አሸናፊ ለመሆን

0
194

በቀደሙት ጊዜያት በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያውያን የነበራቸው ጠንካራ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና እና ወኔ ሌሎች በርካታ ስፖርተኞች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆኗል። ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉት አትሌቶች በየውድድሩ የነበራቸው ከፍ ያለ የማሸነፍ ፍላጎት የሚደነቅ እንደ ነበር በብዙ ባለሙያዎች ተደጋግሞ ይነሳል። እነዚህ የተጠቀሱት  ኢትዮጵያውያን ጀግና   አትሌቶች ጽኑ የማሸነፍ ፍላጎት እና ጠንካራ ሥነ ልቦናን የተላበሱ ስለነበሩ እምቅ ችሎታቸውን አውጥተው ለመጠቀም አልተቸገሩም።

በስፖርቱ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን የአሰልጣኞች እና የሰልጣኞች የማሸነፍ ፍላጎት በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ጠንካራ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ስፖርተኞች እና ባለሙያዎች ማኅበራዊ መስተጋብራቸው እንዲሻሻል በቡድን እና በግል ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከመልካም ውጤት ጀርባ ጠንካራ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና መኖሩን የተሠሩ ጥናቶችን ጠቅሶ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስነብባል። በአንጻሩ ደግሞ ደካማ ውጤት የሚያስመዘግቡ በርካታ ስፖርተኞች ዝቅተኛ የማሸነፍ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን መረጃው ጠቅሷል። በእርግጥም “እንደሚያሸንፉ እምነት የሌላቸው ስፖርተኞች እንዴት ሊያሸንፉ ይችላሉ”? በማለት ጭምር መረጃው ያክላል።

ለመሆኑ በስፖርቱ ዘርፍ ጠንካራ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና እንዴት ይገለጻል?

በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ መምህርነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ሰለሞን አሳየ በዚህ ጉዳይ ላይ ከአሚኮ በኲር የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ስፖርተኞች ለተሰለፉበት ዓላማ ወይም ተግባር ያላቸው ትጋት፣ ቁርጠኝነት፣ ስጋት እና የመስዋዕትነት ልክ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ሊባል እንደሚችል ይናገራሉ።

የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ለሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ትልቁ የማሸነፊያ ምስጢር ወይም መሳሪያ ቢሆንም በአገራችን ግን በግንዛቤ  እጥረት ምክንያት ብዙ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም። አሸናፊነት በውጤት ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን ከብቃት እና ስፖርተኞች ወይም ቡድኖቹ እየተጓዙበት ባለው መንገድም ሊገለጽ እንደሚችል የስፖርት ባለሙያው አቶ ሰለሞን አሳየ ተናግረዋል።

የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ምንጩ ከየት ነው?

የግል ተነሳሽነት እና ትጋት አንደኛው ምንጭ መሆኑን ባለሙያው ይጠቁማሉ። ለአብነት ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያለው የአሸናፊነት ሥነ ልቦና በስፖርተኞቹ ዘንድ እንደ ምሳሌ ተነስቷል።  የቀደመ መልካም ታሪክም ሌላኛው ምንጭ ነው ብለዋል ባለሙያው። በሀገራችን በአትሌቲክስ ስፖርት ማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር፣  ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ መሰረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና አልማዝ አያናን የመሳሰሉ ዕንቁ  አትሌቶቻችን በዘመናት የማይደበዝዝ ታሪክ የፃፉት የታላላቆቻቸውን አኩሪ ገድል በመመልከት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። የቤተሰብ አስተዳደግ ፣ የቡድን አጋር፣ ደጋፊዎች እና የክለብ አመራሮች ለጠንካራ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና መሠረቶች እንደሆኑ ጭምር ነው የተገለጸው።

የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ከስፖርተኞች ማኅበራዊ ክስተቶች ጋርም  መስተጋብር አለው። ከስፖርተኞች ጋር በቅርበት የሚኖሩ ሰዎች ፣ ቤተሰብ ፣ ልጅ ፣ አሰልጣኝ፣ ባለሙያ፣ ከቡድን አጋር እና ከመሳሰሉት ስፖርተኞች  የሚኖራቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ከግለሰቦቹ ወይም ከቡድኑ የማሸነፍ ፍላጎት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ይኖረዋል። “በቅርቡ የባሕር ዳር ከተማውን አማካኝ አለልኝ አዘነ ህልፈተ ሕይወት መስማታችን  ይታወሳል።

የአለልኝ ህልፈተ ሕይወት በቡድኑ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ እንደሚሆን ይገመታል። ምክንያቱ ደግሞ በብዙ ሲጠበቅ የነበረው የእግር ኳስ ኮከብ በተሰማው መንገድ ሕይወቱ ማለፉ፣  ለሕይወት ትርጉም የሚያጡ ስፖርተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ በቡድኑ ተነሳሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።

 የስፖርተኞቹ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና በምን ምክንያት ሊቀንስ ይችላል?

ስፖርተኞች፣ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኖች በተደጋጋሚ የውጤት ማሽቆልቆል ሲገጥማቸው ወይም ያሰቡት ነገር ሳይሳካ  እና በትክክል ተግባራዊ ሳይሆን ሲቀር ችግሩ ይፈጠራል። በግለሰብ ደረጃ በግል ሕይወታቸው ላይ ችግር ሲፈጠር፣ በክለብ ውስጥ የቡድኑ መንፈስ ሲረበሽ፣ በወቅታዊ አቋም ደካማ መሆን፣ ትችት እና ያፈነገጠ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የአሸናፊነት ሥነ ልቦናቸውን ዝቅ ከሚያደርጉት ውስጥ ተጠቃሾች መሆናቸውን ባለሙያው ያስረዳሉ።

በደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ደስተኛ አለመሆን፣ አሰልጣኞች ስፖርተኞችን የሚይዙበት መንገድ ጥሩ አለመሆን፣ የስፖርተኞች ከልምምድ በፊት እና በኋላ ያላቸው የቀን ውሎ እና ስሜታቸውን  አለመቆጣጠርም ሌላኛው ለአሸናፊነት ፍላጎት ማጣት ምክንያት ይሆናል። የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን ለማስቀጠል ወይም ባህል ለማድረግ አወንታዊ አስተሳሰብን ማራመድ ያስፈልጋል። ሁሌም ትችትን ወይም ሙገሳን አለማስተናገድም በራስ መተማመንን ከፍ አድርጎ አሸናፊ ለመሆን እንደሚረዳ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ስፖርተኞች ለሥነ ልቦና ያላቸው ግንዛቤ እና የሚሰለጥኑበት መንገድ ትክክል አለመሆን የአሸናፊነት ሥነ ልቦናቸውን ዝቅ ያደርጋል። እንደ ባለሙያው  አቶ ሰለሞን ማብራሪያ ክለቦች ወይም ብሄራዊ ቡድኖች የቀደመውን ገናና ስም እና ታሪክ ለማስቀጠል የሚያስችል ቁመና ላይ አለመገኘት የማሸነፍ ጉጉታቸውን እና ፍላጎታቸውን በእጅጉ ይቀንሰዋል።

ኢትዮጵያ በቀደሙት ዓመታት እና  አሁን ላይ በመካከለኛ ርቀት ያላትን ታሪክ ስናነፃጽር የተራራቀ መሆኑ የአትሌቶችን ወኔ እና ፍላጎት ይሰልባል። ተተኪዎችም እንዳይበረታቱ ያደርጋል። ተመሳሳይ ተጨማሪ ምሳሌ ስንጠቅስ ስኮትላንዳዊው የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ክለቡ የማሸነፍ ፍላጎቱ ጠፍቶ እየተቸገረ ይገኛል። በፈርጉሰን ዘመን የነበረው  የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ተሸርሽሮ አሁን እስካለው ኤሪክ ቴን ሀግ ዘመን ደርሷል።

ስፖርተኞች ሙያቸውን  የሚፈታተን የሥነ ልቦና ችግር እንኳ ቢገጥማቸው ሁሉም ነገር እንዳበቃለት ዓይነት ስሜት እንዳይሰማቸው ክትትል ማድረግ የአሰልጣኞች እና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት ነው። ሙሉ ትኩረታቸውን በስፖርቱ ላይ እንዲያደርጉ በግል ማማከር እና እገዛ ማድረግ አለባቸው ጭምር ነው የተባለው።

ጠንካራ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና በምን መንገድ ይዳብራል?

ስፖርት ሥነ ልቦና የስፖርተኞችን እና የባለሙያዎችን ባህሪ እና አስተሳሰብ የሚያጠና በመሆኑ የሥነ ልቦና ደረጃቸው እንዲስተካከል ያግዛቸዋል። የአሸናፊነት ሥነ ልቦና የሚመጣው በንግግር ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ መሆኑን የተናገሩት የስፖርት ባለሙያው አቶ ሰለሞን አሳየ ብዙዎች ለዚህ ጽንሰ ሀሳብ ያላቸው አረዳድ እና አመለካከት መቀየር አለበት ይላሉ።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት ከሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ኬኒያ እና ዩጋንዳ ጋር ከፍተኛ ፉክክር የምታደርግ ሀገር ናት። ይህ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት ከታች ለሚመጡ ተተኪ አትሌቶች የማሽነፍ ጉጉታቸው እና ፍላጎታቸው እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። “ሁሌም ታሪክ ያለው ክለብ ወይም ሀገር በተሠሩ ገድሎች ኩራት ይሰማዋል።  ደማቅ ታሪኩን ለማስቀጠል እና ለማሻሻል በትጋት እና በትልቅ ተነሳሽነት ይሠራል። ቀድመው የተሠሩት ታሪኮች የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ”ይላሉ አቶ ሰለሞን።

ለአብነት በአገራችን የእግር ኳስ ስፖርት ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀዳሚው ባለ ታሪክ ክለብ እንደሆነ ይታወቃል። ፈረሰኞቹ የአሸናፊነት ሥነ ልቦናቸው ከፍ ተደርጎ ከተገነቡት ውስጥም በቀዳሚነት ይቀመጣሉ። ክለቡ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የመጀመሪያ ተግባሩ አዳዲስ ተጫዋቾችን በሥነ ልቦናው  ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በሚመጥን ደረጃ ማዘጋጀት ነው። የክለቡን ታሪክ በመንገር እና ስለ ክለቡ ምንነት ማሳወቅ የክለቡ አመራሮች ቀዳሚ ተግባር መሆኑም ይነገራል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎቹ ሳይቀሩ በድጋፍ መዝሙራቸው የክለባቸውን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና በዚህ መልኩ ይበልጥ ያቀጣጥሉታል፤

እናሸንፋለን

በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን

አርማችን ነው መለያችን ነው

ሳንጅዬ ኩራታችን ነው  የሚል መዝሙር በማሰማት ክለባቸውን ያነቃቃሉ፡፡

ሊሳካ የሚችል ግብ ወይም አላማ ማስቀመጥ የስፖርተኞችን የማሽነፍ ጉጉት እና ፍላጎት ለማሳደግ ቀዳሚው ተግባር መሆን ይኖርበታል የባለሙያው አስተያየት ነው።

ስፖርተኞች የቀን ውሏቸው በስርዓት እና ደንብ እንዲመራ ማድረግም ያስፈልጋል። አሰልጣኞች  ቡድናቸው በየትኛውም ችግር ውስጥ ቢወድቅ ለሰልጣኞች የሚያስተላልፉት መልዕክት ተስፋን እና ብርሃንን የሚፈነጥቅ መሆን አለበት የአቶ ሰለሞን ምክረ ሀሳብ ነው፡፡ የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን ለመገንባት በዙሪያው ምን አለ? ባለሙያዎቹ እነማን ናቸው? ምን እየሠሩ ነው? እንዴት ይሠራሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች በጥልቀት መመርመርም ያስፈልጋል ብለዋል የዘርፉ ባለሙያ።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here