በሀገራችን በፌደራል እና በየደረጃው ባሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች በዓመት ከሁለት ጊዜ ባላነሰ በይቅርታ ይለቀቃሉ፡፡ ለዚህ ማሳያም ዘንድሮም የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ባሳለፈው ውሳኔ 1 ሺህ 431 ወንድ እና 29 ሴት ታራሚዎች በይቅርታ መለቀቃቸውን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም ለመገናኛ ብዙኃን ገልፀዋል፡፡
ለመሆኑ የይቅርታ እና ምሕረት አንድነት እና ልዩነታቸው ምንድን ነው? በሚለው እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ምክትል ረዳት ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ወ/ሮ ትዕግስት ጣሰው ከበኲር ጋዜጣ ዘጋቢ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ምክትል ረዳት ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ወ/ሮ ትዕግስት ጣሰው እንደሚገልፁት ጥፋተኝነቱ በፍርድ ተረጋግጦ በማረሚያ ቤት የቆየ እንድ ታራሚ ይቅርታ የሚደረግለት በቆይታው በሥነ ምግባር መታነፁ እና መፀፀቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች የፈጸሙት ወንጀል ይቅርታ የማይከለክል፣ ከተወሰነባቸው የጊዜ ቆይታ ውስጥ አንድ ሦስተኛ፣ አንድ አራተኛ እና አንድ አምስተኛውን የጨረሱ ናቸው ፡፡
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ መንግሥት ፍርደኛው ማረሚያ ቤት ከሚቆይ ይልቅ ኅብረተሰቡን ቢቀላቀል ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያበረክታል ብሎ በሚያስብበት ጊዜም ይቅርታ ያደርጋል፡፡
በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ ይቅርታ ሊደረግ እንደሚችል በወንጀል ሕጉ ቁጥር 229 ላይ ሰፍሯል፡፡ የይቅርታ አሰጣጥ አፈፃፀም ሥነ ስርዓትን ለመምራት የወጣው አዋጅ ቁጥር 840/2006 መሰረት አንደኛ በሕግ አኳኋን ካልተደነገገ በቀር በሕግ የተወሰነ ቅጣት ሥልጣን በተሰጠው አካል በሙሉ ወይም በከፊል በይቅርታ ሊቀር አሊያም ደግሞ ዓይነቱ አነስተኛ ወደሆነ ቅጣት ሊለወጥ እንደሚችል ተቀምጧል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የይቅርታ አሰጣጥ በሕግ እንደተደነገገው ሆኖ ይቅርታ ሲሰጥ ታራሚው ላይ የተወሰነው ፍርድ ቀጣይ ሌላ ወንጀል ፈጽሞ ከተገኘ እንደ ተጨማሪ የወንጀል ማክበጃ እንደሚያዝ በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡
ሦስተኛው ይቅርታው የወንጀል እንጅ የፍትሐብሄር ጉዳዮችን (ኃላፊነትን) አያስቀርም፤ ይሄም ሲባል የሕግ ታራሚው ካሳ እንዲከፍል ፣ የመንግሥት ንብረት እንዲመልስ ፣ የግለሰብ ሃብት እንዲያስረክብ ተወስኖበት ከሆነ እነዚህን ጉዳዮች ይቅርታው አያካትትም፡፡
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ይቅርታ የሚያገኙ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ብቻ ናቸው፡፡ በአቃቤ ሕግ ተከሰው በቀረበባቸው ማስረጃ መሰረት በሌሉበት የጥፋተኝነት ውሳኔ ያገኙ ሰዎች ግን ይቅርታ አያገኙም፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ከይቅርታ ውጭ ምሕረትም ይሰጣል፡፡ ምሕረት እንዴት እና በማን እንደሚሠጥ በአዋጅ ቁጥር 1089/2010 ላይ በግልፅ ሰፍሯል። በዚህ አዋጅ መሰረት ምሕረት ሊያደርግ የሚችለው የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1096/2010 የምሕረት አዋጅ እንዴት እንደሚያደርግ እና እንዴት እንደሚሰጥም በዝርዝር ተደንግጓል፡፡
እንደ ወ/ሮ ትዕግስት ማብራሪያ ምሕረት ሲሰጥ አንድ ሰው ጥፋተኛ ተብሎ በሕግ ቢፈረድበት እንኳ ቅጣቱ ይቀራል፡፡ ይህም ሲባል ፍርድ ተሰጥቶት ከሆነ ይቀራል፤ በክስ ላይ የነበረ ከሆነ ይቋረጣል ፤ ክሱ ካልታየ ደግሞ ክስ አይቀርብበትም፡፡ ምሕረት ፍፁም ነው።
አብዛኛው ምሕረት የሚሰጣቸው የፖለቲካ ወንጀል ፈፃሚዎች በሕገ መንግሥቱ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ ለተፈፀመ ወንጀል፣ የሀገር መክዳት ፣ የአመፅ ወንጀሎች እና በሀገር እና በመንግሥት ላይ አመፅ ማስነሳት እንዲሁም መሰል ድርጊቶችን በመፈፀም ተከሰው ማረሚያ ቤት የቆዩ ታራሚዎችን አልያም የሚፈለጉ ሰዎች መንግሥት ያለፈ ጥፋታቸውን ሁሉ ምሕረት የሚያደርግበት (የሚሰረዝበት ) ነው፡፡
ምሕረት ሲደረግ ምሕረት የተደረገለት አካል ጫካ ገብቶ ከሆነ ምሕረት በተደረገለት ጉዳይ ምሕረቱን ተቀብሎ ካልገባ እንኳን በሌላ ጊዜ ምሕረት በተሠጠበት ወንጀል መልሶ ሊያስከስሰው አይችልም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ሰው በተደረገለት ምሕረት እንደማንኛውም ሰው ንፁህ ተብሎ ቢቆጠርም ሌላ ወንጀል ከሠራ ግን መጀመሪያ የተሰጠው ምሕረት አያድነውም፡፡
በ1996 በወጣው የወንጀል ሕግ ምሕረት ሊደረግ እንደሚችል በዚሁ የወንጀል ሕግ ቁጥር 230 ተደንግጎ ነበር ። ይህንን ሕግ ማስፈፀሚያ ደግሞ ከላይ በጠቀስናቸው 2010 ዓ.ም የወጡ አዋጆች መፈጸሚያ ምሕረትም ይቅርታም ስለሚደረግባቸው ሥነ ስርዓቶች ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ባለሙያዋ እንዳብራሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 28 መሰረት ዘር ማጥፋት፣ ያለ ፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር እንዲሁም ኢሰብአዊ ድብደባ የፈፀመ ታራሚ ግን ይቅርታም ምሕረትም አያገኝም፡፡ ለአብነት አንድ ሰው በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሶ 30 ዓመት ቢጠፋ ይርጋ ሳያግደው በተገኘበት ሰዓት ክስ ይመሰረትበታል፡፡
ሆኖም ግን በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀጽ አንድ የተጠቀሱ ቅጣቶችን ፈፅመው የሞት ቅጣት የተወሰነባቸው ሰዎች ርእሰ ብሄሩ ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት ሊቀይር ይችላል እንጂ ይቅርታ የለውም፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም