በጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ሂጋሺ ዶሪ በተሰኘ የግብይት ማዕከል በጣሪያና ግድግዳ ላይ በተሠራ የብረት መቃን መቶ ሀያ ሺህ መነጽሮችን የያዘው መደብር “የመነጽር ሙዚየም” የሚል ስያሜ ማግኘቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
ከ50 ዓመታት በፊት የመነጽር መደብሩ መስራች ዩታካ ታኪ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ወይም ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ነበር የጀመሩት::
ከጊዜ በኋላ ግን ለዐይን ህመም የሚታዘዙ እና የፀሐይ ብርሃን ማስተካከያ መነጽሮች ሽያጭ ላይ ብቻ ትኩረታቸውን አድረገው ጣሪያ ግድግዳውን ገዢዎችን በሚስብ መልኩ ማደራጀታቸው ተጠቁሟል::
በተለያዩ ቀለማት እና ቅርጽ የተዘጋጁ መነጽሮችን የያዘው መደብሩ በአንድ ወቅት በተደረገ የቁጥጥር ቆጠራ መቶ ሀያ ሺህ መያዙ ተረጋግጧል:: በርከት ያለ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ በርካታ የመነጽር ስብስብን የያዘው ሱቅ በግብይት ማዕከሉ የጐብኚዎች መዳረሻ ሊሆን መቻሉም ተጠቅሷል::
በመነጽር መሸጫ መደብሩ በጣሪያ እና ግድግዳ የብረት መቃኖች ላይ ከተሰቀሉት ባሻገር በመካዘንም ታሽገው የተቀመጡትን አውጥተው በብዛት ለሚገዙ ያቀርቡ እንደነበር ነው በድረ ገጹ የተገለፀው::
የመነጽር መደብሩ ከመቶ ሺህ በላይ መነጽሮች ለሸያጭ የቀረበበት ከመሆኑ ባሻገር ዋጋውም ቅናሽ የሚታይበት ነበር፤ በዚህም እስከ ሁለት ዶላር ወይም በ300 ዬን ዋጋ የተቆረጠላቸው ይበዙ እንደነበር ነው የተጠቆመው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም