በዘንባባ ዝንጣፊ ከሞት ተራፊ

0
166

በምዕራባዊ ፓስፊክ ውቅያኖስ የሞተር ጀልባቸው በማዕበል ተመቶ ከአገልግሎት ውጪ የሆነባቸው ዓሳ አስጋሪዎች በአቅራቢያው በሚገኝ ሰው አልባ ደሴት ላይ ከደረሱ ከስምንት ቀናት በኋላ በዘንባባ ዝንጣፊ ባስተላለፉት የድረሱልን መልዕክት ከሞት መዳናቸውን ያሁ ኒውስ ድረ ገጽ አስነብቧል::

በእድሜ አርባዎቹ ውስጥ የሚገኙ ሦስት ልምድ ያላቸው ዓሳ አስጋሪዎች ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ከቤታቸው ወጥተው ሞተር ጀልባቸውን ይዘው ይሰማራሉ::

ሆኖም ስድስት ሜትር ርዝመት ያላት የሞተር ጀልባቸው በማዕበል በመመታቷ ጉዳት ደርሶባት መንቀሳቀስ ይሳናቸዋል:: ሦስቱ ዓሳ አስጋሪዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ደሴት ለመድረስ ባደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ሰው አልባዋ ፒክ ሎት ኤቶል  ላይ  ይደርሳሉ:: ደሴቷ ኗሪ ሰው አልባ በመሆኗ በእጅጉ ይቸገራሉ:: በረሀብ እና ጥም ላለመሞት የዘንባባ ፍሬ እየበሉና አሸዋ ምስው ያገኙትን የጉድጓድ ውሀ እየጠጡ ቀናትን ያስቆጥራሉ::

ከዓሳ አጥማጆቹ ቤተሰብ አንዷ ከቤት ከወጡ ከስድስት ቀናት በኋላ ቤተሰቦችዋን የበላቸው ጅብ ባለመጮኹ በአቅራቢያዋ ለሚገኝ የአሜሪካ የባህር ሀይል ማዕከል ማስታወቋ ተጠቁሟል:: ይህንኑ መነሻ በማድረግ የነፍስ አድን ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ፍለጋውን ይያያዘዋል::

የባህር ሀይል ማዕከሉ የፍለጋ ግብረ ሀይል አስጋሪዎቹ ተንቀሳቅሰዋል በተባለበት አካባቢ በአውሮፕላን አሰሳ ይካሄዳል:: በዚሁ መካከል በሰው አልባዋ ደሴት አሸዋ ላይ በዘንባባ ዝንጣፊ የተፃፈ የአድኑን የርዳታ ጥሪ መልዕክት ይመለከታል- የፍለጋ ቡድኑ::

የነፍስ አድን ግብረ ሀይሉ ፈጥኖ የአድኑን መልዕክት ወዳየበት ክልል አነስተኛ ጀልባ ይልካል:: በቦታው ከደረሱ የነፍስ አድን ሠራተኞች አንዱ የተፈላጊዎቹ ወይም የዓሳ አስጋሪዎቹ ዘመድ ሆኖ በመገኘቱ በቋንቋቸው መግባባት መቻሉ ነው የተዘገበው::

በመጨረሻም የነፍስ አድን ቡድን አባላቱ ዓሳ አስጋሪዎቹን በሰላም እና በጤና ወደ ወጡበት መኖሪያ መመለሳቸውን ነው በማጠቃለያነት የሰፈረው::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here