

0
193

ጀማሪው ጋዜጠኛ በሬዲዮ ሞገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጹ ሊሰማ ነው:: ስለሆነም ለአሳዳጊ እናቱ ደውሎ እንድታደምጠው ይነግራታል:: በሬዲዮ ሞገድ መረጃውን አቅርቦ ጨረሰ፤ በድምጹ እና በአቀረበው መረጃ ይዘት ከባልደረቦቹ ዘንድ ትልቅ ውዳሴ አገኘ:: ወዲያው ለእናቱ ደውሎ  “እማ እንዴት ነበር? አላት፤ “ኸረገኝ! ያንተ ድምጽ ነው? ምን ሆኖ ነው?” የሚል ያልጠበቀውን ምላሽ ሰጡት፤ በዚህ አላበቃም፤ ቁም ነገሩስ እንዴት ነው? ሲላቸው “ምንም ፍሬ የለው፤ ያልከውም አልገባኝ” ብለውት አረፉ፤ የዚህ አስቂኝ ገጠመኝ ባለቤት አንጋፋው ጋዜጠኛ ሀሰን መሐመድ ነው:: ከገጠመኙም ተደራሽን ለይቶ በዛው ልክ መረጃን ማሰናዳት እንደሚገባ ተምሬበታለሁ ይላል::

ጋዜጠኛ ሀሰን መሐመድ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር ኮምቦልቻ ከተማ ቀበሌ 02 ተወለደ:: እናት እና አባቱ ገና በለጋነቱ ነበር በሞት የተለዩት:: ሆኖም አጎቱ አቶ ይመር መሐመድ እና የአጎቱ ሚስት ወይዘሮ ዘነበች አሊ እንደልጃቸው አድርገው ነው ያሳደጉት:: የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው እዛው ኮምቦልቻ ከተማ ነው::

ጋዜጠኛ የመሆን ህልሙ ከልጅነቱ የጀመረ ነው:: የንባብ ልዩ ፍቅር ያለው ሀሰን የአዲስ ዘመን ጋዜጣን በ25 ሳንቲም እየገዛ ለጓደኞቹ ያነብላቸው ነበር:: በተለይ አርብ አርብ ማታ ለተሰበሰበው ማቲ አዲስ አድማስ የተሰኘችውን አምድ በሬዲዮ ጋዜጠኛ ደንብ ያነብላቸዋል:: አስደናቂ ታሪኮች፣ ተረቶች፣ ግጥሞች፣ አጭር ልብ ወለዶች እና ሌሎች የስነ ጽሑፍ ሥራዎችን በልዩ አተራረክ ለታዳሚው ያቀርባል::

አጎቱ የሸማ ሥራ ይሰራሉ፤ እየሠሩ ደግሞ ሬዲዮ ያዳምጣሉ:: ትንሹ ሀሰንም አብሯቸው እያዳመጠ “የእኔም ድምጽ እንዲህ በሬዲዮ ቢሰማ” በሚል ይመኝ ነበር:: የፖሊስ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ግዛው ዳኜ አርአያው ነው:: ሀሰን አንድ ጊዜ ለፖሊስ ሬዲዮ አስተያየት ጻፈ:: የሚያደንቀው ጋዜጠኛ ግዛው ዳኜ አስተያየቱን አነበበ:: የሰፈሩ ሰው “ይሄ ነው የጻፈው” ሲባባሉ ሲሰማ ለጋዜጠኝነት የበለጠ ፍቅሩ እንደጨመረ ሀሰን ይናገራል::

ወጣቱ ሀሰን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ደሴ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገባ:: የአማርኛ ትምህርት ክፍልንም  ተቀላቀለ:: ይህም ማለት ከስነ ጽሑፍ ጋር የበለጠ እንዲቀራረብ አደረገው:: በዚህ መሰረት ለጋዜጣ እና ለግል መጽሔቶች ጽሑፎችን መላክ ጀመረ::

ጽሑፉንም እየጻፈ የመምህርነት ሙያ ስልጠናውን በ1985 ዓ.ም አጠናቀቀ:: ከከሚሴ ከተማ 15 ኪሎ ሜትሮችን ከምትርቀው እሬንሳ የገጠር ቀበሌ በመምህርነት ተመደበ:: በዚህ ጊዜ ከገጠሩ ማህበረሰብ ጋር መተዋወቅ እና የኑሮ ዘይቤያቸውን ማጥናት ጀመረ:: በዚህ ውስጥ ለጽሑፉ የሚሆን ርዕሰ ጉዳይ አገኘ፡- የገጠር የፍቅር ታሪኮች:: “ሁሉም ሰው ታሪክ አለው” የሚለው ሀሰን ፍቅር በገጠር ምን ይመስላል? የሚለውን በማራኪ ታሪኮች እያዋዛ ለመጽሔቶች መላክ ጀመረ:: መረጃውን ደግሞ የሚያገኘው ማታ ማታ ሰብስቦ ፊደል ካስተማራቸው በኋላ ነበር:: ስለሆነም መሬት የወረደ እና ማራኪ ታሪክ ያገኛል፤ በወቅቱ የተለመደውም የውጭ የፍቅር ታሪኮችን ማቅረብ ነበር:: ይህ አዲስ ነገር ያስደሰተው የግል መጽሔት ባለቤት የፎቶግራፍ ማንሻ ካሜራ ለሀሰን ላከለት:: ከዚያ በኋላ ታሪኮቹ በፎቶግራፍ ተዋዝተው መውጣት ጀመሩ::

ሀሰን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አምደኛም ነበር፤ የሚያስተምርበትን አካባቢ እና  ባህላቸውን ያስተዋውቅ ነበር:: በዚህም የሙሉ ጊዜ ጋዜጠኛ ሳይሆን በጸሐፊነቱ ይታወቅ ነበር:: ይህ ደግሞ ወደሚናፍቀው እና የልጅነት ህልሙ ወደ ሆነው ጋዜጠኝነት ለመግባት በር ከፈተለት:: በኢህአዴግ ዘመን ክልሎች ሲዋቀሩ የማስታወቂያ ቢሮ እንዲኖራቸው ተደርጓል:: በወቅቱ የጋዜጠኝነት ትምህርትም ሆነ ተስጥኦ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት አዳጋች ነበር:: ስለዚህ በቋንቋ እና ስነጽሑፍ ትምህርት የተማሩ፣ ዝንባሌው ያላቸው ባለሙያዎች በፈቃደኝነት ይሰበሰባሉ:: በዚህ አጋጣሚ ሀሰንም በቀድሞው አስተማሪው ጠቋሚነት የአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮን ተቀላቀለ::

ባሕር ዳር መጥቶ ሪፖርት ካደረገ በኋላ የሥራ ቦታው ጎንደር እንደሆነ ተነገረው:: ጎንደርን መጽሐፍት ላይ ካነበበው ውጪ አያውቃትም፤ መጀመሪያውኑም እሱ ያሰበው “ደሴ ወይ ባሕር ዳር ተመድቤ እሠራለሁ” ብሎ ነበር:: ጉዳዩን ከቤተሰቦቹ ጋር ተማከረበት:: አጎቱ ነጋዴ ስለነበሩ ጎንደርን ያውቁታል፤ ስለሆነም “ጥሩ ሀገር ነው ሂድ” አሉት:: የአጎቱ ሚስት ግን “ኸረ የሱዳን ጠረፍ ነው፤ ሩቅ ነው፤ ይቅርብህ” አሉት፤ እሱ ግን የአጎቱን ምክር ሰማ፤ ወደ ጎንደር አቀና::

ጎንደር ከተማ እንደደረሰ አስተዳዳሪው ቢሮ ሰጡት:: ፈተና የሆነው ነገር መረጃ እንዴት ማግኘት እንደሚችል ሀሳብ ብልጭ አለማለቱ ነው:: በኋላ “ለምን ከአስተዳዳሪው ቢሮ የሚመጣውን ሰው ሀሳብ ሰብስቤ የዘገባ መነሻ አላገኝም?” የሚል ማኛ ሀሳብ መጣለት:: ከቢሮው ውጪ የሀሳብ መስጫ ሳጥን አስቀመጠ:: ባለጉዳዩ ሀሳቡን፣ ቅሬታውን እና ጎደለብኝ የሚለውን መጻፍ ጀመረ:: ሀሰንም ቤቱ ወስዶ የህዝቡን አስተያየት ያነባል:: አስተዳዳሪውን የተመለከቱ ደብዳቤዎችን ለአስተዳዳሪው ይሰጣል፣ ለዘገባ የሚሆነውን ደግሞ ዜና ይሠራበታል:: በዚህ መንገድ በሠራቸው ሥራዎች በሦስተኛው ወር ግምገማ ጥሩ ግብረ መልስ አግኝቷል::

እንደዚህ ከመመስገኑ በፊት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራው ዜና አሁንም ድረስ ለራሱም ያስቀዋል:: ጉዳዩ እንዲህ ነው:: ሀሰን ከስነ ጽሑፍ ውጪ በጋዜጠኝነት መስኩ ያሉትን የዜና አጻጻፍ እና የፕሮግራም ስክሪፕት አጻጻፍ አያውቅም፤ ስልጠናም አልወሰደም:: እሱ የሚያውቀው ተራኪ ታሪኮችን፣ ትዝብቶችን እና ሌሎች የስነ ጽሑፍ ሥራዎችን ነው፤ እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ዜና እንዲሠራ ተላከ፤ የተላከውም በበለሳ ወረዳ የተከሰተውን የአተት በሽታ ሽፋን አንዲሰጥ ነው:: ሀሰን ብዙ ሰዎችን አናገረ፣ ባለሙያዎችን ጠየቀ፣ ኃላፊዎችን አፋጠጠ:: በመጨረሻም ዜናውን በጽሑፍ አሰናዳ:: በስልክም ባሕር ዳር ለሚቀበለው ሌላ ጋዜጠኛ ማድረስ ጀመረ:: ሀሰን ያነባል፣ያነባል፣ ያነባል፤ አያልቅም፤ ዜና ተቀባዩ  ጋዜጠኛ “አያልቅም እንዴ?” ይላል፤ ሀሰን ያነባል:: ለካስ ሀሰን የጻፈው ዜና 30 ገጽ ነበር፤ በመጣጥፉ ለምዶ:: አሁንም ይህ 30 ገጽ ዜና ለታሪክ በሀሰን ቤት ተቀምጧል::

ክፍተቱን ለማስተካከል ጎንደር በሚገኘው የኢትዮጽያ ዜና አገልግሎት ቅርንጫፍ በመሄድ ዜና እንዴት እንደሚሠራ ጠየቀ፤ እንዴት እንደሚሠራ አሳዩት፤ የቅርንጫፍ ሠራተኞች በሬዲዮ መገናኛ የሚያደርጉትን ውይይትም እየተመላለሰ ለአንድ ወር ተከታተለ:: በዚህ ምክንያት የሀሰን የጋዜጠኝነት ህይወት ተቀየረ:: ከዚያ ማን ይቻለው::

ቀጥሎ ወደ ባሕር ዳር መጣ፤ ወቅቱ ደግሞ የቴክኖሎጂ ሽግግር የነበረበት ነው:: በኮምፒውተር የሬዲዮ ዜና እና ፕሮግራም ማዘጋጀት የሚቻልበት ጊዜ ነው:: ከ1989 እስከ 1990 ዓ.ም በአማራ ራዲዮ የልማት ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ ሠራ:: በወቅቱ የልማት ፕሮግራሞች ደረቅ እና ከሰውኛ የራቁ አልነበሩም:: ሰው እየተዝናና የሚማርባቸው በታሪክ የተዋዙ ነበሩ:: ሀሰን ስለ አርሶ አደሩ ማወቅ፣ መመራመር እና መዘገብ ይወዳል:: “ይህ ለምንድን ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ “ገጠር በነበርኩበት ጊዜ የመጣልኝ ሀሳብ ነው፤ አርሶ አደሩ ሀሳብ አለው፤ የሚኖርበት የራሱ ፍልስፍና አለው፤ ችግሮቹን የሚፈታበት እውቀት አለው፤ በቅርበት ስላየኋቸው አውቃቸዋለሁ:: “ብዙ ሰው አርሶ አደሮች በባዶ እግራቸው ስለሚሄዱ፣ የተቀደደ ስለሚለብሱ፣ ለእነሱ ያለው እይታ የተዛባ ነው፤ ነገር ግን ዘረኞች ያልሆኑ፣ ሲወዱ ከልብ፣ ማስመሰል የማያውቁ በመሆናቸው የበለጠ እንድወዳቸው እና ስለነሱ ይበልጥ እንድዘግብ አድርጎኛል” ይላል::

የሰዎችን ተሞክሮ ስለመዘገብ ሲናገር ደግሞ “ጀርመኖች በጦርነት ሀገራቸው ከወደመች በኋላ ጋዜጠኞቿ ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን ተሞክሮ በመዘገብ እና ለሌላው መማሪያ በማድረግ ነበር ዳግም ሀገራቸውን የገነቡት” ይላል::

በአማራ ሬዲዮ ለሁለት ዓመታት ከሠራ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማ ትምህርት እድል አገኘ፤ በዛም የጋዜጠኝነት ሙያውን እንዲያዳብር ረድቶታል፤ ከትምህርቱ ባሻገር  ግን ከኢትዮጵያ ሬዲዮ የመጡ የክፍል አጋሮቹ ጋር የነበረው የልምድ ልውውጥ እና የእርስ በርስ መማማር የበለጠ እንደጠቀመው ይናገራል:: በነገራችን ላይ በ1999 ዓ.ም እዛው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ተመርቋል::

ሀሰን ዲፕሎማውን ተመርቆ ሲመጣ በወቅቱ ወደ አንድ ሰዓት ባደረገው አማራ ቴሌቪዢን ውስጥ ተመደበ:: በአማራ ቴሌቪዢን የአርሶ አደሩን እና የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች ይዘግብ ነበር:: ለአብነት ደቡብ ጎንደር ውስጥ የአንድ ዐይነ ስውር ግለሰብን ጠንካራ ተሞክሮ ሠርቷል:: ግለሰቡ አናጺ ነው፣ ዛፍ ይቆርጣል፣ ባትሪ ይጠግናል፤ ሁሉንም ነገር ሢሠራ ቀርጾ “ዐይነ ስውሩ አናጺ” የሚል ዝግጅት አሰናዳ:: ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ በተመልካች ተወዷል፤ ግለሰቡም የሚረዳው ሰው አግኝቷል:: መሰል ሰዎች በተለያየ ችግር ውስጥ ሆነው ሳይበገሩ ለውጤት የሚበቁ ሰዎችን እና የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሠርቷል::

በኋላም አማራ ቴሌቪዢን ወደ ሰባት ሰዓት አየር ሰዓት ሲያድግ ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ:: በዚያም የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ እና ሂደቱን በአግባቡ በመምራት አገልግሏል:: የከተሞች መድርክ፣ የአርሶ አደሮች ወግ እና ሌሎች በተመልካች የሚወደዱ እና በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩ ፕሮግራሞች በእሱ የአመራር ጊዜ የተቀረጹ ናቸው:: ቀጥሎም በአማራ ብዙኃን መገናኛ የሚዲያ ልማት እና እቅድ ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነ፤ ድርጅቱ ወደ ኮርፖሬሽን ሲያድግ እና የመዋቅር ለውጥ ሲያመጣ የስልጠናና ምርምር ዳይሬክተር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል:: ክፍሉ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ ችግሮችን ይጠቁማል፤ የመፍትሔ ሀሳብ ያቀርባል፣ ስልጠና እና ማማከርም ይሰጣል:: የተለያዩ የክልሎች መገናኛ ብዙኃንን ከመሳሪያ ተከላ ጀምሮ አማክሯል፤ ለግለሰቦች እና ድርጅቶች ሥልጠና ይሰጣል::

ሀሰን እና ባለቤቱ የተገናኙበት መንገድ ፈገግ የሚያሰኝም አስገራሚም ነው፤ ይህን ነግረናችሁ ጽሑፋችንን እናብቃ:: አንድ የተቀደሰ ዕለት ሀሰን ከጓደኛው ቤት ጥሪ ተጠርቶ ይሄዳል፤ ከግብዣው ቤት ከጠሪው ውጪ የሚያውቀው ሰው አልነበረም:: ጥግ ላይ አንዲት ወይዘሪት ብቻዋን ተቀምጣለች:: ባለው ክፍት ቦታ ላይ አጠገቧ ሀሰን ተቀመጠ:: ወይዘሪቷ እሷም በዛ ቤት ውስጥ ከባለቤቱ በስተቀር የምታውቀው ሰው አልነበረም እና አጠገቧ ካለው ሀሰን ጋር ወሬ ጀመሩ:: በዚህ ተዋውቀው ተለያዩ፤ ከቀናት በኋላ በአጋጣሚ ሀሰን ወይዘሪቷን መንገድ ላይ አገኛት፤ ትንሽ ካወሩ በኋላ ሀሰን “አንቺን ልጅማ  አገባሻለሁ” አላት፤ ልጅቷ ተበሳጭታ ሄደች፤ ከዚያ ቢፈልጋት የት ትገኝ:: የተወሰኑ ጊዜያት አለፉ፤ ሀሰን ሁለተኛ ዲግሪውን (ማስተርሱን) ሊማር ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጠገብ ካለው መንደር ቤት ይከራያል፤ እዛ ግቢ ውስጥ “አገባሻለሁ” የተባለችው ወይዘሪት ለምን ተከራይታ አልተገኘችም መሰላችሁ:: “አስመርቃ አገባችኝ” ይላል ሀሰን ታሪኩን ሲናገር፤ ከዚችው ባለቤቱ ሁለት ልጆችን አፍርተው በመኖርም ላይ ይገኛሉ::

አንጋፋው ጋዜጠኛ ሀሰን መሀመድ ለወጣት ጋዜጠኞች ያልተነበበ መጽሐፍ ነው ማለት ይቻላል::እኛም በዚህ አምድ ከሀሰን ተሞክሮዎች ቀንጭበን ያጋራናችሁ ብዙ ቁምነገር ትገበያላችሁ በሚል እሳቤ ነው::

ሰላም ሁኑልን!

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here