በኢትዮጵያ ላለው የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች በተጠራው የገንዘብ ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት 610 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል መገባቱ ተገለጸ።
ከሰሞኑ በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ በተካሄደ ገንዘብ ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት ለኢትዮጵያውያን ሕይወት አድን ድጋፍ ለማድረግ ሦስት ነጥብ 24 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር፤ በቃል ደረጃ ለመሰብሰብ የተቻለው ግን 610 ሚሊዮን (35 ቢሊዮን ብር ገደማ) ዶላር ብቻ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው በቃል የተሰበሰበው ገንዘብ እ.አ.አ. በ2024 በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ለመርዳታ ያስችላል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ጆይስ ምሱያ እንዳሉት 20 መንግሥታት 610 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል::
እንግሊዝ 125 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች። አሜሪካ ደግሞ 154 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብላለች። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በበኩሉ ለዜጎቹ የምግብ ድጋፍ ለማድረግ 250 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተገልጿል::
የገንዘብ መዋጮውን ሥነ ሥርዓት ያዘጋጁት ኢትዮጵያ፣ እንግሊዝ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች አካላት ናቸው::
ሆኖም የመንግሥታቱ ድርጅት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች ምላሽ ለመስጠት ለሚቀጥሉት አምስት ወራት አንድ ቢሊዮን ዶላር የግድ ያስፈልገኛል ብሏል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚያጋጥማትን የምግብ እጥረት ለማስቀረት ትሠራለች ብለዋል።
125 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገችው የእንግሊዝ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሩ ሚሼል በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ የከፋ ድረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም