ሕይወት ዕድል ወይስ ምርጫ?

0
299

ገጣሚ መላኩ አላምረው ከዓመታት በፊት ዕድል ብለን ስለምንጠራው ነገር አንስቶ ግጥም አስነብቦን ነበር። ዕድሌ ነው ብሎ ነበር  ያስነበበን።

“በሚስት ልወሰን እኔ ትዳር ሲያምረኝ፤

ሳታገባ የምትቆይ አንድም ሴት አትገኝ

ዕድሌ ነው…

እኔ ዲግሪ ስይዝ ዲግሪ ዋጋ ያጣል

ገንዘብ ያለው ሁሉ  ዶክትሬት ያመጣል

ዕድሌ ነው…

እኔ መድረክ ስይዝ ይፈታል ጉባኤ

እኔ መጾም ሲያምረኝ ይሆናል ትንሣኤ” እያለ ይቀጥላል ግጥሙ። ይህ ሐሳብ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በዕድል የመደገፍን እምነት የሚያንጸባርቅ ነው። የሰዎችን ልፋት እና ዋጋ መክፈል ለማይታይ አንዳች መንፈስ አሳልፎ የመስጠትን ዝንባሌን  ያሳያል ግጥሙ። ዕድል ሽንፈትን መቀበያ እና ለስንፍና እጅ መስጠትን የሚያሳይ ነው። ለዓመታት የለፋንበትን በዕድል እንሸፍነዋለን፤ ጊዜ እና ጉልበት ፈሰስ የተደረጉበትን የድካም ውጤታችንን በዕድል እንሸፍናለን።

ከዓመታት በፊት አንድ ባልደረባዬ ጋር ዕድልን በሚመለከት ተከራከርን። እሱ “ልጅ የራሱን ዕድል ይዞ ይወለዳል” ይለኛል። እኔ ደግሞ “ዕድል ሚባል ነገር የለም፣ ልጅህ ያልሰጠኸውን ከየት ይዞ ይወለዳል” የሚል ነው። “ዝም ብለህ ውለድ ኑሮው እንደሁ ያው ነው ፣ ትናንት ኑሮ ውድ ነው ዛሬም ያው ነው” ይለኝ ጀመር። ሐሳቡ ሊገባኝ አልቻለም፤ አንድ ቢሮ ውስጥ ተቀጥሮ ከሚሰራ ወጣት ልጅ የሚወለድ ልጅ የግሉን ዕድል ይዞ የሚወለደው እንዴት ነው? እኔ አባቱ ሳይርበው  ካላሳደግሁት፣ መስራት የማይችል ሕጻን ዕድል ይዞ የሚወለደው ማን ሊሰጠው ነው? ርግጥ ነው  ሁሉም ሰው  ሲፈጠር  የማድረግ አቅም እና ነጻ ፈቃድ ከፈጣሪው ይዞ ነው የሚፈጠር የሚለውን አውቃለሁ።

የያዝነውን ስልክ ፋብሪካው ሲሰራው  ብዙ ተግባራትን እንዲከውን አድርጎ ነው። ብዙ ሥራዎችን ሊሠራ ከሚችል አቅም ጋር ነው የተመረተው። ስልኩን ገዝቶ የሚይዘው ሰው አጠቃቀም ግን የስልኩን ዓላማ ይቀይረዋል። ጥቂት ሰው ስልኩን ተጠቅሞ ብዙ ገንዘብ ይሠራበታል፤  ቤተሰብ ያስተዳድርበታል። ብዙኀኑ ግን የማይመለከተውን፣ የማይጠቅመውን መረጃ በመሰብሰብ እንቅልፍ የሚነሳውን እና ገንዘብ እና ጊዜውን የሚያባክኑበትን ተግባራት በመሥራት ከአምራቹ ዓላማ ውጪ ያውለዋል።

ሕይወት ምርጫ ሆኖ ሳለ ዕድል ላይ ለምን ሙጥኝ እንዳልን አልገባኝም። በደሀ እና በሀብታም መካከል ያለው ልዩነት የምርጫ እንጅ የዕድል ሆኖ አይታይም። ሀብታሙ “ሀብታም” ለመባል የተጓዘባቸው መንገዶች፣ የወሰናቸው ተግባራት፣ ምርጫዎች እና የሕይወት አቅጣጫዎቹ  ትልቅ ድርሻ አላቸው።

በተቃራኒው ደሀው እንዲሁ ውሳኔዎቹ፣ ተግባራቱ፣ የሕይወት መስመሩ መርተውት “ደሀ” በሚል ሥም እንዲጠራ አድርገውታል። የዓለም አቀፍ ዮጋ ማዕከል ኢሻ  መስራች እና የሕይወት ክህሎት እና መንፈሳዊ ትምህርቶች አሰልጣኝ ሕንዳዊው ሳድጉሩ “በዕድል ላይ የሚተማመኑ እነሱ ሁልጊዜ ከዋክብት፣ ፈለኮች፣ ምርጥ ቦታዎችን፣ የዕድል ጫማዎችን፣ ሳሙናዎችን፣ ቁጥሮችን የሚያሳድዱ ናቸው” ይላሉ። በዚህ  ዕድልን የመጠበቅ ሒደት ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ነገሮች በጭራሽ አይሆኑም ሲሉ ሳድጉሩ ጽፈዋል።

“በሁሉም የሕይወት ዘርፍ እንዲሆን የምትፈልጉትን ነገር እናንተ ራሳችሁ ናቸው የምትፈጥሩት” ይላሉ። አክለውም “ውስጣዊ ሠላም እና መረበሽ ያንተ ሥራ ውጤት ነው፤ኀዘን እና ደስታ፣ ሰው እና ፈጣሪን መምሰል  ያንተ ምርጫ ነው “ በማለት ሳድጉሩ ይቀጥላሉ።

የሰው ልጅ ውስጡ እና ዙሪያውን በሚፈልገው ቅርጽ እና መጠን መሥራት ሲችል ሌላ በተዓምር እንዲሆን በመጠበቅ ላይ መሆኑ ለሳድጉሩ ግርምትን ይፈጥርባቸዋል። የሰው ልጅ ከሚሆነው በላይ ለሚሆኑበት ተግባራት የሚሰጠው ምላሽ እና መረዳት የሕይወት አቅጣጫውን ይወስኑታል። ሳድጉሩ “በዕድል እና በይሆናል አትወሰኑ፣ አንድ ጊዜ ከተቆጣጠሯችሁ በወጥመድ እንደተያዘ አይጥ ትሆናላችሁ፣ ሕይወታችሁም በጠባቂነት የተገደበ ይሆናል” ይላሉ።

በአጋጣሚ ጥቂት ነገሮች (ቻንስ) ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉት ሳድጉሩ ዕድልን የምትጠብቁ ከሆነ መልካም ነገሮች መቃብር ከገባችሁ በኋላ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ይመክራሉ።

ወደ ወዳጄ ሐሳብ ልመልሳችሁ። አሁን ሦስቱ ልጆቹ እንዴት ዕድል ይዘው እንደመጡ እናም ኑሮው ይከብደኛል ሲል እንዴት ቀላል እንደሆነለት እያስረዳኝ ነው።

“የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ ሌላ ቢሮ ነበርሁ፤ ያን ጊዜ አምስት መቶ ብር ደመወዝ ተጨመረልኝ፣ቀጥሎ ሁለተኛ ስወልድ ደግሞ ከ3 ሺህ ብር ደመወዝ ቢሮ ቀይሬ 5 ሺህ ብር ገባሁ። ሚገርምህ በዚህ ቢሮ ደግሞ የደረጃ ዕድገት አገኘሁ እና ደመወዜ 7 ሺህ ብር ሲገባ 3ኛ ልጄ ተወለደች” ብሎ ይነግረኝ ጀመር።  እናም እነዚህ ሦስት ልጆች የየራሳቸውን ዕድል ይዘው ስለ መምጣታቸው አወራኝ። ይህ ሰው ኑሮውን ለማሸነፍ በሰራባቸው ዓመታት ልምድ አካብቷል፤ የቀድሞ ቢሮው የሚከፈለው ብር ትንሽ በመሆኑ ገቢውን ለመጨመር ጥረት አድርጓል። የሥራ ቅጥር ማስታወቂያዎችን ይከታተላል። ሚስት በማግባቱ፣ ልጅ ለመውለድ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንዳለበት ያውቃል።ሥራ ፈልጎ ሌላ የተሻለ ደመወዝ ባለበት ቢሮ ገብቷል። በዚህም ቢሮ የደመወዝ ጭማሪ ለማግኘት ጠንክሮ ሠርቶ ገቢውን አስጨምሯል። በመስክ ስምሪት የሚከፈለውን አበል በመቆጠብ ኑሮውን ቀለል ለማድረግ ሞክሯል።ጥሩ ባህሪውን እያጎለበተ ሥራውን ሠርቷል። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ልጆቼ በተወለዱበት ጊዜ ዕድለኞች ናቸው፤ እነሱ ደመወዝ ጭማሪ እና ጥሩ ገቢን ይዘው መጥተዋል ብሎ ያምናል። እሱ ወጥቶ  ወርዶ የሰራቸው ተግባራት ተደምረው ውጤት ቢያመጡም እንኳን “የልጆች ዕድል ነው” ብሎ ያምናል።

ዝነኛው የእግር ኳስ ሊቅ ፔሌ ስኬት የዕድል ወይስ የጠንክሮ መሥራት ውጤት በሚል ጥያቄ ቀርቦለት ያውቃል። እሱም ሲመልስ “ስኬት አጋጣሚ አይደለም፣ጠንክሮ የመስራት፣ የጽናት፣ የልምምድ፣ የማጥናት እና የመስዋእትነት ውጤት ነው” ሲል ዕድል ከስኬት ጋር ዝምድና እንደሌለው ተናግሯል።

“ከወፍራም እንጎቻ ወፍራም ዕድል፣ያልታደለ ጥጃ በሰኔ ይሞታል፣ልጅ በዕድሉ ያድጋል” የሚሉ እና ሌሎች መሰል ዕድልን እንድንጠብቅ የሚያደርጉን ሐሳቦች ጋር አድገናል።  “ቀበሮ የፍየል ቆለ’ ይወድቃል ብላ ስታንጋጥጥ ትኖራለች” እንዲሉ አበው  በዕድል ጥባቂነት መኖራችን  ፍርሀትና ጭንቀት እንዳይለዩን፣ ርግጠኝነት እንዳይቀርበን አድርጎናል። ከጥረት እና ሥራ ይልቅ ተዓምር ወርዶ አኗኗራችንን እንዲለውጠው በማሰብ የደከምነው ብዙ ነው።

“ዕድሌ ነው” በማለት ብዙዎቻችን የሕይወታችንን ጉድለት ተጠያቂ አድርገን እንመለከታለን። በሕይወት ያልተሳካልን ዕድለኞች ስላልሆንን  ነው  ብለን ዕድልን  ተጠያቂ እናደርገዋለን። የተሳካላቸውን ሰዎች ደግሞ ዕድለኞች ስለሆኑ ነው ብለን ዕድልን ጌታ እናደርገዋለን። የእነሱን ጥረት እና ድካም ዋጋ እናሳጣዋለን።

ሰው እና ሐሳቡ በሚል መጽሐፉ ውስጥ ጄምስ አለን “ሰው በራሱ ይሰራል ወይም ይፈርሳል፣ በውሳኔዎቹ፣ ባለው ኀይል፣ በሐሳቡ፣ በፍቅሩ የራሱ ጌታ ነው” ይላል። በሕይወት ብልህ ውሳኔዎችን ለመምረጥ ብርታት፣ ትዕግሥት፣ ብዙ ሥራን ይጠይቃል። እያንዳንዱ ሰው ታላላቆቹም ይሁኑ ታናናሾቹ ከደረሱበት  ለመድረስ የሚያልፍባቸው የውሳኔ ተግባራት ይለያያሉ። በሕይወታችን ልዩነቱን የሚፈጥረውን ይህ የተለያየ ውሳኔያችን እና የጉዞ አቅጣጫችን ነው።

“ለሁኔታዎች የምንሰጠው ምላሽ፣ ለሌሎች ፍቅራችንን የምንገልጽበት መንገድ፣ ራሳችንን የምንገልጽበት ቃላት፣ ለሥራዎቻችን የምናውለው ጊዜ እና ሌሎች በሕይወታችን የምናሳልፋቸው ጥቃቅን ውሳኔዎች ሕይወታችንን መልክ ይሰጡታል” ይላል ጄምስ አለን በመጽሐፉ።

ዴኒስ ዌትሊ የአሸናፊነት ስነ ልቦና በሚል ርዕስ ባሰናዳው መጽሐፉ “በሕይወት ሁለት ምርጫዎች አሉ ፣ አንደኛው ነገሮች እንዳሉ መቀበል ፤ ሁለተኛው ደግሞ ነገሮችን ለመለወጥ ኀላፊነት መውሰድ ናቸው” በማለት ሕይወት የምርጫ እንጅ የዕድል ጉዳይ አለመሆኑን ያብራራል።  ታሪክን ዘወር ብለን ብናስተውል፣ አሁን በዓለም እየተከወኑ ያሉ ተወዳጅ እና አነሳሽ ተግባራትን  ሁሉም ሰው ከተለመደው ስር ሰደድ ሐሳብ የተለየ፣የከፋ ነቀፋ እና ትችት፣አደገኛ ተቃውሞዎችን፣ እና የማይታሰብ እንቅፋቶችን ተቋቁመው መወሰናቸውን እናያለን ይላል ዴኒስ።

“ሶቅራጥስ በራሱ ሐሳብ በመጓዝ፣ ማሕተማ ጋንዲ ባርነትን በመቃወም፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ ለሰው ልጆች መብት በመታገል፣ ኔልሰን ማንዴላ አፓርታይድን በመታገል ውስጥ አልፈው ጠንካራ እና ትክክለኛ ምርጫዎችን በመውሰድ ምን ማለት እንደሆነ ማሳያዎች ናቸው” የሚለው ዴኒስ ማዘር ቴሬዛ፣ አና ፍራንክ፣ ቤትሆቨን፣ ሮዛ ፓርክስ፣ አብርሃም ሊንከን፣ ስቲቭ ጆብስ፣ ባራክ ኦባማ፣ማይክል ጆርዳን፣ ስቴቨን ሀውኪንስ፣ ኦፍራ ዊንፍሬይ የሕይወታቸውን መስመር በዚህ ልክ ያሰመሩት በትክክለኛ ምርጫዎች ነው ብሏል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here