ሀገር በትናንት ትዝታ፣በዛሬ ሥራ እና በነገ የአብሮነት ተስፋ የምትቆም የሕዝብ መለያ ናት። ኢትዮጵያ የትናንት ትዝታዋ የዛሬም የአብሮነት ገመዶች ናቸው። የአድዋ የጦርነት ታሪክ፣ የላሊበላ ኪነሕንፃ ፣ የአክሱም ሀውልት፣ የሀረሩ የጀጎል ግንብ፣ የገዳ ስርዓት፣ ቅዳሴ እና አዛኑ ተደማምሮ የሀገር መልክ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ሀገሪቱን እየተፈራረቁ የመሩ የፖለቲካ ልሂቃን በፈጠሩት የጥላቻ እና የመፈራረጅ ተረክ ምክንያት የትናንት ትዝታም፣ የነገ ተስፋም ጨልሞ እንዲታይ ሲያደርግ ይስተዋላል።
የአንድ ሀገር ሕዝብ በተቋማዊ መዋቅር፣ በሕግ እና ሥርዓት አብሮ የመኖር ተስፋ ሊኖረው ይገባል። ይህ የሚሆነው ደግሞ በሀገሪቱ ፍትሕ፣ ተጠያቂነት ያለበት አሰራር፣ ለዜጎች የቆመ ሥርዓት ሲኖር ነው። የሀገር ፍቅር በስብከት፣ በተረት፣ በወግ፣ በዘፈን ብቻ አይመጣም። የሀገር ፍቅር ሁሉም ወገንን ያሳተፈ እና ለሁሉም ወገን ዕድልን የሰጠ መንግሥታዊ ውቅር ሲኖር ነው።
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የሕዳሴው የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያን ብሄረሰቦች በአንድ ያስተሳሰረ እና ለነገ ተስፋን የቸረ ፕሮጀክት ነበር። ያ ቢሆንም በፕሮጀክቱ ውስጥ ብሎም በሀገሪቱ የተፈጠሩ የአስተዳደር ብልሽቶች፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች ግድቡን በመሰረታዊነት ባያስተጓጉሉትም፣ በታሰበለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ግን ፈተና ውስጥ ከተውታል። ሕዝብ መልማት፣ ሰላም መሆንን እና የተሻለ ሕይዎትን መኖር ይፈልጋል። ለዚህም የሕዳሴውን ግድብ እንዲጠናቀቅ ያልደገፈ፣ ሀሴት ያላደረገ ኢትዮጵያዊ የለም ለማለት ያስደፍር ነበር። ልማት የአንድን ሀገር ሕዝብ አብሮነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው። የታላቁ ሕዳሴ ግድብም ለዚህ አብነት ሆኖ መጠቀስ የሚችል ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም ይሄ የሀገር ምልክት የልማት ፕሮጀክት እንዲጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ርብርብን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የሚታመን፣ ግልፅ እና ፍትሃዊ አሰራርን ማስፈን ያስፈልጋል። ሀገር በመሳሪያ አፈሙዝ ከምትታረስ ዶማ እና አካፋ የያዙ እጆች እንዲበዙ እውነተኛ የሰላም አማራጭ፣ ከሰላሙ ቀጥሎ ደግሞ እንደ ዓባይ ግድብ አይነት ታሪክ ለዋጭ ፕሮጀክቶች ያስፈልጋሉ። ለዚህም ለሰላሙም፣ ለልማቱም ትኩረት መስጠትን ይሻል። ምንጊዜም ቢሆን ያለሰላም ልማት የለም፤ ያለ ልማትም ሰላም አይኖርም። ሰላም እና ልማት መንትያ በመሆናቸው ሳይነጣጥሉ ለሁሉም መሥራት ግድ ይላል። ዓባይ ጓዳችንን አልፎ የሲና በረሃን የሚያረሰርሰው፣ ሜዲትራኒያንን የሚሞላው እኛ ውሃ ተርፎን፣ መብራት ኑሮን አይደለም። ውስጣዊ ሰላም ባለማግኘታችን ለስልጣኔ እና ዕድገት ጀርባችንን ሰጥተናል። አሁንም ግጭቶች በንግግር እና በውይይት ይፈቱና ሰላም የሰፈነበት ሀገር ይኑረን። ሰላሙን ተከትሎ ደግሞ ልማት ይመጣል። አንድ ማዕድ ተቋርሰው፣ አንድ ትምህርት ቤት የተማሩ ዜጎች በተለያየ ጎራ ተሰልፈው የሚዋጉበት ጊዜ አልፎ በጋራ የሚሰሩበት ጊዜ እንዲመጣ ከእልህ፣ ከአጉል እብሪት እና ፍረጃ የወጣ ሁሉን አካታች ሥርዓተ መንግሥት እና የሰላም አማራጭ ያስፈልጋል። ያ ሲሆን ዓባይ ብቻ ሳይሆን የልማት ምንጭ የሚሆነው የኢትዮጵያ ጫካ፣ በረሃ፣ ውሃማ አካላት ሁሉ የዕድገት አውድማ ይሆናሉ።
(የሺሃሳብ አበራ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።