የገንዘብ ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ የእርዳታ ስምምነት ተፈራረሙ

0
340

የገንዘብ ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ የአንድ ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ተቋማቱ የተፈራረሙት ገንዘብም ዘላቂ ልማትን እና አጠቃላይ እድገትን ለማምጣት ለታቀዱ ስድስት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ነው ተብሏል፡፡

የገንዘብ ሚኔስቴር ከሰሞኑ እንደገለጸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የማይበገር የምግብ ገበያና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የገጠር መንገድ አስተዳደር ተቋማዊ አቅምን ለማጠናከር የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያን አዳፕቲቭ ሴፍቲኔት ፕሮጀክትን ለማጠናከር የ200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚደረግ ነው የተጠቆመው፡፡

በከተማ የሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ማኅበረሰቦች ገቢ ለማሳደግ እና የተቸገሩ የከተማ ወጣቶችን የሥራ ገበያ ለማጠናከር ደግሞ የ82 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚገረግ ተገልጧል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ለሚገኙ የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦችን ኑሮ እና የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ የ340 ሚሊዮን ዶላር ብድር ይሠጣል ተብሏል።

ለኃይል ሴክተር ማሻሻያ ኢንቨስትመንት ደግሞ 522 ነጥብ 63 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚደረግ እና በአዲስ አበባ እና በተመረጡ ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች የውኃ እና ንፅህና አጠባበቅ ውጤታማነትን ለማሻሻል የ275 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ ይደረጋል።

ስምምነቶቹ የተፈረሙት በኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን በኩል ነው።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here