ትንቢት እና ደመላሽ

0
190

ከዓመታት በፊት ከ10ኛ  ወደ 11ኛ ክፍል ለማለፍ ስሟን ያስቀየረችን ልጅ ዛሬ ድረስ አስታውሳታለሁ። በፈተና መውሰጃ ክፍል ውስጥ ትንሳኤ የሚባል ጎበዝ ተማሪ ነበር። ይህ ተማሪ  ወደ ሚቀጥለው ክፍል ለመሸጋገር ብዙዎች ዓይናቸውን ጥለው የሚጠብቁት ሰው ነው። ይህች ዛሬ ድረስ የማስታውሳት ልጅ ስሟን ብትችል ትንሳኤ ማለት ትፈልግ ነበር ።

መምህራን እና  ተማሪዎችም እንደሚያሽ ሟጥጡባት ተገንዝባ ቢያንስ ትንቢት ልባል ስትል ወሰነች። በዚህ ስሌት መሠረት ትንቢት ከትንሳኤ ጎን ወይም ከኋላው ተቀምጣ እሱ መልስ ሲያከብ እየተከተለች ልትሞላ ተዘጋጀች። ይህ ስም የመቀየር ዝግጅት ግንቦት መጨረሻ ላይ ለሚደረግ ፈተና ቀድሞ ሕዳር ላይ ተጠናቋል።  የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በሙሉ የትንቢት እና የትንሳኤን ጉዳይ እያወራ ወራት ነጎዱ። “ግሩም ነው ዝም ብላ ብታጠና አይሻላትም ነበር” በሚል ብዙዎች ተነጋገሩበት።

ይህን ያውቁ የነበሩ መምህራን ትንቢትን የፈተና ቀን ሲደርስ ብቻዋን እንድትቀመጥ ተወስኖባት ወይኔ ስትል ቀርታለች። “ኧረ ካርዱ እንዲመጣልሽ እንኳን ትንሽ አንብቢ” ሲሉ የነበሩት አባቷ ብስጭት ይዘው ቀሩ። “ዕድሜ ለትንሳኤ ፏ ብዬ ነው ማልፈው” ስትል ከርማ ሳይሳካላት ቀረ።

የስም ነገርን አንስቼ እስኪ ትንሽ ልበላችሁ። ስም እና ተግባር አንድ ቀን ሲገናኙ ሌላ ጊዜ ሆድና ጀርባ ሲሆኑ እናያለን። በብዛት ግን ስም ከተግባር እና ማንነት ጋር ዝምድና የለውም። እውነትም እንደ ስሟ (እንደስሙ) የሚባለውን ያህል የስሙ ክፋት ይባልለታል። የመልዓክ ስም ይዘው የሰይጣን ተግባር  ያላቸው ሰዎችም አሉ።

ስሞች በብዙ ምክንያቶች እና ዓላማዎች ለሰው ልጆች እና ለነገሮች ሊሰጡ ይችላሉ። በኢትዮ_ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ጠላትን ለመከላከል አንድ የሰፈራችን ሰው ሚስቱን አስረግዞ ዘመቻ ይሄዳል። ሚስትዬዋ ቀንም ሌትም ለቅሶዋን ቀጠለች። ጽንሱ ገፍቶ ልጅ ተወለደ። እናት ገና ልጅቷ ሳትወለድ ስም አውጥታ ነበር። መልሽው ይርጋ ስትል ስም አወጣች።

ጦርነቱ አልቆ ባልዬው በድል ወደ ቤቱ ተመለሰ። በናፍቆት ሚስቱን ሲገናኝ ሌላ ልጅ ተረገዘ። ስሙንም ተመስገን ይርጋ ብለው አወጡለት። እያንዳንዱ ስም ምክንያት እና ከጀርባው አንዳች ምስጢር አለው። በደርግ ዘመን እና በኋላም የተወለዱ ልጆች አብዮት የሚል ስም ወጥቶላቸዋል።

በደርግ ዘመን መንግሥቱ የሚሉ ሥሞችም ይበዛሉ።ምናልባትም የወቅቱን መሪ መንግሥቱ ኀይለ ማርያምን ምሳሌ አድርጎ ይሆናል።  ዓባይ የሚል ስም ቀደም ብሎ የሚሰማ ቢሆንም እንኳን የሕዳሴ ግድቡን የመገደብ ሐሳብ እና ተግባር ሲጀመር ስሙ በብዛት ተሰምቷል። እንዲያውም ይገደብ ዓባይ የሚሉ ስሞች ቀድመው የመሰማታቸውን ያህል ፣ሕዳሴ የሚሉ ስሞች ዓባይ ከተገደበ በኋላ በዝተዋል።

መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ የሚል ብሂል ደግሞ  አለን።ማህበረሰቡ ቁንጅና እንዲህ ነው ብሎ ተስማምቶ ካስቀመጠው መስፈርት በተቃራኒ የሚወጡ አስቂኝ ስሞች አሉ። ዓይታችሁ ይች ፉንጋ የምትሏት ልጅ ስሟ አበባ፣ ቆንጅት፣ ብርቱካን፣ ማሪቱ፣ ወርቅነሽ፣ ሻሺቱ፣ ብሪቱ እና ሌሎች መሰል ስሞችን ይዛ ልታዩ ትችላላችሁ። በዚህ አተያይ መልክ እና መጠሪያ ስሙ ግንኙነት እንደ ሌለው እንገነዘባለን።

እስኪ ደግሞ ስምን በወንዶች በኩል እንየው። ደፋሩ፣ አንበሳው፣ ዋጠው፣ ሰልቅጠው፣ አይሸሽም፣ ማንደፍሮ እና ሌሎችም ስሞች የተሰጡት ሰው በእውነቱ ስታዩት ተቃራኒ ይሆናል። ኮሽ ሲል ሚደነብርን ወንድ አንበሳው ወይም አይሸሽም ብሎ መጥራት ያስቃል።

አንዳንድ ስሞች አደራ የሚመስሉ ናቸው። በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ጉልበት ትልቁ መከበሪያ እና መታፈሪያ ነው።ለግጭት ከሚዳርጉት ዋናዎቹ ነገሮች ደግሞ የመሬት ሀብት አንዱ ነው። ሁለት ባላገሮች በመሬት ድንበር ይጣሉና ጉልበታሙ ደካማውን ይገድለዋል።

ይህ ታሪክ ወደ ቋሪት አካባቢ የተፈጸመ ነው ብሎ ያጫወተኝ አጎቴ ነው። በአጋጣሚ የሟች ሚስት ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የሞተው ባሏን እያሰበች ሕጻኑ ወንድ በሆነልኝ ስትል ትጸልይ ነበር። ባሏ ድንገት በወጣበት መሬቱን ለማስከበር ባደረገው መከላከል መሞቱ ውስጧን ሰብሮታል።

ልጇ አድጎ የእርሻ ማሳ ላይ የሞተውን ባሏን ደም እንዲመልስ አብዝታ ትፈልግ ነበር። ፈጣሪ ልመናዋን ሰምቶ  ወንድ ልጅ ሰጣት። ቀድሞ ታስቦ ነበር እና ሕጻኑ እንደተወለደ ደመላሽ የሚል ስም ተሰጠው። የሕጻኑ ስም ፤ ከስምነት በላይ ትልቅ አደራ እና ኀላፊነት የተሰጠው ልጅ መሆኑን ያሳያል።

ሕጻኑ የሞተው አባቱን ደም እንዲመልስ ታሪክ እና ቁጭት እየተጋተ ፤ለበቀል ዝግጅት እያደረገ፤ የአባቱን ገዳይ እያየው፤ ገዳይ እያረጀ የሟች ልጅ ደግሞ እየጎረመሰ እናም ቀኑ ደረሰ እያለ ፤ እናትም “ደም መላሽ” እያለች ባላደራነቱን እያስታወሰችው አደገ።

ሕጻኑ ደመላሽ በቀል ይዞ አደገ 22 ዓመታት ተቆጠሩ። ገዳይ ደመላሽን ፊቱ ላይ ሲያድግ ቢመለከተውም፤ ስሙም አደራ ያለበት ቢሆንም እንኳን ደመላሽ የልቡን በልቡ አድርጎ ከገዳይ ጋር ወዳጅ መስሎ አደገ።

ግንኙነቱ የሚበቀል አይመስልም፤ አባቱን የገደለበት ሰው ጋር በዚህ ደረጃ ይቀራረባል ብሎ መጠበቅም አይገመትም ነበር። የሟች ወዳጆች “አንተ ሞኝ ደምህን መልስ እንጂ” እያሉ ያስታውሱት ነበር። ልጅ የተሰጠውን አደራ  አልረሳም።ጊዜ እና ሁኔታውን እየጠበቀ ነበር። አንድ ቀን የአባቱን ገዳይ እርሻ ማሳ ላይ ባለበት ገድሎት በበቀል ስሜት ሰክሮ አካባቢውን ጥሎ ተሰደደ። ደም መመለስ ነበር የተሰጠው ተልዕኮ 22 ዓመታትን ጠብቆ አሳክቷል።

ከዘጠኝ ወንድ ልጆች መካከል አንዷ ብቸኛ ሴት ናት። የቄስ ልጅ ናት። እናቷ አምስት ወንድ ልጆችን ሲወልዱ ደስ ቢላቸውም እንኳን ሴት ልጅ በማጣታቸው ይማረሩ ነበር። ስድስተኛ ልጅ ሲሞክሩ ሴት ተወለደች። ቤተሰቡ በደስታ ፈነጠዘ።

አንድ ዓመት ሲሞላት ይህቺ የቤተሰቡ ብርቅዬ ሴት ልጅ ሞተች። ቤተሰቡ ድጋሜ በሴት ልጅ ምኞት እና ናፍቆት ውስጥ ቀጠለ። እናት በተለይ  ሴት ልጅ አገኘሁ ሲሉ በሞት በመነጠቃቸው ከፍተኛ ኀዘን ውስጥ ገቡ። እንጉርጉሮ እና ለቅሶ አልለያቸው ይላል። በቅርብ ጊዜ ድጋሜ አረገዙ። ጠይም አሳ መሳይ ሴት ልጅ ወለዱ። ስሟንም አስረስ አሏት። የቀደመውን ኀዘኔን እና ለቅሶዬን በአንቺ ረሳሁ ማለታቸው ነው።ይህ እማሆይ ሰገዱ አየለ ያጫዎቱኝ ታሪካቸው ነው። ከዚህ ጋር የሚቀራረቡ ብዙ ስሞች አሉ። አስረሳኸኝ፣ ሰማኸኝ፣ ማስረሻ እና መሰል ስሞች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ አትርሳው የሚል አደራን ሰጥተው ሁልጊዜ በንቃት እና በማስታወስ ውስጥ እንድንቆይ የሚያደርጉ አሉ።

አትርሳው ሁልጊዜ ንቁ ሁን ፣አደራ አለብህ የሚልን ሐሳብ ሊገልጽ ይችላል። ርግጥ ከዚህ የተለየ ሐሳብን ሊያንጸባርቅ ይችላል። ድሮ የተፈጸመብህን በደል እና ጥላቻ እንዳትረሳ በሚል ስናየው ደመላሽ ከሚለው ጋር ይቀራረባል። ቂም እና ጥላቻን አስይዞ ሊያሳድገንም ይችላል። ይህ ስም ከጀርባው ታሪክ ካለው። ደምሰው ተሻገር የሚል ስም ለልጁ አደራ ሰጥቶ የሚያሳድግ ይሆናል።

ስሞች ፓለቲካዊ፣ መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ታሪካዊ ግለሰባዊ  ሁነትን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላሉ። የሚያወጣቸው ሰውም የተለያዬ ሊሆን ይችላል። ስምን ወላጅ፣ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ የሀይማኖት አባት፣ ማህበረሰብ ሊያወጡት ይችላሉ ፤ አንዳንድ ቤተሰብ በድህነት ውስጥ ሆኖ ልጁን ሀብታሙ ብሎ ይጠራል። ለምን ሀብታሙ እንዳለ ቢጠይቁት ምክንያቱን የሚያውቀው ስም አውጪው ብቻ ነው። ምናልባት ገንዘብ ቢያጣ ጤና በማግኘቱ ሀብታም ነኝ እያለ ይሆናል ወይም ደግሞ ደሀ ነህ የሚሉትን ሰዎች ለማበሳጨት አለዚያም ልጄ ሀብታም እንዲሆን እፈልጋለሁ እያለ ሊሆን ይችላል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ስሞችን ብንመለከት ከሁለት ዘርፎች ውስጥ የሚመዘዙ ናቸው። አንዱ ከቅዱሳን መጽሐፍት (መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁርዓን) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከማህበረሰቡ አኗኗር የሚቀዱ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚወለዱ ልጆች ስማቸው ኢትዮጵያዊ ለዛ እየራቀው ነው፤ የኢብራይስጥ ስሞች ቀጥታ ከመጽሐፍት ተወስደው ለልጆች እየተሰጡ ነው ብለው የሚወቅሱ አሉ። የቀደሙትን ስሞች መቀየር በብዛት የተለመደ ሆኗል። ልጆች በወላጆች የወጣላቸውን ስም ሲያድጉ ይቀይሩታል። ይህ ደግሞ “ስሙ እኔን አይገልጽም፣ አልተመቸኝም፣ ያስፎግረኛል፣ ያሳቅቀኛል” እና ሌሎችንም ምክንያቶች በማቅረብ ስምን መቀየር የተለመደ ሆኗል። ድምጻዊ ኤልያስ ተባባል የቀድሞ ስሙ ልዋጥህ ተባባል የሚል ነበር። አዲስ አበባ ማሲንቆውን ይዞ ሲመጣ ብዙዎች ይስቁበት እና በስሙ ይገረሙበት ነበር። ቀጥሎም ስሙን መቀየርን ምርጫው አድርጓል። ዛሬ ላይ ኤሊያስ ተባባል እያልን እንጠራዋለን። የልጆች ስም ከዘመኑ ጋር መጣጣም አለመቻሉ ለስነ ልቦናዊ ጫና ስለሚዳርጋቸው ስማቸው ብሩህ እና ተስፋ ያለው ቢሆን ሳይመረጥ ይቀራል?

የዛሬ ስሞች ምን መልክ አላቸው? በእኔ ማስተዋል በቅጽል ስም መጠራት እየተለመደ ነው። የኪነ ጥበብ ሰዎች በቅጽል ስሞች የመጠራት ልምምድ አላቸው።በተለይ የፊልሙ ዘርፍ ሰዎች በቅንፍ የሆነ ስም አላቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከቅዱስ ቁርዓን፣ የታዋቂ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ስሞች ፣ የቁልምጫ ስሞች በሀገራችን አሉ። በዚህም ምክንያት ብዙው ስም መሀሙድ፣ ወይም አቤል የመሆን ዕድሉ ሰፊ ይሆናል። እንደ ቀድሞው ዘመን የተለያየ ምክንያት ሲኖር ስሞች የመመሳሰል እድላቸው ጠባብ ነው። ልዩ ምክንያት ሲኖር ስሞች የመደጋገም ዕድላቸው አናሳ ነው። እንደ ቀድሞው ዘመን  ከግለሰብ ተሞክሮ በመነሳት የሚወጡ ስሞችን መስማት ብርቅ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን ሳድያ እና ቤተልሄም  መሰል ስሞችን ከቅዱሳን መጽሐፍት  ላይ የመውሰድ ልምዳችን አድጓል። አደም ግዛቸው ፣ዘልቀህ በላቸው፣ ሽማጫሽ ተሰማ እና መሰል ስሞች አሁን ወደ ከተሞች ሲገቡ እንግዳ ይሆናሉ። የመለወጥ ሐሳብን የሚያመጣውም ይህ የእንግዳነት ስሜት ነው። ዘንድሮ ረጃጅም ስሞች እየተወደዱ አይመስለኝም። አጭር እና ቀላል ስሞች በብዛት ሲወጡ እንሰማለን። ታዋቂ ሰዎች ስማቸው ብርቅናት ቤሪ፣ ኢየሩሳሌም ጄሪ፣ ወንድወሰን ወንዲ፣ ቴዎድሮስ ቴዲ፣ ሕይወት ሒዊ፣ መኮነን ማክ በሚል በአጭር ሲጠሩ እንሰማለን። ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፋዊነት ምክንያት ከሌላው የዓለም ዳርቻ እዚሁ እኛ ጓዳ ውስጥ ይገኛሉ። በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች ያሉ ስሞች በስሞቻችን ላይ ተጽእኖ አላቸው። ስም በተለያዩ ምክንያቶች ይቀየራል። መግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት ፈተና ለመኮረጅ፣ ለፓለቲካዊ ዓላማ፣ በሹመት፣ ከፉገራ እና ሽሙጥ ለመገላገል፣ ለመደበቅ፣ የትጥቅ ትግል፣ በድብቅ ለመጻፍ፣ በፓለቲካዊ ለውጥ እና ሌሎች ምክንያቶች መቀየር ግድ ይሆናል። ከግለሰቦች በተጨማሪ ተቋማትም በየፖለቲካ ለውጥ መታጠፊያው ላይ የስም ለውጥ ያደርጋሉ።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here