ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ክልል፣ ከአዲስ አበባ 510 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአርባ ምንጭ ከተማ አቅራቢያ በአባያ እና ጫሞ ሀይቆች መካከል ይገኛል::
ፓርኩ በ1979 እ.አ.አ በዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ህብረት ነው የተመሰረተው:: በሁለቱ ሀይቆች መካከል የእግዜር ድልድይ ተብሎ የሚጠራ የተንጣለለ የመሬት ወሽመጥ ላይ የተከለለ ፓርክ ነው:: የፓርኩ ክልል 514 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ወይም 127 ሺህ ሄክታር ተለክቷል::
ፓርኩ ከመሬት ወለል በላይ ከ1 ሺህ 250 እስከ 1 ሺህ 650 ሜትር ከፍታ ልዩነት ተመዝግቦበታል:: ፓርኩ በከፍታ እስከ 4 ሺህ ሜትር የተለካዉ የሲዳሞ ተራራ መገኛም ነው::
የፓርኩ ክልል ደን፣ የከርሠ ምድር ውኃ፣ የተፈጥሮ ፍል ውሀ እና በሣር የተሸፈነ ሜዳን ያካተተ ነው:: ስነ ምህዳሩ በበርካታ አጥቢ እንስሳት፣ በዓሳ እና በእጽዋት ዝርያዎች መኖሪያነቱም ይታወቃል::
በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ አጥቢ እንስሳት አንበሳ፣ ጉማሬ፣ የሜዳ አህያ፣ ጦጣ፣ ጅብ ወዘተ ይገኙበታል:: አእዋፍትን በተመለከተም ከ300 በላይ ዝርያዎች ተመዝግበዋል:: በሀይቆቹ እና ወንዞች “ናይል ፐርች” ዓሳዎች በብዛት እንደሚገኙ ድረ ገጾች አስነብበዋል:: ሀይቆቹ በርከት ያሉ ዓዞዎች መናኸሪያ ሲሆኑ እስከ ስምንት ሜትር የሚረዝሙ ዓዞዎች መገኘታቸውን የድረ ገጾች ጽሑፍ አመላክቷል:: በተጨማሪም በአባያ ሀይቅ ዳርቻ የአዞ ገበያ መኖሩ ነው የተገለፀው::
በፓርኩ ክልል ከሚገኙ እጽዋት በርከት ብለው ግራር፣ በለስ በየሳሩ እና ኮረብታዎች መካከል ይታያሉ:: የእጽዋት ዝርያ ከቦታ ቦታ እንደየወቅቶቹ ሳስቶ እና ተበራክቶ ነው የሚስተዋለው- በፓርኩ ክልል:: ይህም በወቅቶቹ የዝናብ፣ የሙቀት መጠን ወዘተ. ለልዩነቶቹ ምክንያት መሆኑን ልብ ይሏል::
በሀይቆቹ መካከል የተንጣለለው የነጭ ሳር ሜዳ በግልቡ ሲያዩት ባዶ ይመስላል:: ነገር ግን በትኩረት ለተመለከተ የሜዳ አህያ መንጋ፣ ቀበሮ፣ የዱር ውሻ “ስዋይን ሀርት ቢስት” ለዕይታው ይበቃሉ::
የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን በከበቡት ሀይቆች ዳርቻ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አስራ አምስት የቢራቢሮ እና ስምንት የውኃ ተርብ ዝርያዎችንም ይዟል::
ለዘገባችን አክሸንተር ኢትዮጵያ ሜክ ሄሪቴጅ ፈን፣ እና ኢትዮቪዚት ድረ ገጾችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም