የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በአሁን ወቅት የትምህርት ቤቶች ቁጥር ከ47 ሺህ በላይ ተሻግሯል:: የትምህርት ቤቶቹ ገጽታ እና የመምህራን አቅም የተለያየ መሆን፣ የትምህርት ቁሳቁስ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች በእኩል አለመሟላት የትምህርት ዘርፉ ፈተናዎች ናቸው:: በእስካሁን ጉዞው በሀገሪቱ በአጠቃላይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ደረጃን የሚያሟሉት አራት ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ የትምህርት ሥርዓቱ በሚፈለገው ልክ አለማደጉን የሚያረጋግጥ ነው::
በእነዚህ ዓመታት ያለው የትምህርት አሰጣጥ፣ ጥራት እና ተደራሽነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚለው በጥናት የሚለይ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የትምህርት ዘርፉ በጥራትም ሆነ በተደራሽነት ችግር ውስጥ እየገባ መሆኑን የሚያረጋግጡ ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው።
ለአብነት ኢትዮጵያ በተለይ በ2012 ዓ.ም የተከሰተውን ዓለም አቀፍ የኮቪድ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚል ትምህርት ተቋሞቿን ዘግታለች። የበሽታው ስርጭት ረገብ ባለበት ወቅት መደበኛው የመማር ማስተማር ሥራ ቢጀመርም ይዘቶች በአግባቡ በወቅቱ ስለመሸፈን አለመሸፈናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ይህም በአንድም ይሁን በሌላ በተማሪዎች ዕውቀት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል።
የትርምህርት ሥርዓቱ ፈተና ግን በዚህ አላበቃም፤ በ2013 ዓ.ም ከተከሰተው የሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በቀጠሉ ግጭቶች ክፉኛ እየተፈተነ ይገኛል። ግጭቶች አሁንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ አድርገዋል። በትምህርት ላይ ያሉትም ቢሆን ብቁነታቸውን እያረጋገጡ ናቸው ወይ? ለሚለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየተመዘገበ ያለው ዝቅተኛ ውጤት ዋቢ ነው።
በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተፈተነ ያለውን የትምህርት ሥርዓት እንዴት መታደግ ይቻላል? የሚለው ጉዳይ በልዩነት ሊሰመርበት የሚገባ ነው። የትምህርት ጥራትን በሚገባ በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የትምህርት መሰረት ልማትን ከማረጋገጥ እና ግብዓትን ከማሟላት ባለፈ ትልቁ መፍትሄ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት ፖሊሲን መከተል እንደሚገባ ይታመናል::
ትምህርትን በቴክኖሎጂ ታግዘው ለተማሪዎቻቸው ከሚሰጡ የዓለም ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ማሌዢያ፣ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ እና ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ መሆናቸውን ትምህርት ኢንዱስትሪው ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው (monitor.icef.com) ድረ ገጽ አስነብቧል::
“ሀገራት ትምህርትን በቴክኖሎጂ ታግዘው በኦላይን መስጠታቸው የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተጉ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ሲል ሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ በድረ ገጹ አትቷል:: የኦንላይን ትምህርት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ የሚጠፋውን ጊዜ እና ጉልበት በመታደግ ተማሪዎች ለጥናት ሰፊ ጊዜ እንዲኖራቸው ያደርጋል:: ይህም የዕውቀት አድማሳቸውን ለማሳደግ ምቹ መንገድ ነው:: ተማሪዎች ለሚጠይቁት ጥያቄ ፈጣን እና ተገቢ በቂ ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ ከየትኛውም የመማር ማስተማር ስነ ዘዴ ተመራጭ ያደርገዋል::
ተማሪዎች በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ በበየነ መረብ አማካኝነት ተገናኝተው እንዲረዳዱ እና እንዲተጋገዙ ያበረታታል:: ይህም ተማሪዎች ተቀራራቢ ዕውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው::
ሀገራት ትምህርትን በቴክኖሎጂ (ኦላይን) ታግዘው ሲሰጡ የትምህርት ቤቶች ከመኖሪያ ቀዬ ያለው ርቀት የሚያሳስብ አይሆንም:: በተጨማሪም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በሚሄዱበት ወቅት ለምግብ፣ ለመጓጓዣ /ትራንስፖርት/ እና ለሌሎች መሰል አገልግሎቶች የሚወጣውን ወጪ በማስቀረት ለእያንዳንዱ ኅብረተሰብ የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ሆኖም ይጠቀሳል::
በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ትምህርትን በቴክኖሎጂ ታግዞ ተደራሽ ለማድረግ የፋይናንስ አቅርቦት ከፍተኛ ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል ይታመናል:: በአንጻሩ ትምህርት የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁሉ መሰረት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል:: ይህ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዓመታዊ ገቢያቸው ውስጥ ለትምህርት ዘርፉ ብለው የሚመድቡትን በጀት እንዲያሻሽሉ የአፍሪካ ሕብረት 37ኛውን የመሪዎች ጉባዔ ባካሄደበት ወቅት አጽንኦት ሰጥቷል::
የሕብረቱ መሪዎች ለትምህርት ጥራት ትኩረት እንዲሰጥ ሲወተውቱ አህጉሪቱ በቴክኖሎጂ ለታገዘ ለትምህርት ትኩረት ልትሰጥ ይገባል የሚለውን ጉዳይ በቀዳሚ መርህነት ይዘው ነው:: ምክንያቱም በአህጉሪቱ በሰላም እጦት፣ በትምህርት መሰረተ ልማት ተደራሽ አለመሆን፣ በድህነት እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ከ100 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን የመታደጊያው አንዱ አማራጭ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት ሥርዓት መገንባት ሲቻል እንደሆነ ተጠቅሷል::
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራር መምህር እና ባለሙያው ሸጋው ሞላ ሐሳቡን በመደገፍ ያጠናክሩታል:: በተለይ ዓለም ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እየገባች ባለችበት ወቅት በተደጋጋሚ እየተፈተነ ያለውን የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ለማስቀጠል የትምህርት ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው የመፍትሄ ርምጃ መሆኑን ያስረዳሉ::
ትምህርትን በርቀት በቴክኖሎጂ ታግዞ መስጠት በጸጥታ መታወክ የተቋረጠውን መማር ማስተማር ሁሉም ተማሪ ባለበት በማስቀጠል ተማሪዎችን፣ ወላጆችን እና መምህራንን ከሥነ ልቦና ጉዳት ከመታደጉም ባሻገር ዓለም የምትፈልገው ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያግዝም አቶ ሸጋው ጠቁመዋል::
በዕውቀት የበቁ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል:: በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የታገዘ የመማር ማስማር ዘዴ በመንገድ ርቀት እና በትራንስፖርት እጦት ሊቋረጥ የሚችልን ትምህርት ለመታደግ እንደሚረዳም ይታመናል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም