ኢትዮጵያ ከምትከተለው የግብርና መር ፖሊሲ ዋና ዓላማዎች መካከል በምግብ እህል ራስን መቻል፣ የሀገሪቱን የግብርና ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ እና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ማቅረብ ይገኙበታል::
የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እና ለአግሮ ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉ የግብርና ምርቶችን በማቅረብ እና ከውጭ የሚገባውን ለመተካት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እና አጠቃላይ ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማረጋገጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ዘርፍ ነው:: በአሁኑ ወቅትም የሀገራችን ግብርና 80 ከመቶ ለሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ መተዳደሪያ፣ 40 ከመቶ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) አስተዋፅኦ የሚያደርግ እና ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡት ምርቶች ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ዘርፍ ነው::
የአማራ ክልል በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች የአገሪቱን 33 በመቶ ያህሉን የምርት አስተዋጽአ የሚያበረክት መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል:: በመሆኑም የሰብል ልማት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በተደራጀ ሁኔታ ማቅረብ፣ ማሰራጨትና መጠቀም ይገባል::
የክልሉ የግብዓት አቅርቦት፣ ስርጭት እና አጠቃቀም እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም የተጠቃሚውን ፍላጎት በተሟላ ሁኔታ ማርካት እንዳልተቻለ መረጃዎች ያሳያሉ::
ከምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች ውስጥ ደግሞ በዋነኛነት ምርጥ ዘር ተጠቃሽ ነው:: ምርጥ ዘርን በወቅቱ፣ በመጠን፣ በጥራት፣ በዓይነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ማቅረብ ከተቻለ የክልሉን የሰብል ምርታማነት ማሳደግ እንደሚቻል ይታመናል::
ይሁን እንጅ የክልሉን የምርጥ ዘር ተደራሽነት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም በክልሉ ይህን ግብዓት በጥራት፣ በመጠን፣ በወቅቱ እና በዓይነት ማቅረብ ባለመቻሉ የሚጠበቀዉ ምርት እየተገኘ አደለም::
በክልሉ በምርጥ ዘር የሚሸፈነው ማሳ ከ11 በመቶ እንደማይበልጥ ይነገራል:: አብዛኛው ዘር የሚሸፈነው በኢ-መደበኛ የዘር ሥርዓት ነዉ:: የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲጎለብት ከተመሠረቱ ተቋማት መካከል አንዱ ነዉ:: ሰማኝ አስረዴ (ዶ/ር) ደግሞ የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክተር ናቸው::
አራቢ ዘር፣ ቅድመ መሥራች ዘር እና መሥራች ዘር ለዘር አባዥዎች እንደሚያቀርብ ዳይሬክተሩ ለበኩር አስረድተዋል::
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለአርሶ አደሮች የሚሰራጨው የተመሰከረለት ምርጥ ዘር ከ11 በመቶ አይበልጥም:: ከዚህ ውስጥ ደግሞ 97 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የሚሆነውን ምርጥ ዘር የሚሸፍኑት በቆሎ፣ ስንዴ እና ጤፍ ናቸው::
በክልሉ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ለሀገር ውስጥ በክልሉ የሰብል ዘር በሚፈለገው መጠንና ጥራት በማምረት የአርሶ አደሩን ፍላጎት ማሟላት እና የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው በየደረጃው ያሉ ፈጻሚ እና አስፈጻሚ አካላት በጋራ ተቀናጅተውና በየድርሻቸው ሊያከናውኑ የሚገባቸውን ተግባራት ለይተው ሲያከናውኑ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ያብራራሉ:: እንደ እርሳቸው ማብራያ ምርትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን መከተል፣ የባለሙያ ምክረ-ሀሳብ መከተል፣ ማዳበሪያ እና ጸረ-ተባይ ኬሚካል መጠቀም እና ሌሎች ለምርት ዕድገት የሚረዱ ግብአቶችን መጠቀም ግድ ይላል::
የግብርና ምርምር ዋና ተግባሩም የግብርና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ፍጆታን ከማሟላት ባሻገር ለግብርና ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትን እና የውጭ የምንዛሬ አቅምን ማሳደግ የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችን ማፍለቅ፣ ማላመድ፣ መጠበቅ፣ ማስተዋወቅ እና መነሻ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ነው ብለዋል::
በ2016 ዓ.ም ከሦስት ሺህ ሀምሳ በላይ ኩንታል አራቢ፣ ቅድም መሥራች እና መሥራች በማዕከላት ማሳ እና በሌሎች ኮንትራት በወሰደባቸው ማሳዎች እንዳመረተም አስታውቀዋል::
የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዋናነት መነሻ ዘር ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፤ ለስርጭትም ያዘጋጃል:: ምርጥ ዘር መጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል::
ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት በተለይ የድንች ምርጥ ዘር መጠቀም ምርቱን 50 በመቶ ከፍ እንዲል ያደርጋል:: በተቃራኒው ደግመ ምንም እንኳን በቂ የአፈር ማዳበሪያ፣ የተሻለ አስተራርስ እና የማሳ አዘገጃጀት ዘዴዎችን ብንከተልም ምርጥ ዘር መጠቀም ካልተቻለ 50 በመቶ የምርት ቅናሽ እንደሚያስከትል አክለዋል:: ምርጥ ዘር የተለያዩ በሽታን የመቋቋም ችሎታ ያለው፣ ምርትን የሚጨምር፣ ፈጥኖ የሚደርስ እንዲሁም ለሜካናይዜሽን እርሻ ምቹ እንደሆነም ያብራራሉ:: በስንዴ፣ በበቆሎ እና በባቄላ ምርጥ ዘር ላይ የአርሶ አደሩ የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል::
ይህን ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ በቂ መሬት እና ምርጥ ዘር ማምረት ይኖርብናል ብለዋል::
በቂ መሬት ባለመኖሩ በክልሉ የቢራ ገብስ መነሻ ዘር ማምርት እንዳልተቻለ የሚናገሩት ዳይሬክሩ በአኩሪ አተር፣ በሰሊጥ እና በጤፍ ዘር አማራ ክልል እየሠራ ያለው ተግባር አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል::
የምርምር ተቋሙ ከ21 በላይ ሰብሎች እያባዛ ይገኛል:: ከ71 በላይ አዳዲስ የአትክልት ዝርያዎችን ከውጭ ለማስመጣት ቅድመ ዝግጅት አድርጓል:: ድርቅን መቋቋም የሚችሉ እና በአጭር ጊዜ መድረስ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችንም እያባዛ ይገኛል:: በሠላም መደፍረስ ምክንያት የተሻሻለ ዘር ለማምረት ጫና ማሳደሩንም ተናግረዋል::
የክልሉ መንግሥት የመሬት አቅርቦት ችግርን በፍጥነት ካልቀረፈ ምርጥ ዘር ለማምርት ፈተና እንደሚሆን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የዘር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ሥራዎችን ለማከናወን የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ለበኩር ተናግረዋል::
በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦት እና ስርጭት ችግር በመኖሩ ክፍተቱን ለመሙላት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን እያመረተ የሚገኘው ደግሞ የአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ነው:: ሆኖም ግን የሚጠበቅበትን ያህል መሥራት አለመቻሉን የኢንተርፕራይዙ የዘር ማምረት መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሻው ወርቅነህ ለበኩር ተናግረዋል:: በተለያዩ ችግሮች አሁንም የምርጥ ዘር እጥረቶች መኖራቸውን አክለዋል::
ኢንተርፕራይዙ 10 ዋና ዋና የምግብ ሰብሎችን ዘር እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: በዚህ ዓመት 77 ሺህ 460 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን እስካሁን 66 ሺህ 630 ኩንታል (86)በመቶ የሚሆነው ዘር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል:: ከተሰበሰበው ዘር 31 ሺህ 734 ኩንታል ዘር ተዘጋጅቶ (ተበጥሮ) ለተጠቃሚው በመሰራጨት ላይ መሆኑን አክለዋል:: በተለይ ቀድመው ለሚዘሩ በቆሎ እና መሰል ሰብሎች አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል:: በቀጣይም በሌሎች ምርጥ ዘሮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል::
ኢንተርፕራይዙ ምርጥ ዘር ያመርታል፣ ያበጥራል እንዲሁም አሽጎ ለተጠቃሚው አርሶ አደር እንዲደርስ ያደርጋል:: ከቴክኖሎጅ ጋር በተያያዘ ተጓዳኝ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል:: የተመረተውን ዘር አበጥሮ በፍጥነት ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ ኢንተርፕራይዙ ሙሉ ጊዜውን እየተጠቀመ መሆኑን አስረድተዋል::
የዘር ብዜት ሥራ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል ያሉት አቶ እምሻው ከአርሶ አደሩ እና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
ምርጥ ዘር መጠቀም እንደ ብርዕ አገዳ፣ ጥራጥሬ እና የቅባት ሰብሎች እስከ 30 በመቶ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ እስከ 50 በመቶ የምርት ጭማሬ እንደሚያሳይ ያብራራሉ:: ይህን ውጤት ለማግኜትም የአፈር ማደበሪያ፣ የተሻሻሉ የግብርና ሥራዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደተጠበቀ መሆን አለበት ብለዋል፤ ምርጥ ዘር ላይ የአርሶ አደሩ ፍላጎት እየጨመረ ቢሆንም በጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች አዳዲስ ለሚወጡ ዝርያዎች የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን አመላክተዋል::
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም