ብሔራዊ ፓርኩ ከመዲናዋ አዲስ አበባ በስተምዕራብ 850 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጋምቤላ ክልል ይገኛል፡፡ ፓርኩ በ1973 ዓ.ም በቀጣናው የሚገኙ የዱር እንስሳት እና መኖሪያቸውን መጠበቅን መሠረት አድርጐ 50 ሺህ 600 ሄክታር ስፋት ይዞ ተከልሏል፡፡
ፓርኩ በባሮ እና ጊሎ ወንዞች መካከል መከለሉ በዙሪያው ላለው ብዝሀ ሕይወት ዋነኛ መሠረት ሆኗል፡፡
የፓርኩ ክልል በምስራቅ በኩል ኮረብታ ቢኖረውም የሚበዛው ሜዳማ ሥነ ምህዳር ነው፡፡ ረግረጋማ፣ በወንዝ የረሰረሰ ደንና እስከ ሦስት ሜትር ቁመት የሚሸፍን ሣር የለበሰ ሜዳ የተዘረጋበት ክልል ነው፡፡
ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በስፋቱ በሀገሪቱ ቀዳሚ ቢሆንም የጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች ውጤታማ አለመሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ለዚህም በቀጣናው ለጥጥ ልማት ደን መመንጠሩ፣ ሕገ ወጥ አደን፣ ተፈናቃይ ሱዳናውያን በአካባቢው መስፈራቸው በመንስኤነት ተመላክቷል፡፡
ቀጣናው የኑዌር እና የአኙዋክ ነባር ጐሣዎች መኖሪያ ነው፡፡ በፓርኩ 69 አጥቢ የዱር እንስሳት ተመዝግበዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ዝሆን፣ ጐሽ፣ የዱር አሣማ፣ ቀጭኔ፣ ጉማሬ፣ ነብር፣ አንበሳ፣ የሜዳ አህያ፣ ዝንጀሮ፣ ጅብ ይገኙበታል፡፡
በፓርኩ ክልል 327 የአእዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ገሚሶቹ የአእዋፍ መንጋ በተለያዩ ወቅቶች የሚፈልሱ መሆናቸውም ተለይቷል፡፡
በወንዞች የተከበበው የፓርኩ ክልል ከየብስ የዱር እንስሳት ባሻገር ወንዞቹ የዓሳ ሀብት መናኸሪያ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ “ናይል ፐርች” የተሰኘው የዓሳ ዝርያ በብዛት ከመገኘቱ ባሻገር አንዱ በክብደት እስከ 100 ኪሎ ግራም የሚመዘን ከባሮ ወንዝ መያዙ በአብነት ተጠቅሷል፡፡
በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ የዱር እንስሳት እና አእዋፍን ከልሎ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች ሙሉ በሙሉ ስኬታማ አለመሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት በቀጣናው ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡ የፓርኩ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአፍሪካ ቀንድ የምርምር ማዕከል ጋር ግንኙነት ፈጥሮ እየሠራ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡
በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክስ ወርልድ ዋይድ እና ዊኪፒዲያ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም