አካዳሚዎች እና ህልማቸዉ

0
205

የእግር ኳስ አካዳሚዎች ወጣቶችን በማዘጋጀት  ለከፍተኛ ደረጃ የሚያበቃቸውን የሥነ ምግባር፣ የቴክኒክ፣  የታክቲክ እና የአካል ብቃታቸውን በማጎልበት የላቀ ሚና ይጫወታሉ። በዘርፉ ባለ ተሰጥኦ ታዳጊዎች በሳይንሳዊ ስልጠና ከታገዙ ክለቦችን እና ብሔራዊ ቡድኖችን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታመናል።

የእግር ኳስ አካዳሚዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ የታላላቅ ክለቦች ስኬት መሰረቶች ናቸው። የባርሰሎናው ላሜሲያ፣ የቦርሲያ ዶርትሙንዱ ኢቮኒክ፣ የአያክስ አምስተርዳሙ እና የቤኔፊካው እግር ኳስ አካዳሚ ባለ ተሰጥኦ የእግር ኳስ ኮከቦች የሚፈለፈሉበት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሀገራችንም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የክለቦች እና ሌሎች የመንግሥት እና የግል በርካታ የእግር ኳስ አካዳሚዎች እንዳሉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መረጃ ያረጋግጣል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የእግር ኳስ አካዳሚዎች ውጤታማ ናቸው ለማለት ግን አያስደፍርም። ለውጭ ገበያ ለማቅርብ ይቅርና በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ የሊግ እርከን የሚጫወቱ ተጫዋቾችን እንኳ ለማፍራት እየተቸገሩ ነው። ምንም እንኳ በሀገራችን ሳይንሳዊ ስልጠና መስጠት የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም አሁንም ግን  ተግባራዊ  እየተደረገ አይደለም።

ለመሆኑ የእግር ኳስ አካዳሚ ምንድነው? መስፈርቱስ ምንድን ነው?

የእግር ኳስ አካዳሚ ታዳጊ ወጣቶች የአካል ብቃታቸውን ፣ የቴክኒክ፣  የታክቲክ ክህሎቶችን ለማሻሻል እና ታዳጊዎቹ እንደ  ግለሰብ እና እንደ ስፖርተኛ ራሳቸውን ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ትምህርታዊ እና ሥነ ልቦናዊ  ልዩ ስልጠና የሚወስዱበት የስልጠና ማዕከል ነው።

ወጣት ተጫዋቾች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች እንዲሆኑ የተለያዩ መሰረታዊ ክህሎት የሚማሩበት ቦታ ጭምር ነው። የእግር ኳስ አካዳሚዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አነስተኛ ስቴዲየሞች፣ ልዩ እና የተሟላ የንድፈ ሀሳብ የስልጠና ማዕከል፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ የመኝታ ሥፍራ እና የተሟላ የስፖርት ቁሳቁስ ሊኖራቸው እንደሚገባ የኢንተርናሽናል ፉት ቦል አካዳሚ መረጃ ያስነብባል።

እነዚህን መስፈርቶችን ተመልክተን ወደ ሀገራችን ስንመጣ የእግር ኳስ አካዳሚዎችን  በየሰፈሩ ካሉት  ትናንሽ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች ለመለየት ያዳግታል። በአህጉራችን ካሉት አካዳሚዎች የምሥራቅ እና የደቡቡ  ከሰሜን እና ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃጸር ልዩነቱ የሰማይ እና የምድር ያህል መሆኑን መስካሪ አያሻም።የምእራብ እና የሰሜን አፍሪካ ሀገራት አካዳሚዎች በልዩነት ከፍ ብለው የሚገኙ ናቸው፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ አካዳሚ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና የእግር ኳስ አሰልጣኙ በላይነህ ጨቅሌ  (ዶ.ር ) ከአሚኮ በኩር ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ባለሙያው በላይነህ ጨቅሌ (ዶ.ር) አሁን ላይ የፖለቲካ ተቋማት የእግር ኳስ ልማቱን እየመሩት መሆናቸው አካዳሚዎች ላይ ለውጥ ማየት እንዳልተቻለ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን ጨምሮ ሌሎቹ የእግር ኳስ አካዳሚዎች ስልጠናዎችን የሚሰጡበት፣ የታዳጊዎችን አቅም፣ ብቃት እና ጥራት የሚለኩበት የራሳቸው ብሄራዊ ሞዴል (National Model) የላቸውም ብለዋል ባለሙያው። በሀገራችን የሚገኙ የእግር ኳስ አካዳሚዎች በሥርዓተ ትምህርት(curriculum) አለመመራታቸው የራሳቸው ማንነት (Identity) እንዳይኖራቸው አድርጓል።

ለአብነት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ታዳጊዎችን ይዞ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። ከአሰልጣኞች መካከል አንዱ  በላይነህ ጨቅሌ (ዶ.ር) ስልጠናውን የሚሰጡበት ምንም ዓይነት ብሄራዊ ሞዴል ወይም የእግር ኳስ  ፍልስፍና እንደሌላቸው ጭምር አስረድተዋል። ችግሩ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ብቻ ሳይሆን  የሁሉም የሀገራችን የእግር ኳስ አካዳሚዎች ችግር   ነው ተብሏል።

እየተከተሉ ያሉት የቆየውን ኋላቀሩን አሠራር በመሆኑ አብዛኞቹ ታዳጊዎች የአካዳሚ ስልጠናቸውን ጨርሰው ሲወጡ ባክነው ነው የሚቀሩት። በርካታ ታዳጊዎች የመጨረሻውን  የዕድሜ እርከን (ከ17 ዓመት በታች)  ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላ በክለቦች ዐይን ውስጥ ለመግባት ይቸገራሉ።

ታዳጊዎች በአካዳሚ ቆይታቸው ተከታታይነት ያለው የውድድር መድረክ አያገኙም። ይህ ደግሞ ከስልጠና ማዕከሉ ብቁ ሆነው እንዳይወጡ እያደረጋቸው ይገኛል። በአጠቃላይ ስልጠናው የሚሰጥበት፣ የሚመዘኑበት መንገድ  እና ሌሎችም ሳይንሳዊ አለመሆናቸው የታዳጊዎችን ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል። የእግር ኳስ አሰልጣኝ እና መምህር በላይነህ  ጨቅሌ (ዶ.ር) የእግር ኳስ አካዳሚዎች በምን መንገድ መሥራት እንዳለባቸው የመፍትሔ ሀሳብ ያሉትን ጠቁመዋል።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የእግር ኳስ አካዳሚዎች በምን መንገድ መሥራት እንዳለባቸው  ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት የእግር ኳስ ባለሙያዎች ቀዳሚው ተግባር ነው። በዓለም ላይ በእግር ኳሱ የተሳካላቸው ሀገራት እንደነ ጀርመን፣ ስፔን፣ ስዊዘርላንድ፣ ብራዚል እና አርጀንቲናን የመሳሰሉት የራሳቸውን ብሔራዊ ሞዴል(National model) በማዘጋጀት ሥራቸውን ጀምረው ውጤታማ ሆነዋል። በቅርቡም አውስትራሊያ ከላይ የጠቀስናቸውን ሀገራት ፈለግ እየተከተለች መሆኑን የእግር ኳስ ባለሙያው ተናግረዋል። ታዲያ በሀገራችን የሚገኙ የእግር ኳስ አካዳሚዎችም የራሳቸው የእግር ኳስ ማንነት፣እሳቤ እና ብሔራዊ ሞዴል ያስፈልጋቸዋል ነው የተባለው።

መሰረተ ልማቶችን በማሟላትም ትልቁን የእግር ኳስ አካዳሚ ችግር መቅረፍ ይገባል።በሀገራችን ለእግር ኳስ ኢንቨስትመንት የሚወጣው ረብጣ  ገንዘብ ቢሆንም የእግር ኳስ መሰረተ ልማቶች ግን የተሟሉ አይደሉም።  ኢትዮጵያ ውስጥ የእግር ኳስ አካዳሚዎች ብቻ ሳይሆኑ አብዛኞቹ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች  በቂ የጅምናዚየም እና የልምምድ ቦታ እንኳ እንደ ሌላቸው ይታወቃል። እነዚህ ክለቦች በርካታ ገንዘብ በማውጣት ተጫዋቾችን ከማስፈረም ይልቅ  የእግር ኳስ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ቢጀምሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአካዳሚዎች ላይ የሚፈለገውን ለውጥ መምጣት እንደሚቻል ተጠቁሟል።

የእግር ኳስ አካዳሚዎች  የጋራ ሀገር አቀፍ መስፈርት ያስፈልጋቸዋል፤ የራሳቸው የመተዳደሪያ ደንብም ሊኖራቸው ይገባል።  ከጊዜው ጋር የሚሄዱ፣  ራሳቸውን የሚያሻሽሉ እና ሳይንሳዊ ስልጠና የሚሰጡ የበቁ አሰልጣኞች ሊኖራቸው ግድ ይላል። ውድድር በራሱ አንድ የእድገት አካል በመሆኑ የአካዳሚ ሰልጣኞች ራሳቸውን ለመገምገም እና ለመፈተሽ እንዲያግዛቸው በቂ የውድድር መድረክም ማግኘት ይኖርባቸዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ሰልጣኞች እግር ኳሱን እንዲወዱ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ አካዳሚ ስልጠናዎችን ጨርሰው የሚወጡት የ17 እና የ18 ዓመት ታዳጊዎች በተፈጥሮ የአካል ብቃታቸው ደካማ በመሆኑ ፈተና ላይ ይወድቃሉ። በዚህ እድሜያቸው ሳይጠነክሩ ከአካዳሚ መውጣታቸው በክለቦች ያላቸውን ተፈላጊነት ይቀንሰዋል። ይህ ደግሞ በሥነ ልቦናቸው ተጽዕኖ በማሳደር እግር ኳስን እንዲያቆሙ ያስገድዳቸዋል፡፡  ታዲያ ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው በ17 እና በ18 ዓመታቸው የአካዳሚ ስልጠናቸውን ጨርሰው የሚወጡ ሰልጣኞችን ወደ ሌላ ተጨማሪ የልህቀት ማዕከል በማሸጋገር ብቁ የማድረግ ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል የእግር ኳስ ባለሙያው።

የቤልጂየም ወርቃማ ትውልድ እንዴት እንደተፈጠረ ስናስብ እና የመረጡትን መንገድ በተወሰነ ስንቃኝ   ቤልጂየሞች ነገን በማሰብ ታዳጊዎቻቸው ዘመናዊ ስልጠናን እንዲያገኙ  ወደ አጎራባች ሀገራት አካዳሚዎች በመላክ  ስልጠና እንዲወስዱ አድርገዋል።  ልጆቹ ሀገራቸውን ሳይዘነጉ መሰረታዊውን የእግር ኳስ አቅም በማዳበር ለዓለም ክስተት መሆን እንደቻሉ የፉትቦል አካዳሚ መረጃ ያሳያል።

እግር ኳሱ በባለሙያ ከተመራ፣ የእግር ኳስ አካዳሚ ጥራት እና  ታዳጊ ወጣቶች ለእግር ኳስ የሚሰጡት ግምት ከፍ ካለ በእግር ኳስ አካዳሚዎች የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በአካዳሚው የሚገኙ የትኛውም የሥራ ከፍሎች ለቦታው በሚመጥኑ ብቁ (Qualified) በሆኑ ባለሙያዎች የሚመሩ መሆን ይኖርባቸዋል። በአንድ ወቅት የባየርሙኒክ እግር ኳስ አካዳሚ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የእግር ኳስ አካዳሚ ለመክፈት መፈራረሙ አይዘነጋም፡፡  ኢትዮጵያዊያን አካዳሚዎች ከሌሎቹ ሀገራት አካዳሚዎች ጋር በአጋርነት  ቢሠሩም የተሻለ ለውጥ ማየት ይቻላል።

አካዳሚዎቹ የራሳቸው የሆነ የአካል ብቃት ባለሙያ (fitness coach)፣ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች(Nutritionist) እና የተሟላ የሚዲያ ባለሙያ እንዲኖራቸው አስገዳጅ ሕግ መቀመጥ አለበት፤ የባለሙያው ሀሳብ ነው፡፡ እግር ኳስ የታዳጊ ወጣቶችን አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውንም ሊቀይር እንደሚችል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ታዲያ ይህንን  በኢትዮጵያ መመልከት ለምን ተሳነን? ይህ ለሁሉም የስፖርት አመራሮች እና ቤተሰቦች ጥያቄ መሆን አለበት።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here