የተሳሳተ ትርክት እንዲታረም …

0
147

ዩናይትድ ስቴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፒስ (United States Institute of Peace) የተሰኘው ተቋም አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት፣ ጎጠኛ አስተሳሰብ፣ ድህነት፣ ሌብነት፣ … የአፍሪካ ጠንቆች መሆናቸውን ያብራራል፤ ተቋሙ በናይጄሪያ ያለውን ብሔር ተኮር ግጭት መነሻ አድርጎ በድረ ገጹ  ባስነበበው መረጃ አክራሪነት እና ብሔርተኝነት ለዘመናት ሀገሪቱን ሲያምሳት እንደነበር አመላክቷል። በአሁኑ ወቅት ታዲያ በሀገሪቱ  የብሔር ፖለቲካ ቦታ ስለሌለው የብሔሮች መብዛት ስጋት አልሆነባትም።

ሪሰርች ጌት (Research Gate) የተባለ ድረ ገጽ እንዳስነበበው ደግሞ ከ140 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ናይጄሪያ 250 ያህል ብሔረሰቦች መገኛ ናት፤ በተመሳሳይ ከ54 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ኬንያም ከ70 በላይ ብሔረሰቦች ይገኛሉ። ሁለቱ ሀገራት ታዲያ ብሔር በወለደው ግጭት ሲታመሱ ነበር፤ ነገር ግን ሀገራቱ በወሰዱት ቁርጠኛ የእርምት እርምጃ እና ለሕዝቡም ስለ ብሔርተኝነት መዘዝ በፈጠሩት ግንዛቤ መዘዙን በእጅጉ ቀንሰውታል።

ሀገራቱ ብሔር ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴን እስከ ማገድ ደርሰዋል:: ለአብነትም ከዐሥር ዓመት በፊት በኬንያ ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ብሔር ተኮር ግጭት ተቀስቅሶ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፤ ይህን ተከትሎም የብሔርተኝነት ፖለቲካ ማራመድን ሀገሪቱ በሕግ አግዳለች።

በተመሳሳይ በናይጄሪያ ስለ ብሔርተኝነት ማውራት ዘብጥያ ሊያስወረውር የሚችል የተወገዘ ድርጊት ነው። በሀገራችንስ? ስለ ብሔርተኝነት በማቀንቀን አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ አድማሱን አስፍቶ ይስተጋባል። በርካቶችም በብሔራቸው ምክንያት እየተገደሉ ነው።

ይባስ ብሎም “የሀገራችን ብሔሮች የቀደመ ግንኙነት የተዛባ ነበር” በሚል ሕገ መንግሥታዊ ከለላ በመስጠት ጦሱ አድማሱን እንዲያሰፋ አድርጓል፤ ለአብነትም የሀገራችን ሕገ መንግሥት መግቢያ “… መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና…” ይላል፤ የተዛባ ግንኙነት በሚል የተገለጸው ደግሞ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትን የሚያቀነቅን ነው።

ይህ መሆኑ ታዲያ የሀገራችን ብሔረሰቦች አንዱ ሌላኛውን በጥርጣሬ እንዲመለከቱት አድርጓል:: ይህም ለበርካታ ዓመታት ሲቀነቀን የቆዬ በመሆኑ ጦሱ በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን እያመሳት ይገኛል:: የጦሱ ፍሬ እየታጨደ ይገኛል። በተለይ ደግሞ አማራው ላይ በተሠራበት የተሳሳተ ትርክት ምክንያት በመላው ሀገሪቱ በማንነቱ ምክንያት የችግሩን ገፈት እየተጎነጨ ነው።

ቹቹ አለባቸው (ዶ/ር) በአማራ ክልል ሥራ አመራር ተቋም የምርምር እና ሥርፀት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም “ዳገት ያበረታው የአማራ ፍኖት” የሚለው መጽሐፍ ደራሲ ናቸው፤ በአማራ ፖለቲካም የብዙ ዓመታት ልምድ ያላቸው ናቸው። ቹቹ (ዶ/ር) ከበኩር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት የአማራ ሕዝብ ችግሮች ውስብስብ እና ሥር የሰደዱ ናቸው፤ ጠላቶቹም የበዙ ናቸው።

የአማራን ሕዝብ ማዳከም የተጀመረው ከጣሊያን ወረራ በፊት መሆኑን የሚናገሩት ቹቹ (ዶ/ር)፣ የተለያዩ የውጭ ጸሐፍት አማራን አስመልክተው ይጽፏቸው የነበሩ ጽሑፎች በተለይ አማራን እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን ነጥሎ በማጥቃት ሌላው ዓለምም ይህንን ሕዝብ በመጥፎ እንዲስለው ጥረት ያደርጉ ነበር ብለዋል::

ምሁሩ እንዳሉት አማራው በተሠራበት የፈጠራ ትርክት ምክንያት ላልበደለው በደል መከራን እንዲያጭድ የተደረገ ሕዝብ ነው:: ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችም በተሠራበት መጥፎ ትርክት ምክንያት እንደ ጨቋኝ ነው የሚመለከቱት።

ቹቹ (ዶ/ር) አለባቸው አክለው እንዳብራሩት የአማራ ሕዝብ በተሳሳቱ ተረኮች ምክንያት ያልደረሰበት መከራ እና ግፍ የለም። በፖለቲካ ሥልጣን በሚገባው ልክም የተወከለ አይደለም፤ ከዚህ በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ የአማራን ሕዝብ በሚጐዳ መልኩ የተረቀቀ ነው። አሁን ላይ በስፋት የሚቀነቀነው የብሔር ፖለቲካም አማራን በጨቋኝነት የፈረጀ ነው።

በሌላ በኩል ፌዴራላዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ አስፈላጊዋ ቢሆንም ሲዋቀር ግን ብዙ ነገሮችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት። በተለይ የሕዝብን አንድነት የሚያፀና መሆን ይኖርበታል:: በፌዴራል ሥርዓቱ ምክንያት ሕዝብ ከሕዝብ ጋር መጋጨት እና የቂም ቁርሾ መያዝ የለበትም። ከችግሮቹ በመማር፣ ችግሮቹን ለማስወገድ መሥራት ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝብ የሚጠበቅ አንኳር ጉዳይ ነው። መንግሥትም ይህንን ጉዳይ በተገቢው መልኩ መረዳት አለበት፣ እንደ ቹቹ (ዶ/ር) ማብራሪያ።

በርካታ የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት የብሔር ፖለቲካ ጦስ ኢትዮጵያን እስኪያፈርስ መጠበቅ አይገባም። በመሆኑም የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም የሕዝብ አንድነት እንዲጠነክር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባው ነው የሚናገሩት።

የአማራ ሕዝብ በተሳሳቱ ትርክቶች ምክንያት ግፎች ሲፈጸሙበት ቆይተዋል። አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። ከዚህ ጋር በተገናኜ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር ውይይት ማድረጋቸውን  በማሕበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አጋርተዋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረም እና ለሀገር ግንባታ ሂደቱ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በሕዝብ አንድነት ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ያሉት አቶ አረጋ፣  የአማራ ሕዝብም የተሳሳቱ የፖለቲካ ትርክቶች ታርመው በምክክር ወደ ተሻለ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲገባ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያነሳ መቆየቱን አክለዋል።  በሐሰተኛ ትርክት የተፈጠረውን ሐሳብ በማረም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽዖ ለማድረግ ታዲያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው የጠቆሙት።

በመሆኑም ኢትዮጵያን ከገባችበት ቅርቃር መንጥቆ ለማስወጣት፣ አማራውም በተሳሳተ ትርክት ምክንያት እያስተናገደ የሚገኘውን ግፍ ለማስቀረት ሁሉም የተስማማበት ሕገ መንግሥት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ምሁራን ጠቁመዋል።

ከዓለም ምን እንማር?

የችግሮች ማዕከል የሆነችው አፍሪካ አክራሪ ብሔርተኝነትም በእጅጉ እየፈተናት ይገኛል። ጥቁር አሻራም አሳርፎባታል። ለአብነትም ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። ሀገራቱ በወሰዱት የእርምት እርምጃ ታዲያ በአሁኑ ወቅት በነበር አስቀርተውታል። ደቡብ አፍሪካ ሁሉንም አካታች ሕገ መንግሥት በመተግበር ችግሩን ተሻግራዋለች።

በተመሳሳይ ብሔርተኝነት በአንድ ጀንበር አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጎቿን የነጠቃት ሩዋንዳ በአሁኑ ወቅት ብሔርተኝነትን በሕግ ከማገድ ባለፈ ሕዝቡም ብሔርተኝነትን እንዲጸየፍ ግንዛቤ ፈጥራለች። ብሔር ተኮር እንቅስቃሴ ከተገኘም የማያድግም እርምጃ ትወስዳለች።

በመሆኑም ከላይ ከተጠቀሱት ሀገራትም ሆነ ከሀገራችን የቀደመ ታሪክ በመማር አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የዘርፉ ምሁራን የሚጠይቁት።

ከምንም በላይ ደግሞ በተሠራበት የተሳሳተ ትርክት ምክንያት እንደ ሕዝብ አማራው እየተፈጸመበት ካለው ግፍ እና ሀገራችንንም ከገባችበት ከባድ ስጋት ለማስወጣት ሁሉን አካታች ሕገ መንግሥት ዕውን ማድረግ፣ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ነው። በቅርብ በተደረገ ጥናት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር ወይም እንዲሻሻል እንደሚፈልግ መረጋገጡን ልብ ይሏል።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here