እ.አ.አ በ1840 በአውሮፓ የተከሰተው የምግብ ዋጋ ንረት፣ የምጣኔ ሀብት ውድቀት ረሃብን አስከትሎ ነበር። ረሃቡም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል። ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ሥራአጥ እንዲፈጠር እና የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲከሰት ምክንያትም ነበር።
ችግር ብልሃትን ያመጣል እንዲሉ ታዲያ አውሮፓዊያን በገጠማቸው ችግር ምክንያት እርዳታን መሠረት ያደረገ እና ድጋፍ የሚሰጥ ሕብረት ሥራ ማሕበር በማቋቋም በአንድ ተሰባሰበ። በአንድ ተሰባስበው የፈጠሩት የሕብረት ሥራ ማሕበርም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና በድህነት አረንቋ ውስጥ ላሉ ሰዎች ምግብ እና ምግብ ነክ ፍጆታዎችን በማቅረብ ከገቡበት ችግር እንዲወጡ አድርጓል።
በተመሳሳይ በአፍሪካ ዘመናዊ የሕብረት ሥራ ማሕበር እንቅስቃሴ የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል። ከዚህ በፊትም ባሕላዊ ሕብረቶች እንደነበሩ የተለያዩ ምንጮች ያሳያሉ።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1844 የመጀመሪያው የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበር በእንግሊዝ አገር ሮችዲል በምትባል ከተማ እንደተቋቋመ አይ ሲ ኤ ዶት ኩፕ (ica.coop) የተሰኘው ድረ ገጽ ያብራራል።
የሕብረት ሥራ ማሕበራትን በኢትዮጵያ ማደራጀት ከተጀመረ ከ60 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን ከአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ማሕበራት ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ቢሆንም ለሀገራዊው ምጣኔ ሀብት እና ማሕበራዊ ዕድገት ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም።
የሕብረት ሥራ ማሕበራት በተለይ እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ጉልህ ሚናን ይጫወታሉ። የሕብረት ሥራ ማሕበራት መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በሚፈለገው መጠን እና ጊዜ ባለመገኘታቸው የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ በማሰብ የተቋቋሙ ናቸው::
የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ምርታማነት ከማሻሻል ባሻገር የተሻለ የገበያ ዋጋ እንዲያገኙ ያደርጋሉ፤ በአጠቃላይ ሻጭ እና ሸማችን የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው:: በዚህም የንግድ ሥርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ድርሻቸው የጎላ ነው::
ከዚህ በተጨማሪም የግብርና እና መሰል ግብዓቶችን ያቀርባሉ፤ ዘርፉን ለማዘመንም ያስችላሉ::
አቶ ጌትነት አማረ የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ማሕበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን ኃላፊ ናቸው፤ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ለሃገር ምጣኔ ሀብታዊ እና ማሕበራዊ ዕድገት የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱ ያብራራሉ::
ኃላፊው እንዳብራሩት ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማሕበራት የግብዓት ስርጭት፣ ግብይት፣ ሜካናይዜሽን ማስፋፋት፣ ምርትን ለሸማቹ ማቅረብ፣ ገበያን ማረጋጋት እና መሰል ሥራዎችን ያከናውናል:: የቁጠባ እና ብድር ማሕበራት የቁጠባ ባሕልን በማሳደግ የብድር ስርጭትን ከፍ እንዲል በማድረግ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ የላቀ ሚና አላቸው::
አቶ ጌትነት አክለውም ሰዎች በተናጠል የማይፈፅሟቸውን ችግሮች በጋራ ሆነው ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን አሰባስበው ችግሮችን የሚፈቱበት ተቋም ነው ይላሉ:: በዚህም ሰዎችን ከመጥቀም ባለፈ ለሀገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ያነሳሉ::
ከዚህ ባሻገር የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን፣ ምርጥ ዘር፣ የእርሻ መሣሪያዎችን፣ ፀረ ተባይ መድኃኒት ወይም ኬሚካል፣ የፍጆታ ምርቶችን በሚፈለገው ቦታ፣ መጠን፣ ወቅት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል::
እንደ ኃላፊው ገለጻ በኢትዮጵያ ከ110 ሺህ በላይ መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ይገኛሉ:: በአማራ ክልል ደግሞ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን አባላትን ያቀፉ 29 ሺህ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ይገኛሉ::
በገንዘብ ቁጠባ እና ብድር የተደራጁ ሕብረት ሥራ ማሕበራት የተሻለ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንም አቶ ጌትነት አስረድተዋል። ዘርፉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ያነሱት አቶ ጌትነት በክልሉ ለ55 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ነው የተናገሩት::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የገንዘብ እጥረት ዋነኛው ማነቆ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሕብረት ሥራ ማሕበራት የኑሮ ውድነቱን እና ገበያን ለማረጋጋት አውንታዊ ሚና ይጫወታሉ፤ ለአብነትም በዚህ ዓመት ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር ተመቻችቶላቸው የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶችን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕብረት ሥራ ማሕበራት አገልግሎት አሰጣጣችውን በማዘመን ቁጠባ የማሰባሰብ እና የፋይናንስ አቅማቸውን በማሳደግ በሕብረት ሥራ ማሕበራት እና በአባሎቻቸው መካከል መተማመን እንዲዳብር አዲስ ሪፎርም (ማሻሻያ) ማስፈለጉ ተመላክቷል:: ይህን ታሳቢ በማድረግም ሥራዎች እየተሠሩ ነው::
ወቅቱ የሚጠይቀውን የአሠራር፣ የአመራር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ የአባላትን ምጣኔ ሃብታዊ እና ማሕበራዊ ጥያቄዎች ከመመለስ አኳያ አሁንም ችግሮች መኖራቸዉን አቶ ጌትነት ያነሳሉ፤ በመሆኑም “የሕብረት ሥራ ማሕበራትን ከማደራጀት ባሻገር” በሚል መሪ ሐሳብ ወደ አዲስ ለውጥ መገባቱን አስታውቀዋል:: በአደረጃጀታቸው የጠነከሩ፣ ተልዕኳቸውን በአግባቡ የሚወጡ፣ ብልሹ አሠራርን የሚያስቀሩ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ፣ በገንዘብ እና በቴክኖሎጂው የበለጸጉ፣ … እንዲሆኑ ለውጡ ማስፈለጉን ተናግረዋል።
ማሕበራት በገበያዉ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ የአባላቱ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ የግብይት፣ የብድር ስርጭት እና የቁጠባ አቅማቸውን ለማሳደግ የአደረጃጀት ተቋሙን ድጋፍ እና የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ የለውጥ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ጌትነት ማብራሪያ ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ማሕበራትን ልምድ በመውሰድ ነው ወደ ሥራ የተገባው:: ማሕበረሰቡ ስለ ሕብረት ሥራ ማሕበራት ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ በተቋቋመለት ዓላማ መሠረት መሥራት፣ ደረጃውን የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጅ አጠቃቅም፣ … በለውጡ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል:: የክህሎት፣ የእውቀት እና የአመለካክት ችግሮች እየተስተዋሉ በመሆኑ ማሻሻል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ማሕበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ጌትነት አማረ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ያላቸውን ጥቅም ለማሳየት የጎረቤት ሀገር ኬንያን ተሞክሮ አንስተዋል:: በኬንያ ከጠቅላላው 52 ሚሊዮን ሕዝቧ ውስጥ 63 በመቶው በሕብረት ሥራ ማሕበራት የተደራጀ እንደሆነ ያብራራሉ፤ ሀገሪቱ በሕብረት ሥራ ማሕበራት ላይ በሠራችው ውጤታማ ሥራ የአባላትን ተጠቃሚነት እና የቁጠባ ባሕልን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችላለች ብለዋል።
ከሀገራችን ጋር ሰፊ ልዩነት መኖሩን በማንሳት ለአብነትም በዘርፉ በኢትዮጽያ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ሲፈጠር በኬንያ ደግሞ 7 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።
ሪሰርች ጌት (researchgate) ድረ ገጽ እንዳስነበበው ደግሞ በሕንድ 50 በመቶ ሕዝብ በገንዘብ፣ ቁጠባ እና የብድር አገልግሎት የሚሰጥ ኮኦፕሬቲቭ (የሕብረት ሥራ) ባንክ ሥርዓትን እስከ ወረዳ ዘርግተዋል:: ባንኩ 67 በመቶ የሚሆነውን የሸማቾችን ፍላጎት ምርት እንደሚያቀርብም ያብራራል።
ዘርፉ በኬንያ አጠቃላይ ከሀገሪቱ ዓመታዊ ጥቅል ምርት (GDP) ከ43 እስከ 45 በመቶ ድርሻ እንዳለው ከአፍሪካን ጆርናል (africanjournal) ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል:: በሀገራችን ደግሞ ከዓመታዊ ጥቅል ምርት (GDP) 12 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን አቶ ጌትነት ተናግረዋል።
በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ውጤታማ ለማደረግም የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች መቀመጣቸውን አስታውቀዋል::
“የሕብረት ሥራ ማሕበራት የሕዝብን ሁለንተናዊ የልማት አቅም ለጋራ ዓላማ እና ፍላጎት በማደራጀት በሃገራት ማሕበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ልማት ከፍትኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ኖረዋል፣ እያበረከቱም ነው” ያሉት ደግሞ የፌደራል ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ ናቸው:: እንደ ሀገር ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙም ግንባር ቀደም ምላሽ መስጠታቸውን አክለዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም