የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው

0
273

በምርት ዘመኑ ከ2015/16 የምርት ዘመን በ24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፤ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል በምርት ዘመኑ ክልሉ ለማግኘት ያቀደውን እቅድ ለማሳካት አቅም ይፈጥራል ተብሏል።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የቢሮው ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ከምርት ጭማሪ ባሻገር የምርታማነት እድገት ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን ከአምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በማልማት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ አየተሠራ ይገኛል። ባለፈው የምርት ዘመን ከተገኘው ምርት በ24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። አማካይ ምርታማነቱን በሄክታር ወደ 32 ኩንታል ለማድረስ እየተሠራም ነው ብለዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በምርት ዘመኑ የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጅዎችን እና ግብዓትን በሙሉ ፓኬጅ ለመጠቀም እንዲሁም ለምርታማነት እድገት ማነቆ በሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጓል። ግብርናው የሉዓላዊነት መገለጫ እና ሰላምን ማረጋገጫ መንገድ መሆኑንም አንስተዋል:: በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች እና በየትኛውም ተቋም ላይ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ሥራ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። አርሶ አደሩም የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ ተቀብሎ እንዲተገብር አሳስበዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ቃልኪዳን ሺፈራው በምርት ዘመኑ የምግብ ፍላጎትን ማሳካት፣ በክልሉ እየተስፋፉ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ በቂ ግብዓት ማሟላት እና የኤክስፖርት (ለውጪ ገበያ የሚላኩ) ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ለምርት መቀነስ ምክንያት የሆኑ የሰብል ተባይ እና በሽታዎች መከላከል ላይ እንደሚሠራ ነው ያስገነዘቡት።

የአፈር አሲዳማነትን ማከም፣ የጥቁር አፈር ፓኬጅን ተግባራዊ ማድረግ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀምን የማሻሻል ሥራም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ ምህረቱ ተስፋየ በ2016/17 የምርት ዘመን በቂ ግብዓት እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፤ ምርታማነትን ለመጨመር የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦችን (የአፈር ለምነትን ማሻሻል፣ የምርጥ ዘር ብዜት፣ …) ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። አሁን ላይ እንደ በቆሎ የመሳሰሉ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የግብዓት ሥርጭት መጀመሩንም ገልጸዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ በሪሁን እውነቱ እንደገለጹት በ2015/16 የምርት ዘመን በነበረው የማዳበሪያ እጥረት፣ የተለያዩ ተባዮች እና በሽታዎች ምክንያት የታቀደውን ምርት ማሳካት አልተቻለም። በ2016/17 የምርት ዘመን ግን ምርታማነትን ለማሻሻል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ቀድሞ ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀመጡ ፓኬጆችን እና ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here