በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የላይ አርማጭሆ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል። በዚህም እስከ 60 ሺ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በወረዳው የአይነት ውኃ ቀበሌ አርሶ አደሮች ለአሚኮ እንደተናገሩት በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ከ40 ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ ነው::
የቀበሌው ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ግዛቸው ወርቁና እንደሻው አይጠገብ ባለፉት ዓመታት በግንዛቤ ክፍተት ምክንያት አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ልማት ላይ እንደማይሳተፉ ይገልጻሉ:: አሁን ላይ ግን በተፈጠረላቸዉ ግንዛቤ በዘርፉ ውጤታም ስለመሆናቸዉ ነዉ ለአሚኮ የተናገሩት::
በማንጎ፣ በሎሚ፣ በፓፓያ፣ በጌሾ፣ በቡና እና በሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን እያመረቱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ግዛቸዉ ወርቁ በየዓመቱ ከ 40 ሺ እስከ 60 ሺ ብር እንደሚያገኙም ነግረውናል:: ሌላኛዉ አርሶ አደር እንደሻዉ አይጠገብ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከ20 ሺ ብር በላይ ማግኘታቸውን ተናግረዋል::
አርሶ አደሮቹ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አሁን ላይ ከራሳቸዉ አልፈዉ ለገበያ በማቅረባቸዉ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸዉ ገልጸዋል:: ዘርፉ የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝም ነዉ አርሶ አደሮቹ የተናገሩት::
የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቱ የተሻለ እንዲሆን የግብርና ባለሙያዎች እገዛ እንዲጠናከርም አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል። በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ የሚከሰት በሽታ ስጋት እንደፈጠረባቸው በማንሳት፣ አካል የመድኃኒትም ይሁን የባለሙያ እገዛ እንዲያደርግላቸዉ ጠይቀዋል::
አቶ ደጀን ቦጋለ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤጽ አትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ ናቸው። የወረዳው የመሬት አቀማመጥ ተዳፋታማና ለአፈር መሸርሸር የተመቸ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንንም የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን እያስፋፉ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ላይም አርሶ አደሩ በቡና ክላስተር (ኩታ ገጠም)፣ በማንጎ፣ በሎሚ፣ በፓፓያ፣ በብርቱካን፣ በጌሾ እና በመሳሰሉት ምርቶች እየተጠቀመ እንደሚገኝ ገልጸዋል::
የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በአርሶ አደሩ ዘንድ በቂ ግንዛቤ እንዳልነበር የሚያነሱት አቶ ደጀን በመሪ አርሶ አደሮች በመጀመር በአሁኑ ወቅት ሁሉም በሚባል ደረጃ ጥቅሙን ተረድቶ ምርቱ በስፋት እየለማ ይገኛል ብለዋል:: ለዚህም የግብርና ባለሙያዎች እገዛ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ነው የተናገሩት::
የዞኑ አትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ሀውልቱ ታደሰ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በዞኑ በ14 ወረዳዎች በስፋት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: አርሶ አደሮችም በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል::
አቶ ሀውልቱ እንዳሉት በቡና ክላስተር (ኩታ ገጠም) በላይ አርማጭሆ እና በአቮካዶ ክላስተር ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል::
ለአብነትም የላይ አርማጭሆ ወረዳ በተያዘዉ ዓመት ከ634 ሺህ በላይ የቡና ችግኞችን ማዘጋጅቱን አቶ ሀውልቱ ተናግረዋል:: በዞኑ አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸዉን ገልጸዋል:: ዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆንም በኩታ ገጠም መልማት አለበት ብለዋል አቶ ሀውልቱ::
እንደ ክልል ከአቮካዶ ምርት የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሀውልቱ የክልሉን ዕቅድ ለማሳካትም ዞኑ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ አክለዋል::
አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከምጣኔ ሀብታዊ ጥቅሙ ባሻገር መቀንጨርን ስለሚከላከል ምርቱን ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል::
የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለበሽታ ሊጋለጥ የሚችለዉ ከእንክብካቤ ጉድለት ነው የሚሉት አቶ ሀውልቱ አርሶ አደሩ በቂ ክትትልና እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል:: በሌላ በኩል የግብርና ባለሙያዎችን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት በትኩረት ይሠራል ብለዋል::
(ደስታ ካሳ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም