አውሮፓውያን አፍሪካን በተቀራመቱበት የበርሊኑ ጉባኤ ላይ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ ለጀርመን ተሰጡ። ይህ ግዛት ሩዋንዳ-ኡሩንዲ ሲባል አስተዳደራዊ ዋና ጽሕፈት ቤቱም ቡጁምቡራ ነበረች- የዛሬዋ የቡሩንዲ መዲና።
በ1898 ዓ.ም ዶ/ር ሪቻርድ ካንድትን ለሩዋንዳ የመጀመሪያው ልዩ ተቀማጭ ገዢ አድርጎ ሾመው። የኒያሩጌንጌ ኮረብታማ ስፍራን ለሀገሪቱ አማካይ በመሆኑ መረጠ። እንደ ቢሮውም የሚያገለግለው የመኖሪያው ቦታውን በአሁኑ ጊዜ ጋኪንጂሮ ገበያ ያለበት አካባቢን አደረገው። መላዋ ሩዋንዳ ከዚህ ማእከል ነበር የምትተዳደረው።
እስከዚያን ድረስ ከቡጁምቡራ አንቀልባ ላይ ያልወረደው የሩዋንዳ አስተዳደር በ1899 ዓ.ም ነፃነቱን አወጀ፤ ከቡጁምብራ አስተዳደር። ከዚያም በቀጣዩ ዓመት በ1900 ዓ.ም የሩዋንዳ አስተዳደራዊ ማእከሏ ኪጋሊ ተባለች።
በ1901 ዓ.ም የአሁኑ የንያሩጌንጌ ገበያ ባለበት ስፍራ 20 ሱቆች ብቻ ተገንብተው ነበር:: ባለቤቶቻቸው ደግሞ ሕንዳውያን ነጋዴዎች። የዛሬው የኪጋሊ ማእከላዊ እስር ቤት በሚገኝበት ስፍራ ላይም አንድ ወታደራዊ ካምፕ ተመስርቶ ነበር።
ኪጋሊ በመጨረሻ በአቀማመጧ ማእከላዊነት የተነሳ ጠቃሚ የንግድ ማእከል በመሆን አደገች። በቡጁምብራ አልፎ በቡኮባ እና ኪጎመ(ታናጋኒካ በዛሬዋ ታንዛኒያ) ለሚደረገው በዲሞክራቲክ ኮንጎዋ ኪሳንጋኒ እና በኡጋንዳዋ ካምፓላ መካከል ይደረጉ ለነበሩት የንግድ እንቅስቃሴዎች መተላለፊያ ማእከል ነበረች። ይህ ለውጥም የንጉሡ ቤተ መንግሥት ከነበረበት ኒያንዛ ወደ ኪጋሊ በርካታ የአረብ እና የሕንድ ነጋዴዎች እንዲሳቡ አድርጓል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመን በመሸነፏ ቤልጅየም የሩዋንዳን አስተዳደር ከጀርመኖች እጅ ወሰደች፤ ነገር ግን ኪጋሊ አሁንም የመላ ሀገሪቱ አስተዳደራዊ ማእከል እንደሆነች ቀጠለች። ከተማዋ የሀገሪቱ ጠንካራ መናገሻ እና ጠቃሚ የቢዝነስ ማእከል ወደ መሆን ማደጓን በመቀጠሏ፣ ከቀሪው የሀገሪቱ ክፍሎች ጋር የሚያገናኙ የመንገድ መገናኛዎች እና ከቀሪው ዓለም ጋር እንደ መግቢያ በር የሆነውን የካኖምቤ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ አይነት ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች እየተሟሉ መጡ።
የሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ በሀገሪቱ እምብርት ላይ፣ በኪጋሊ ተራራ እና በጃሊ ተራራ መካከል በኒያቡጎጎ ወንዝ አቅራቢያ ቡዋናሲያምቡዌ እየተባለ በሚታወቀው በተፈጥሮ የታደለ ክልል ውስጥ ትገኛለች። የሺ ኮረብቶች ምድር የምትባለው የሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ የተቆረቆረችው እርስ በርስ በተቆላለፉት ተራሮች መሀል ሲሆን ተራሮቹ በሂደት የሚገናኙ እና አንዳቸው ከአንዳቸው በትላልቅ ሸለቆዎች የተለያዩ ናቸው፤ ያም የእንቁላል ቅርጽ ይሰጣቸዋል።
የኪጋሊ ከተማ በስምንት ወረዳዎች ወይም ክፍለ ከተማዎች የተከፋፈለች ናት። ንያሩጌንጌ፣ ካሲሩ፣ ንያሚራምቦ፣ ኪሱኪሮ፣ ጊኮንዶ፣ ካኖምቤ፣ ቡታምዋ ይባላሉ። ከ1.5 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ተጨናንቆ የሚኖርባት በዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ከተማ ናት።
ይህን የተጨናነቀ ሁኔታ ለማስተካከል ተያያዥ የተደቀኑ ችግሮችን በመቅረፍ ላይ ማተኮር የከተማ አስተዳደሩ ሃላፊነት ነበር። የከተማዋን አካባቢያዊ ጽዳት መጠበቅ እና የትራፊክ መጨናነቅን ለመቅረፍ መንግሥት ከ76 ሚሊየን በላይ በሆነ በጀት የከተማ ውስጥ መንገዶችን በዘመናዊ እና ሳይንሳዊ መንገድ በታገዘ መልኩ የመገንባት ሰፊ ስራዎችን አከናውኗል። ዜጎች ከመሀል ከተማ እስከ ከተማ ዳርቻዎች የሕዝብ ማመላለሻ ባሶችን እንዲጠቀሙ አበረታቷል። በከተማዋ የአረንጓዴ ልማት አካል የሆነውን የጋዝ ልቀት መጠን ቅነሳን ለማሳካት ነዳጅ የማይጠቀሙ ሞተር ሳይክሎችን እና መኪናዎች እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል ። እንዲህ አይነት የቴክኖሎጂ ምርቶችን የሚያቀርቡ በርካታ ኩባንያዎች በከተማዋ እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል።
ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በማውጣትም ፋብሪካዎች ከከተማ ወጥተው በተዘጋጀላቸው ስፍራዎች እንደገና እንዲተከሉ በማድረግ የልቀት መጠኑን መቀነስ ተችሏል። በሌላ በኩል ኪጋሊ ምንም አይነት የፕላስቲክ ከረጢት ሆነ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲኮችን በየመንገድ ተጥሎ ማየት ብርቅ እስኪሆን ከተማዋ ጽድት ያለች ሆናለች። የፕላስቲክ መያዢያዎች ወደ ሀገርም እንዳይገቡ እና ወደ ውጭም እንዳይላኩ ሩዋንዳ እገዳ በማድረግ ከባንግላዲሽ ቀጥላ ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች። ይህን እገዳ ተላልፎ በፕላስቲክ የታሸጉ ምርቶችን ሲያስገባም ሆነ ሲያስወጣ የሚገኝ ግለሰብ ደግሞ ጠንከር ያለ ቅጣት ተዘጋጅቶለታል። እስከ ስድስት ወራት እስራት ወይም ሕዝብ ፊት ወንጀሉን እንዲናዘዝ እና በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ይደረጋል። ይህ ክልከላ በመደረጉ ታዲያ የኪጋሊን አካባቢ ንፁህ አድርጓታል።
ኪጋሊ አንድ ለየት የሚያደርጋት ነገር አለ። ይኸውም ከመኪና ነፃ የሆነ ዞን ነው። ኢምቡጋ ሲቲ ወክ ይባላል፣ በከተማዋ እምብርት ያለ ክልል ነው። ወደ 520 ሜትር የሚሸፍን በመሀል ከተማዋ ያለው የኪጋሊ ትልቁ ከተሽከርካሪ ነፃ የሆነ መተላለፊያ ኮሪደር ነው። በከተማዋ መስተዳድር የተገነባው እና በአንድ የግል ኩባንያ የሚተዳደረው ይህ ጎዳና ለሕዝብ ሕይወትን ያላበሰ ነው።
ተሽከርካሪዎችን በማስወገድ እና በአረንጓዴ የተዋበ የሕዝብ ስፍራ በመፍጠር የትራፊክ መጨናነቅን እና የበካይ ጋዝ ልቀትን በከተማዋ ማእከል ላይ ለመቀነስ ያለመ ነው። በ2013 ዓ.ም በከተማ አርሰን ፕላኒንግ ዘርፍ የተጠናቀቀው የኢምቡጋ ሲቲ ዎክ አረንጓዴ ስፍራዎችን፣ የኪነት ክልሎችን፣ የአንስተኛ የንግድ ኪዎስኮችን፣ የመንገድ ዳር መቀመጫዎችን እና ሌሎችን ለእግር ተጓዦች ተስማሚ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ይዟል።
እጅግ ሰላማዊ፣ ፀጥ ያለ ስፍራ በመሆኑ ሰዎች በጧት ተነስተው ወይም ወደ ማታ እየመጡ ይዝናናሉ፣ ሀሴት እያደረጉ መንፈሳዊ እርካታ የሚያገኙበት ስፍራ ነው። ሰርግ፣ ምርቃት፣ ልደት እና መሰል ክስተቶችን በዚሁ ስፍራ የሚያከብሩ ሁሉ በነፃነት ይገለገሉበታል።
ምንጭ – kigalicity -greencitykigali.com
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም