የከፍተኛ ሊግ ክለቦቻችን አቋም

0
193

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚመራቸው ውድድሮች መካከል የሀገሪቱ ሁለተኛው የሊግ እርከን የሆነው ከፍተኛ ሊግ አንዱ ነው:: የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር ወደ ትልቁ  የሊግ እርከን ማለትም ወደ  ፕሪሚየር ሊጉ ለመቀላቀል የሚደረግ ትንቅንቅ ነው:: ይህ ትልቅ የእግር ኳስ መድረክ በ2007 ዓ.ም በአዲስ ቅርጽ ተጀምሯል:: የሰሜን እና የደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሚል ተከፍሎ በሁለት ምድብ ነው የተጀመረው:: ከፍተኛ ሊጉ በአዲስ መልኩ ከተጀመረ በኋላ ፋሲል ከነማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ፣ ባሕር ዳር ከተማ እና የመሳሰሉት ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጋቸው ይታወሳል::

የዘንድሮው የ2016 ዓ.ም የከፍተኛ ሊግ ውድድር ህዳር አንድ ቀን በአዲስ አበባ እና ሀዋሳ ከተሞች ነው የመጀመሪያው ዙር የተጀመረው:: በዚህ መድረክ በሁለቱም ምድቦች 28 ክለቦች እየተሳተፉ ነው:: ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያድጉ ክለቦች ቁጥር መቀነስ እና ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የሚወርዱ ክለቦች ቁጥር መጨመር ፉክክሩን ጨምሮታል:: ሁለት ቡድኖች ብቻ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያድጉ ሲሆን አምስት ክለቦች ደግሞ ወደ አንደኛ ሊግ እንደሚወርዱ  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ያስቀመጠው አዲሱ ሕግ እና ደንብ ያትታል:: ከፍተኛ ትንቅንቅ እየተደረገ ባለበት የወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር አራት የአማራ ክልል ክለቦች እየተሳተፉ ነው:: ወልዲያ ከነማ፣ ደሴ ከነማ ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ሰሜን ሽዋ ደብረ ብርሃን  በመድረኩ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው::

በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና በመሳተፍ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጉን ያረጋገጠው ሞጣ ከነማ በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በውድድሩ መካፈል አልቻለም:: ሞጣ ከነማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ሊግ የደረሰ ድንቅ ክለብ መሆኑን አሳይቷል:: በዚህ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ቀንሷል:: 28 ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው መርሐ ግብራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ::

ደሴ ከነማ በምድብ አንድ ተደልድሎ ጨዋታውን እያከናወነ ሲሆን ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ ጥንካሬውን እያስመሰከረ ነው:: ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በ34 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው:: ምንም እንኳ ወደ ፕሪሜየር ሊጉ ለመግባት በሚደረገው ፉክክር ከመሪው አርባ ምንጭ ከተማ በ17 ነጥቦች ቢርቅም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል:: ውድድሩ ሲጀምር ደካማ አጀማመር ያደረገው ደሴ ከነማ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ እና ሜዳ ላይ ለውጥ እያሳየ መጥቷል:: ካደረጋቸው 19 ውድድሮች በአስሩ አሸንፏል:: በአምስቱ ሲሸነፍ በቀሪው አራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል::

ደሴ ከነማ ከአርባ ምንጭ ቀጥሎ በምድቡ አስፈሪ የፊት መስመር ያለው ክለብ ነው:: 32 ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ ማሳረፍም ችሏል:: ወደ መሪው ክለብ ለመጠጋት እና ተፎካካሪ ለመሆን ግን የኋላ ክፍሉ ችግር መፈታት እንደሚኖርበት እስካሁን ያገኘው ውጤት ያመለክታል፡፡ በአማካኝ በየጨዋታው ሁለት ግቦች እና ከዛ በላይ የተቆጠረበት ሲሆን በአጠቃላይ እስካሁን 24 ግቦች ተቆጥሮበታል::

ደሴ ከነማ እነዚህን እና ሌሎችንም የሜዳ ላይ ችግሮችን ማስተካከል ከቻለ የበለጠ ተፎካካሪ እና ጠንካራ ክለብ ሆኖ መቅረብ ይችላል:: በ1980ዎቹ በወሎ ምድር “የወሎ ምርጥ” የነበረውን ስም እና ዝናም ይመልሳል ተብሎ ይገመታል::

በዚሁ ምድብ ያለው ደብረ ብርሃን ከነማ ከአምናው የተሻለ የውድድር ጊዜ አይደለም እያሳለፈ ያለው:: እንዲያውም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ ክለቡ ትንሽ ደከም ብሏል:: ውድድሩ ሲጀመር በተደጋጋሚ የገባበት የውጤት ቀውስ አሁን ላይ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል:: ብርሃኖቹ ከእነርሱ ምድብ ካለው ደሴ ከነማ በሰባት ነጥቦች አንሰው በ27 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጡት::

እስካሁን ካደረገው አጠቃላይ 19 ጨዋታዎች በስምንቱ አሸንፏል፣ በተመሳሳይ በስምንቱ ተረቷል:: በሦስቱ ደግሞ አቻ ነው የተለያየው:: በተጋጣሚ መረብ ላይ ካስቆጠራቸው 23 ግቦች የበለጠ 25 ግቦች ተቆጥረውበታል:: ብርሃኖቹ የኋላ ክፍላቸውን ችግር በዘላቂነት የሚፈቱ ከሆነ በቀላሉ ወደ መሪው አርባ ምንጭ ከተማ የሚያስጠጋቸውን ውጤት መሰብሰብ ይችላሉ::

በከፍተኛ ሊግ የሚሳተፈው ሌላኛው የአማራ ክልል ክለብ ወሎ ኮምቦልቻ በዚሁ በምድብ አንድ ነው ያለው :: ባሳለፍነው ዓመት በምድብ አንድ በ28 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር ያጠናቀቀው:: በአንድ ነጥብ ልዩነትም ከመውረድ መትረፉ አይዘነጋም:: ክለቡ የአምናውን ደካማ አቋሙን ዘንድሮ እያሳየ ይገኛል:: ክለቡ ወራጅ ቀጣና ውስጥም ነው የሚገኝው:: አሥራ ሁለት ነጥቦችን ብቻ በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል::

እስካሁን 19 ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አራቱን ብቻ ነው በድል የተወጣው::  በአምስት ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋራ ገና ከወዲሁ በአስር ጨዋታዎች ደግሞ በመሸነፍ ከአምናው የከፋ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ነው:: ወሎ ኮምቦልቻ ደካማ የፊት መስመር እና የኋላ ክፍል ካላቸው የከፍተኛ ሊግ ክለቦች መካከልም አንዱ ነው:: ግብ ለማስቆጠር ዓይን አፋር የሆነው የፊት መስመሩ 19 ብቻ ግቦችን ሲያስቆጥር የተከላካይ ክፍሉ ደግሞ 28 ግቦች ተቆጥረውበታል:: ወሎ ኮምቦልቻ በቀሪ ጨዋታዎች ያሉበትን ችግሮች ማሻሻል ካልቻለ በቀጣይ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ላንመለከተው የምንችልበት ዕድል ሰፊ ነው::

ወልዲያ ከነማ በከፍተኛ ሊጉ ረዥም ጊዜ የቆየ ሲሆን ድጋሚ ወደ ላይኛው የሊግ እርከን ለመሸጋገር ዳገት ሆኖበታል:: ከዚህ በፊት በፕሪሚየር ሊጉ ልምድ ያለው ወልዲያ ከስድስት ዓመታት በፊት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ከወረደ በኋላ አልተመለሰም:: በተደጋጋሚ ሞክሮም አልተሳካለትም:: ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት ባሳለፍነው ዓመት ጥሩ ፉክክር ማድረጉ ግን የሚታወስ ነው::

ዘንድሮ ግን የአምናው ጉልበቱ ዝሎ አቅሙ ተዳክሞ ተስተውሏል:: አሁን ላይ ከመሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ19 ነጥቦች ርቆ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል:: ስድስት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በስድስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል:: በሰባት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፏል:: አሁን ላይም ከወራጅ ቀጣናው በአምስት ነጥብ ብቻ ርቆ ይገኛል:: ለክለቡ መዳከም በሁሉም የሜዳ ክፍል ያሉት ተጫዋቾች በቀድሞ ጠንካራ አቋማቸው ላይ አለመገኘታቸው አንደኛው ምክንያት ነው:: በአስተማማኝ ከወራጅ ቀጣናው ለመራቅም ከፊት ያሉበትን ፈተናዎች በድል መወጣት ይኖርበታል ተብሎ ይገመታል::

ክለቦቹ በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ወደ ውድድር መሄዳቸው በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል:: የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድርን በሁለቱም ምድብ ባሳለፍነው ዓመት ከፕሪሚየር ሊጉ የወረዱት ክለቦች ናቸው እየመሩ ያሉት:: ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምድብ አንድን አርባ ምንጭ ከተማ ከተከታዩ ነገሌ አርሲ በስምንት ነጥብ ርቆ በ51 ነጥብ እየመራ ይገኛል:: ምድብ ሁለትን ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ43 ነጥብ እየመራ ነው::  ከተከታዩ ኦሮሚያ ፖሊስ ጋርም ያለው የነጥብ ልዩነት 10 ደርሷል::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here