አዲሱ የኅይል ምንጭ

0
217

ዕፅዋትን  ለፈጠራ መነሻ በማድረግ በወረቀት ላይ በስሱ በተነጠፉ የማግኒዥዬም ቀጫጭን ሽቦዎች አማካይነት በዓየር ውስጥ ከሚገኝ ኦክስጂን እና ውኃ የኃይል ምንጭ (ባትሪ) ማግኘት መቻሉን ቴክ ኤክስኘሎር ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በጃፓን ቶሆኩ ዩኒቨርስቲ የተመራማሪዎች ቡድን በብረት እና ኘላስቲክ የሚሰሩ ቁሳቁስ ጥገኝነትን ለመቀነስ በወረቀት ላይ በስሱ የተቀቡ ማግኒዢዬም ጥቅልል ሽቦዎችን ከውኃ እና ዓየር ጋር በማጣመር ኃይል መፍጠር መቻላቸውን አብስረዋል፡፡

ላለፉት ከሁለት ሺህ ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ለጽሁፍ አገልግሎት ብቻ ይውል የነበረውን ወረቀት በላዩ ላይ በስሱ በታተመ ማግኒዥዬም ከዓየር እና ውኃ ጋር ተጣምሮ የኃይል ምንጭ መስራት ተችሏል፡፡ ይሄ ደግሞ ከብረት እና ኘላስቲክ የሚሰራውን የማይበሰብስ ቁስ፣ የሚተካ፣ ለአካባቢ ስምሙነቱ ለመጪው ዘመን ተመራጭ ያደርገዋል ነው ያሉት – ተመራማሪዎቹ፡፡

በወረቀት ላይ የተመሠረተው የኃይል ምንጭ ለህሙማን የምርምራ መሣሪያዎች ተላላፊ በሽታዎችን በአነስተኛ ወጪ እና በፍጥነት ለመለየት እንደሚያስችል አረጋግጠዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡

ጥናቱን ካካሄዱት መሪ ተመራማሪዎች አንዱ ሂሮሺ ያቡ ዕፅዋት ከከባቢ ዓየር እና ከዓፈር ውስጥ የሚያገኙትን ውኃ በፀሀይ ብርሃን አማካይነት በኬሚካል ውህደት ለኃይል መሙያ እና ወደ ውጪ ለማስወጣት እንደሚጠቀሙበት በውል መገንዘባቸውን አብራርተዋል፡፡ ይህንኑ ስልት ላቀዱት አዲሱ ለከባቢ ስሙም የኃይል ምንጭ ባትሪ መስሪያነት ሁነኛ ሆኖ እንዳገኙት ነው  የገለጹት፡፡

ስስ የማግኒዥዬም ሽቦዎች የታተሙበት ንድፍን የያዘው ወረቀት ከውኃና ከዓየር ጋር ተዋህዶ ተንቀሣቃሹ የኃይልምንጭ በቀላሉ አካባቢን ሳይበክል ሊወገድ የሚችል ወይም ሊበሰብስ የሚችል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ተለባሹ የኃይል ምንጭ በሚፈለገው ብዛት ተመርቶ ለአገልግሎት ሲበቃ በማንኛውም ቦታ ለመጠቀም ምቹ መሆኑን ነው ያሰመሩበት ተመራማሪዎቹ፡፡

በወረቀት ላይ የሚሰራው የኃይል ምንጭ (ባትሪ) በተመራማሪዎቹ ናሙናው ተሰርቶ አንድ ነጥብ ስምንት  ቮልት ወይም የጤና ምርመራ መሣሪያዎችን ለማንቀሳቀስ በቂ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ተመራማሪዎቹ አብስረዋል። ተመራማሪዎቹ ባትሪው ወይም የኃይል ምንጩ ለቦታ መለያ “ጂፒኤስ ሴንሰር” እንዲሁም  የልብ ምትን ለመለካት አስቻይ መሆኑን  ነው በሙከራ ያረጋገጡት።

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here