በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ሰላም በር መስጊድ ኢማም (አሰጋጅ) ናቸው:: የተወለዱት በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ከነፋስ መውጫ ወጣ ብሎ ነው:: የመደበኛ ትምህርታቸውን እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል:: ቤተሰቦቻቸው የሃይማኖት ትምህርት እንዲማሩ ይፈልጉ ነበር:: አንድ ዕለት ወዳጃቸውን መንገድ ላይ አግኝተውት የት እየሄደ እንደሆነ ሲጠይቁት ወደ ሃይማኖት ትምህርት ቤት እንደሆነ ይነግራቸዋል:: በዚህም ምንም ሳያመነቱ አብረውት ያቀናሉ፡- ወደ ወሎ መርሳ:: ከቁርዓን ጀምረውም ሀዲስ እና ተፍሲርን አጠናቀዋል:: የረመዳን ወርን አስመልክተን ከሼክ መሐመድ አብራር ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ::
ወደ ሃይማኖት ትምህርት እንዴት ገቡ?
የመደበኛ ትምህርት ትንሽ ሞክሬያለሁ፤ በ1984 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ:: አስታውሳለሁ ሚያዝያ 13 ቀን 1984 ዓ.ም ጓደኛዬ፣ ሙሳ ይባላሉ፤ አሁን ሼክ ሆነዋል፤ እሳቸው የሃይማኖት ትምህርት ሊማሩ ሊያቀኑ መሆኑን ሳውቅ አብሬያቸው ሄድኩ:: የሄድነው በሰሜን ወሎ ዞን ሀርቡ ወረዳ መርሳ ዙሪያ ቁራኔ የሚባል ሀገር ነው:: የመልዓክም ሆነ የነብይ ስሪት ያላደለውን፣ የአላህ /ሱ.ወ/ ስሪት የሆነውን ቁርዓን አሊፍ (ሀ) ብዬ ጀመርኩ:: አረብኛ ስለማልችል ትርጉሙን ሳላውቅ በሕጉ መሠረት ድምጹን ብቻ ነው ያጠናሁት::
ፍቂ ወደተባለው ሼሪያተ ኢስላምን (የእስላም ሕግን) የምናውቅበት ክፍል ተዘዋወርኩ:: እንዴት ፈጣሪን ማወቅ፣ መጾም፣ መስገድ፣ ዘካ መስጠት እንዳለብን እና መሠረታዊ የኢስላም ሕጎችን መከወን እንደሚጠበቅብን ተማርኩ፤ ከንጽህና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ ከሦላት በፊት እንዴት ኡዱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ እንዴት ገበያ መገበያየት፣ መጋባት፣ እናት እና አባቱን እዲሁም ሰውን ማክበር፣ በአጠቃላይ በአላህ /ሱ.ወ/ ሕግ መሠረት እንዴት መኖር እንደሚያስፈልግ አወቅኩ::
ቀጥሎ አረብኛ ቋንቋን መማር ጀመርኩ፤ ነሁ እና ሶርፍ ቀጣይ የተማርኩት ነው፤ ዐረፍተ ነገርን መረዳት፣ የቃላትን ፍቺ ማወቅ፤ እንዲሁም ጊዜን ወይም አጠቃላይ ሰዋሰውን አጠናሁ:: ቅኔ መሳይ ሀሳብን አስገራሚ አድርጎ እና አሳጥሮ መግለጽን የሚያስችል በመንጢቅ እና በላኻ በሚባል ትምህርት አውቄያለሁ::
በመጨረሻ ሀዲስ እና ተፍሲርን አጠናቀቅን:: ሀዲስ ነብዩ መሐመድ /ሰ.ዐ.ወ/ አጠቃላይ አስተምህሮታቸው እና በተግባርም ያሳዩበት በስድስት ኪታቦች የቀረበ ነው:: ተፍሲር ደግሞ በመጀመሪያ ላይ የቀራነውን ትርጉሙን የሚሳውቅ ነው:: በዚህ ሂደት ካላለፉ ቃል በቃል ተርጉመው ቁርዓንን መረዳት አይቻልም:: ትምህርት ቢማሩት አያልቅም፤ ነገር ግን ራስክን ለመምራት፣ ምዕመኑንም ለማስተማር እና ለማገልገል ይረዳል:: ከትምህርቱ በኋላ ያለው ትግል ያወከውን በተግባር መኖር እና የአላህን /ሱ.ወ/ ፍላጎት መፈጸም ነው ዋናው ፈተና::
አዛን ማለትስ ምን ማለት ነው? ትምህርቱ እንዴት ይገኛል?
አዛን ማለት የሶላት ሰዓት መድረሱን ማሳወቂያ ነው:: ሰዎችን ለሶላት ማንቂያ ነው፤ ሕግ አለው፤ ድምጽ ያለው ሁሉ ዝም ብሎ አይለቀውም፤ ቃላት አሉ፤ የሚሳቡ እና የሚቆረጡ ቃላት አሉ፤ የተመረጠ ሰው ነው አዛን የሚያደርገው፤ እኔ በዋነኛነት አገልግሎቴ ማሰገድ ነው፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ አዛን አደርጋለሁ::
ረመዳን ምን ማለት ነው? ታሪካዊ አመጣጡስ ምንድን ነው?
አላህ /ሱ.ወ/ “እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ በባለፉትም ነቢያቶች ግዴታ ሆኖ እንደተጻፈባቸው ሁሉ በእናንተም ላይ ጾም ግዴታ ሆኖ ተጻፈባችሁ” ብሏል፤ ረመዳን በሂጂራ የቀን መቁጠሪያ ዘጠነኛ ወር ነው:: የሂጂራ ቀን መቁጠሪያ ከእኛው በየ ዓመቱ 10 ቀን ይቀንሳል፤ የቃሉ ትርጓሜም መቃጠል ማለት ነው:: ስለሆነም በረመዳን አላህ /ሱ.ወ/ በትዕቢትም ሆነ ያለማወቅ ያጠፉትን ኀጢያት የሚያቃጥልበት ነው::
ረሱል አለይሂ ወሰላም በ40 ዓመታቸው ነብይ ሆኑ፤ በ53 ዓመታቸው ሂጂራ አደረጉ በሁለተኛው ዓመት መካ ተቀመጡ:: ከዚያ በኋላ ረሱል አለይሂ ወሰላም እና በአማኞች ጾሙ ተጻፈባቸው:: መካ ከዘለቁ በኋላ ከአንድ ዓመት በኋላ ማለት ነው:: ሕጉም የመጣላቸው በቁርዓን ነው:: ነብይ ከሆኑ ጀምሮ የተለያዩ ሕጎች ከአላህ እየወረደ መቆየቱን መገንዘብ ያስፈልጋል:: የረመዳን ጾምም ቁርዓን መውረድ ከጀመረ ከ15 ዓመታት በኋላ ተጀመረ ብሎ መተርጎም ይቻላል:: አጿጿሙም በጥንቱ ዘመን ጠንከር ያለ ነበር፤ አሁን ሕጉ ላልቶልናል፤ ሌሎች ሕጎችም ላልተዋል፤ ለምሳሌ በእነ ሙሳ ዘመን ዘካ የሚሰጠው አንድ አራተኛ ነበር፤ አሁን አንድ 10ኛ ሆኗል:: የማይሻረው ሕግ አላህን በመገዛት እና እሱነቱን ጠንቅቆ በማወቅ ማመን ነው::
በረመዳን ጾም ወቅት ምን ምን ነገሮች ይደረጋሉ?
ረመዳን አላህ /ሱ.ወ/ ለየት ያለ ረህመቱን (ምህረቱን) የሚያወርድበት ነው:: ስለሆነም በዚህ ወር የሰው ልጅ ኢባዳ ማብዛት አለበት (አብዝቶ ለፈጣሪው መገዛት አለበት)፤ ከምንጊዜውም በላይ ቁርዓንን አብዝቶ መቅራት ይጠበቅበታል:: ዚክር ማብዛት አለበት፤ ይህን በመፈጸማችን ምንዳውን እስከ 70 እጥፍ ይይዝልናል:: ሌሎች ኢባዳዎች ደግሞ በፈርድ ይያዙልናል፤ ስለሆነም ይህን በረመዳን እናደርጋለን::
ከዚህ ባሻገር የታረዙትን በማልበስ፣ ለተቸገሩ በመስጠት፣ የታመሙ በማጽናናት፣ የተጣሉ በማስታረቅ ያልፋል:: ረሱል አለይሂ ወሰላም “እንደ ሀይለኛ ንፋስ ነው ስጦታቸው” ይላል ቁርዓን፤ በመሆኑም ለተቸገሩ በመስጠት እና ምዕመኑን በማስተማር እንዳሳለፉት አገልጋዩ እና ምዕመኑም በዚሁ መንገድ ያሳልፋል:: ማታ ደግሞ የተቸገሩትን ምዕመኑ ያስፈጥራል፤ የተለያዩ ስግደቶችን ይሰግዳል፤ ከሁለት ረክዓ ጀምሮ እስከሚችለው ይሰግዳል፤ ነብያችን /ሰ.ዐ.ወ/ በሌላው ጊዜ 13 ወይም 11 ረክዓ ይሰግዳሉ፤ በረመዳን ደግሞ 23 ይሰግዳሉ፤ ሶላት ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው፤ ሶላት ከትምክህት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከጠብ አጫሪነት፣ ከአጉል ኩራት እና ሌሎች በሽታዎች የምታጠራ እና ወደ አላህ /ሱ.ወ/ የምታቀርብ መድሃኒት ናት::
የረመዳን ጾም ሃይማኖታዊ እና ሰብዓዊ ጠቀሜታው ምንድን ነው?
የረመዳን ጾም ጠቀሜታው ለሙስሊሙ ማኀበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዱኒያ (ዓለም) ነው:: አላህ /ሱ.ወ/ ትልቅ ምህረት በሰው ልጅ ላይ ያወርዳል:: ከዚህ በላይ ሰው ለሰው የሚረዳዳበት፣ ፍቅር የሚሰበክበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፤ ሰው ከሌላ ሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱ ጋር የሚታረቅበት ወር በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው:: በሌሎች ወራት የማታገኘውን እዝነት፣ ሰላም፣ ፍቅር እና እርቅ በረመዳን ታየዋለህ::
በሀገራችን ያለውን አለመረጋጋት በረመዳን መንፈስ እንዴት ማስወገድ እንችላለን?
ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የሀገራችን እሴት የነበረው መከባበር እየተሸረሸረ መጥቷል:: ትልቅ ሰው ማክበር፣ የበላይን ማክበር እና የሃይማኖት አባቶችን ማክበር እየቀረ መጥቷል:: ከዚህ አልፎ ሰው ሞተ ሲባል ማስደንገጡን አቁሟል:: እኛ እኮ ልጆች ሆነን አንድ ሰው ፍየል እንኳ ሲሞትበት ዘመድ ወዳጅ ያጽናናዋል:: በመሆኑም አሁን ካለንበት ችግር ለመውጣት መከባበር፣ መረዳዳት፣ መግባባት ያስፈልጋል:: እንኳን በሰው ሕይወት በእንስሳ ላይ መጨከን የለብንም::
ሰላምን በማስፈን ረገድ የሃይማኖት አባቶች እና የምዕመኑ ሚና ምንድን ነው?
የሌላውን ጥንቅቄ አላውቅም በተለይ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ምንም ሳያውቁ የእስልምና ካባ ለብሰው ምዕመኑን የሚያታልሉ እና የተሳሳተ አስተምህሮ የሚሰጡ አሉ:: በእስልምና መንገድ “ስልጣን ስጡኝ ልምራ” አይባልም:: አንድ ጊዜ ነብያችንን /ሰ.ዐ.ወ/ አንድ ባልደረባቸው “ወደ አንድ ሀገር ሹመው ይስደዱኝ?” አላቸው፤ “በእኛ እስልምና እኮ ምረጡኝ ላለ ሹመት አንሰጥም” አሉት:: ሰው በእጅጉ ስልጣን ከወደደ እና “ምረጡኝ” ካለ ጥቅም አንግቦ መጥቷል ማለት ነው፤ ስለዚህ ለወገኑ አይጠቅምም:: አብሮ የመጣው ሰው ደንግጦ “ይህንን አስቦ መምጣቱን ባውቅ አብሬ አልመጣም ነበር” አለ:: ረሱል አለይሂ ወሰላም እሱን ሹመው ሰደዱት::
የፖለቲካው ውጥንቅጥ እንዳለ ሆኖ የሃይማኖቱ ውጥንቅጥም ሀገራችንን ዋጋ እያስከፈለ ነው:: እምነትን ለባለቤቱ መስጠት ያስፈልጋል:: የገጠር አባቶቻችን እስልምናን እየተናገሩ ሳይሆን በተግባር እያሳዩ ነው መርተው ያሳዩት::
ሁሉም ወደ ቀልቡ መመለስ አለበት፤ ራሱን ይፈትሽ:: ለሰላም ሁሉም ድርሻ አለው፤ ይህም ቤተሰብን ከማነጽ ልጆችን በሥርዓት ከማሳደግ ይጀምራል:: ከልቡ ሃይማኖተኛ የሆነ ዜጋ መፍጠር ይገባል፤ ይህ ከሆነ ሰው ለመግደል፣ ሌላውን ለመጉዳት እና ጥፋት ለማድረስ አዕምሮው አሺ አይለውም:: እስልምና የሚያስተምረው ሥርዓትን ነው፤ ይህን የማይከተል ሰው በዚህ ዓለም ሆነ በዛኛው ምን እንደሚገጥመው በግልጽ አስቀምጧል:: ሥርዓት ያለው ትውልድ በመፍጠር ሀገርን ማጽናት ይቻላል::
ሁሉም በየእምነቱ በሰላም፣ በመተሳሰብ እና በፍቅር መኖር ይጠበቅበታል:: ሀይማኖት የግል ነው፤ ሀገር የጋራ ነው:: በመሆኑም በሀዘኑም በደስታውም እስከዛሬ እንደኖርነው እሴታችንን ጠብቀን ሀገራችንን ከጠላት እየጠበቅን ድህነትን እየጣልን መቀጠል ይገባናል:: ለዚህም የሃይማኖት ትምህርት ወሳኝ ነው::
እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም