ቀውሱ ሌላ ቀውስን እየፈጠረ፣ የአንድ ሀገር ዜጎች ሟች እና ገዳይ ሆነው፣ የሀሳብ ፖለቲካ በሩ ተከርችሞ የነፍጥ ፖለቲካ ገንኖ ሰላምን እያሳደዳት ይገኛል። ከሰሜኑ ጦርነት ማብቃት በኋላም በአማራ ክልል ሌላ ግጭት አገርሽቶ ክልሉ ሰላም ርቆታል፡፡
ይህ በነፍጥ የታገዘ ግጭት ምንም አይነት ፖለቲካዊ እልባት ሳያገኝ ስምንት ወራትን ዘልቋል። ሰላምን በነፍጥ ለማረጋገጥ የሚመስል ዘመቻው አሁንም ቀጥሏል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ መኸሩ እየገባ ነው። መኸሩ የእርሻ እና የአዝመራ ወቅት ነው። “አንድ ሰኔ የነቀለውን ሰባት ሰኔ አይመልሰውም” እንደሚባለው። ስለሆነም ከአሁኑ ግብዓት እንዲቀርብላቸው አርሶ አደሮች ጥሪ እያቀረቡ ነው።
አሁንም ገና የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና መሰል የግብዓት አቅርቦቶች በበቂ ሁኔታ አልቀረቡም። በመሆኑም ገበሬው የሚፈልገው ግብዓት በወቅቱ ይደርስ ዘንድ ሰላም እጅጉን አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
ገዝቶ ለማጓጓዝ፣ ወደ አርሶ አደሩ መንደር ለማድረስ፣ የባለሙያ ሐሳብ ለመቀበል ነፃ እንቅስቃሴ እና ለባለሙያዎች የሰላም ዋስትና ያስፈልጋል።
በመሆኑም ለሰው ሕይዎት እና ለልማት ሥራዎች ሲባል ሰላምን መፈለግ ግድ ይላል። ሰላም ደግሞ በአንድ ወገን አሸናፊነት ሳይሆን ሁሉንም ባካተተ መንገድ በሁሉም ወገን ውይይት የሚረጋገጥ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ዛሬም እንደ ትናንቱ አርሶ አደሩ ወደ እርሻው፣ ነጋዴው ወደ ገበያው፣ ተማሪው ወደ ትምህርት ቤቱ እንዲሄድ የሰላም ንግግሮች ሳይረፍድ ቢደረጉ ጥሩ ነው። ሁሌ የሚሰሙ የደመሰስናቸው፣ የመታናቸው፣ የበተንናቸው አይነት መግለጫዎች ፉክክርን እንጂ ምክክርን፣ መራራቅን እንጂ መቀራረብን ስለማያመጡ ነገሮችን ቆም ብሎ በሰከነ መንፈስ ማጤንና መወያየት መመረጥ አለበት።
ምንጊዜም ቢሆን ሰላም የሚመጣው በፍትሐዊነት፣ በእውነት እና በመርህ ሲቆም በመሆኑ ለጋራ ንግግር እንዲሁም ሰላም መስፈን በጋራ መቆም ያስፈልጋል። እስከ ዛሬም እንዳስተዋልነው የሴራ ትንታኔ፣ የመገዳደል ዜና፣ የመፈራረጅ ወሬ ሕይዎትን ለማዳንም ሆነ ለልማት የሚሆን አስተዋፅኦ የለውም።
ስለዚህ ለሰላም በመሥራት ግብርናው የሚጠይቀውን ግብአት በተቀላጠፈ መልኩ በማቅረብ፣ የግብርና ሥራውንም በፍጥነት በተባበረ ክንድ በመከወን መሬቶች ፆም እንዳያድሩ ከማድረግ በዘለለ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ረሃብን መመከት ይቻላል። ነፍጥ ለማንሳት ምክንያት ለሆኑ ችግሮች ቁጭ ብሎ በጋራ መፍትሄ መፈለግ፣ ሰላምን ማስፈን እንዲሁም ረሃብን ለማሸነፍ በጋራ በመጣር እንጂ በተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳዎች ምክንያት በነፍጥ ለመሸናነፍ መሮጥ ለጋራ ውድቀት እንደሚዳርግ መረዳት ያስፈልጋል። በጦርነት ድህነትን እንዲሁም ርሀብን እንጂ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደማይቻልም ማጤን ግድ ይላል፡፡ ለችግሮች በጋራ መፍትሄ መፈለግ፣ በጋራ ሠርቶ በጋራ ረሀብን ማሸነፍ ካልተቻለ ህልውናን ማረጋገጥ አይቻልም። በመሆኑም የሰው ልጆች ሀሉ የጋራ ጠላት የሆነውን ረሃብን ለማሸነፍ ሰላምን ማስፈን፣ ለጋራ እድገት በጋራ መነሳት ያስፈልጋል።
(የሺሃሳብ አበራ)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም