“ለመሥራት መማር ወይም ገንዘብ ማግኘትም ብቻውን በቂ አይደለም”

0
241

ከወ/ሮ ዝናሽ እንየው ጋር  በባሕር ዳር ከተማ ዋርካው የገበያ ማዕከል አካባቢ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ በቦታው ስንገናኝ  ወ/ሮ ዝናሽ እንየው  በአንድ እጇ በቅርጫት   ሶፍት፣ በትናንሽ እቃ የተሞላ ዳጣ፣ ስቲኪኒ እና የጆሮ ማፅጃ እንዲሁም በሌላኛው እጇ ደግሞ በፌስታል ትናንሽ ሶፍት፣ የሞባይል ካርድ፣ የምሳ እቃ ይዛለች፡፡ በአንገቷ ደግሞ በላስቲክ የታሸገ /ላምኔት የተደረገ/ “ዳግም፣ ዝናሽ እና ጓደኞቻቸው የህብረት ሥራ ተቋራጭ” የሚል ማስታወቂያ አንጠልጥላ  ነበር፡፡

ወ/ሮ ዝናሽ  ትውልዷ በሰሜን ወሎ ዞን  ላሊበላ ከተማ ነው፡፡ ባለታሪካችን የመጀመሪያ እና  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተማረችው ከአጎቷ ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርቷን ደግሞ  በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሰርቬይንግ (ቅየሳ) የመጀመሪያ ዲግሪዋን  በ2005 ዓ.ም  ተመርቃለች፡፡

ወ/ሮ ዝናሽ በባሕር ዳር እና  አካባቢዋ ባጠናችው የሙያ ዘርፍ  በመንገድ ሥራ  ተቀጠረች፡፡  በገባችበት ድርጅት በባለሙያነት ለአራት ዓመታት ካገለገለች በኋላ የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ  በሌላ መንገድ ሥራ ድርጅት ተቀረች፡፡    ለአምስት ዓመታትም ሠርታለች፡፡

“ብዙ ጊዜ የግንባታ ሥራ ክረምት  ስለማይሠራ ደመወዝ የለንም፡፡ እናም  ምን ሰርቼ ቤቴን ላግዝ? ገቢዬን እንዴት ላሳድግ?” ብላ ታስብ ነበር፡፡ በ2013 ዓ.ም የክረምት ወቅት ግን ሀሳቧን ወደ ተግባር ለመለወጥ ዳር ደረሰች፤ የሥራው ዘርፍም አሁን ላይ የተሰማራችበት  የተለያዩ ቁሳቁስን እየተዘዋወሩ መሸጥ ነው፡፡

ወ/ሮ ዝናሽ ሥራውን የጀመረችው በባሕር ዳር ከተማ አዝዋ ሆቴል  ፊት ለፊት በ500 ብር በገዛችው የአፍ እና አፍንጫ ጭምብል/ማስክ/ እና ትናንሽ ሶፍት በመሸጥ ነበር፡፡ የደንበኞቿን ፍላጎት በመገንዘብ  ጎን ለጎን ደግሞ ቅቅል በቆሎ  ጨመረች፡፡

ባለታሪካችን እንደምትለው ክረምት አልፎ ወደ መደበኛ ሥራዋ ስትመለስ የጀመረችውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ሳታቋርጥ በረፍት ቀኗ ቅዳሜ እና እሁድ ቀጠለች፡፡ በዚህም በወርሀዊ ደመወዝ ብቻ  ቤተሰቦቿን ለመምራት ትቸገር የነበረችው ወ/ሮ ዝናሽ በክረምት ወቅት የጀመረችውን ሥራ በመቀጠል  ኑሮዋን በመጠኑም ቢሆን አቀለለች፡፡

በበጋ በተቀጠረችበት ድርጅት፤ በክረምት ደግሞ  ጥቃቅን ነገሮችን እየተዘዋወረች በመሸጥ በምታገኘው ገቢ  ቤተሰቦቿን ታስተዳድር የነበረችው ወ/ሮ ዝናሺ፤   “እንኳን ዘንቦብሽ እንዳውም ጤዛ ነሽ” እንደሚባለው በቅጥር ስትሠራበት ነበረው የጭስ ዓባይ ፕሮጀክት  ሥራውን አጠናቆ    ወደ ደብረ ማርቆስ አካባቢ ተዛወረ፡፡ እርሷም ወደዛው  እንድትሠራ ተነገራት፡፡

በወቅቱ ወ/ሮ ዝናሽ ባለቤቷ ለትምህርት ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ  ከጎኗ ባለመኖሩ    ቤተሰቧን ጥሎ ላለመሄድ በመወሰን በክረምት ወቅት የጀመረችውን የገቢ ማስገኛ ሙሉ ቀን አድርጋ ለመቀጠል ወሰነች፡፡

ባለታሪካችን በሥራዋ የምታገኘው ገቢ  ደስ ቢያሰኛትም አንዳንድ ሰዎች “ተመርቀሽ ይሄን ሥራ ለምን ትሠሪያለሽ? ሻይ ቡና ወይም ሱቅ ተከራይተሽ አትሠሪም?” ቢሏትም  ጆሮ ባለመስጠት ሥራዋን ቀጠለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ሲያዩዋት የማፈር ሁኔታ ይሰማት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

በሂደት ግን መሥራት የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ተግባር አለመሆኑን በመረዳት  ተዘዋውሮ መሥራትን ከእሁድ ውጭ የሙሉ ቀን ሥራዋ አድርጋ  ቀጠለች፡፡   “አይዞሽ!” የሚሏት ሰዎችም  ሲጨምሩ የበለጠ ተበረታታች፡፡ “በየቦታው እየተዘዋወሩ መሥራት ደግሞ ገቢ ከማግኘት ባለፈ አዲስ የሥራ አማራጮችን የማየት፣ ከሰዎች ጋር የመግባባት…እድል ፈጥሮልኛል” ስትልም ነግራናለች፡፡

ወ/ሮ ዝናሽ  ዘወትር በጠዋት ለልጆቿ አስፈላጊውን ሁሉ ካደረገችላቸው በኋላ ወደ ሥራዋ ትሄዳለች፡፡ ቀን ላይ ግን በየቦታው ሰዎች የማያገኙዋቸውን የጆሮ ማጽጃ፣ ስቲክኒ፣ ሶፍት፣ የሞባይል ካርድ…በደረቷ እና በእጆቿ አንጠልጥላ  ሰዎች በብዛት በሚንቀሳቀሱባቸው ዋና ዋና መንገዶች፣ በሆቴሎች…እየተዘዋወረች ስትሸጥ ውላ ማታ አንድ ሰዓት ቤቷ እንደምትገባ ነግራናለች፡፡  እሁድ ቀን ደግሞ ለልጆቿ የምትሰጠው ጊዜ ነው፡፡

በ500 ብር የተጀመረው ሥራ ቤተሰቦቿን በአግባቡ እንድታስተዳድር፣ የሥራን ክቡርነት እንድትገነዘብ እና ሌሎች የሥራ አማራጮችን እንድታስብ አስችሏታል፡፡ “ይሄንን ሥራ ብተወው መንገድ አካባቢ የተጠባበሱ ምግቦች (ፋስት ፉድ) ለመሸጥ አሊያም አሁን እየሰለጠንሁበት ያለውን የወንዶች ውበት መጠበቂያ /ፀጉር ቤት/ ለመክፈት አስቤያለሁ” ስትል ተናግራለች፡፡

አሁን ላይ እየተዘዋወረች የምትሠራውም ቢሆን በሰዎች ዘንድ ስለተለመደ እና በርካታ ደንበኞችንም ስላፈራች  ብዙም እንደማትቸገር የምትናገረው ወ/ሮ ዝናሺ  የምትገዛበት ወረት ካለቀባት እንኳ በዱቤ አምጥታ ሸጣ መመለስ እንደምትችልም ገልጻልናለች፡፡

ምንም እንኳን ቀኑን ሙሉ መዞር አድካሚ ቢሆንም ተቀጥራ ታገኝ ከነበረው ገቢ ያልተናነሰ እንደምታገኝ እና እቃዎቹ በቀላል ዋጋ ስለሚሸጡ የገበያ ችግር እንደሌለም ተናግራለች፡፡ ወ/ሮ ዝናሽ እንደምትናገረው በተለይ ደግሞ ፆም ባልሆነ ጊዜ በስጋ መሸጫ አካባቢዎች የስጋ ቁርጥ ማባያ ዳጣ እና ስቲኪኒ ያለው ገበያ ጥሩ ነው፡፡

“ሥራው አውቀው ካልተውት ረፍት የለውም” የምትለው ወ/ሮ ዝናሽ ባለቤቷ “ራስሽን አታድክሚ ረፍት አድርጊ “ ቢላትም  ባመነችበት ሁኔታ መሥራቷ እንደሚያበረታታ ትናገራለች፡፡ “ሥራ  ለመሥራት መማር ወይም ገንዘብ ማግኘት ብቻውን በቂ  አይደለም ፤ ይሄንን ሥራ ብሠራ  ሰዎች ምን ሊሉኝ ይችላሉ ? የሚል ይሉኝታ ካለም ደግሞ  አንድም ሥራ አይሠራምና ውስጣዊ ስሜትን አዳምጦ በመወሰን ሰዎችን ከማስቸገር ይልቅ ለመለወጥ የሚያስችለውን ቀላል ነገር ሁሉ መሞከር ተገቢ ነው፡፡ ሥራ ከጀመሩ ደግሞ እየተማረሩ ሳይሆን በሚሠሩት ነገር ደስተኛ መሆን  ይገባል” ስትል ከእርሷ ተሞክሮ ሌሎች እንዲማሩ መልእክቷን አስተላልፋለች፡፡

በአንድ ወቅት ምሽት ላይ ወደ ቤቷ ለመሄድ እየተዘጋጀች ባለበት ወቅት ሸቀጣ ሸቀጧን መሬት ላይ እንዳስቀመጠችው ከመቅፅበት በሚባል ሁኔታ እንደተሰረቀባት ታስታውሳለች፡፡  ይሁን እንጅ በተፈጠረው ችግር ብትናደድም  ወዲያው ረስታ  ወደ ሥራዋ መመለሷንም ነው የምትናገረው፡፡ ወደፊት በተመረቀችበት የሙያ ዘርፍ  ከጓደኞቿ ጋር  ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ እና የግሏ  የሆነውን ሱቅ በደረቴ ሥራዋን አሳድጋ  ለመሥራት አስባለች፡፡

ወ/ሮ ዝናሽ “ዲግሪ አለኝ ወይም ለሥራ መነሻ በቂ ገንዘብ የለኝም “ ሳትል ዝቅ ብላ በመሥራት ቤቷን መምራት ችላለች፡፡  ሥራ የለም ብሎ አልባሌ ቦታ ከመዋል ሥራን ሳይመርጡ መሥራት እንደሚያስከብር፣ ለነገ ስንቅ ለመያዝ፣ የሥራ ተነሳሽነት ለመፍጠር…እንደሚያግዝ ግንዛቤ ይፈጥራልና “ልብ ያለው ልብ ይበል” መልእክታችን ነው፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here