የአባቶቹ ልጅ

0
213

ጣሊያን ከአድዋ ሽንፈቱ ማግስት ጀምሮ ወዳጅነት የመሰረተ መስሎ በትግራይ፣ በጎንደር፣ ጎጃምና፣ ሸዋ፣ ደሴ እና አፋር በከፈታቸው ቆንስላዎቹ፣ በሚሺነሪዎቹ እና ሌላ ስውር የተንኮል ሴራዎችን እየሰራ ለጦርነት ሲያደርግ የነበረውን የአርባ ዓመታት የዝግጅት ጉዞውን ባለፈው ሳምንት ባጭሩ ለማሳየት ሞክረናል።  የዚያን ቀጣይ ታሪካዊ ሂደቶች እነሆ!

አሳፋሪውን የአድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል እንዲህ ያለ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው የፋሽስት ሙሶሎኒ አገዛዝ በቂ ዝግጅት እንዳደረገ ሲረዳ ወረራ ለመጀመር አንዳች ሰበብ እየጠበቀ ነበር።

ነገሩ በእንዲህ እያለ ነበር ለሙሶሊኒ የተመቼ ክስተት ብቅ ያለው፥ የወልወል ግጭት። ግጭቱ ጉዳት አስከተለ። ጣሊያን በላይ ሆና ኢትዮጵያ በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ እና ካሳ እንድትከፍል ጠየቀች። ኢትዮጵያ በተቻለ መጠን ነገሩ በሰላማዊ ሽምግልና እንዲያልቅ የቻለችውን አደረገች እና ለሊግ ኦፍ ኔሽንስ አቤት አለች። ነገሩ ሁለቱንም ለግጭቱ ተጠያቂ ባለማድረግ እንደ ነገሩ ተቋጨ።

ይሁን እንጂ በዓመቱ የሙሶሊኒ ጦር መጠነ ሰፊ ወረራ በሰሜን ከፈተ። የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት በአየር እና በምድር ሜካናይዝድ ጦር እየታገዘ መስከረም 21 ቀን 1928 ዓ.ም በይፋ ወረራ ጀመረ። የኢትዮጵያ ሠራዊት በሚገባ ተከላክሎ ለማስመለስ ሞከረ። ነገር ግን የጠላት ጦር ሀይሉን አጠናክሮ መስከረም 26 ቀን 1928 ዓ.ም በብዙ መስዋእትነት አድዋን ከተማን ያዘ። የአድዋን መያዝ ሙሶሎኒ ሲሰማ ዜናውን በማስተጋባት መላ ጣሊያንን አስፈነጠዘ።

የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር የጣሊያንን ወረራ መጀመር ሲገነዘብ በመላ ኢትዮጵያ የክተት ጥሪ አወጀ። መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም። የጣሊያን ጦር በይፋ ወረራ ከጀመረ አንድ ቀን በኋላ መሆኑ ነው። የጀግኖቹ ምድር እንደገና በቁጣ በንዴት ተንተከተከ። ወትሮም ሀገር ስትጠቃ ተነስ ተብሎ ለአፍታ መቀመጥ የማያስችለው የእነዚያ ጥቁር አናብስት ልጅ ልክ እንደ አድዋው ሁሉ ተነሳ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ በእጁ ያለውን መሳሪያ ይዞ ለዘመቻ ተነሳሳ። ሴቶች የዘማቹን ስንቅ ማዘጋጀቱን አጧጧፉት። በየአካባቢው ይፎክራል፣ ይሸለላል።

የጦር መሪዎች ሹመት በንጉሠ  ነገሥቱ  ተሰጠ። ራስ ሙሉጌታ የሰሜኑ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው ተሾሙ። ራስ እምሩ የጎጃም እና የጎንደር፣ ራስ ካሳ የወሎ፣ ራስ መንገሻ ስዩም የትግራዩን እየመሩ ወደ ሰሜን እንዲዘምቱ ተሾሙ። የከምባታው ጦር ጥቅምት 1 ቀን 1928 ዓ.ም ገስግሶ አዲስ አበባ ደረሰ። የወለጋ፣ የከፋ፣ የኮንታ፣ የጎሬ ጦር በየአለቃው ወደ አዲስ አበባ ከተተ። በአዲስ አበባ ታላቅ የሰልፍ ትእይንት ተደረገ። ሁሉም በየአዛዡ የየራሱን ሰልፍ እያሳየ በንጉሡ ፊት አለፈ። ንጉሡም በሰራዊታቸው የሚቀጣጠለው የሀገር ፍቅር ስሜት አስደንቋቸው ታላቅ ንግግር አሰሙ፣ “….አሁንም የመጣብን ጠላት ደም የተቃባነው ከጥንት የቆየ ነው፣ እንጂ አዲስ ድንገተኛ ጠላት አይደለም። ሰላም ፈላጊ የሆነውን የመንግሥታቱን ማኅበር አምነን ጦራችንን ወደ ግንባር ባለማስቀደማችን አሁን ያገኘውን ሁሉ በጭካኔ ከመግደል በቀር እንኳን ለወታደር ለሽማግሌ፣ ለሴት፣ ለሕጻንም ይራራል ተብሎ አይጠረጠርም። ለሕፃናት እና ለሴቶች አለመራራቱን ባጀማመሩ ሰምተነዋል።

“በማንኛውም ቢሆን ሞት አይቀርም እና እገሌ በሳልና በጉንፋን፣ በተስቦ ሞተ ከሚባል ለሀገሩ ነፃነት፣ ለንጉሡ ክብር፣ ለትውልዱ ስም ደሙን አፍስሶ ሞተ ሲባል ትልቅ ጥቅም ያለው መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በጦርነት ላይ አንዱ ቢሞት ተራውን ተወጣ ይባላል እንጂ፣ እገሌ ሞተ ብሎ መደናገጥ የጀግንነትን ክብር የሚያዋርድ መሆኑን ማወቅ ነው።

“ለወታደርም፣ ለባላገርም፣ ለነጋዴም ቢሆን ትልቁ ኩራቱ የሀገሩ ነፃነት መሆኑ የማይጠረጠር ነው። ስለዚህ ከመካከላችሁ ጠብ እና ተንኮል እንዲጠፋ፣ ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፋ ሎሌ ለጌታው፣ ጭፍራ ለአለቃው መታዘዝን እንዲያውቅ በሚቻላችሁ ሁሉ ማስረዳት ነው። ኢጣሊያኖች በመሣሪያቸው ቢኮሩብን እኛም ትልቁ መሣሪያችን የእግዚአብሔር እርዳታ ስለሆነ እንኮራባቸዋለን።

“ቀይ፣ ቢጫ፣ እና አረንጓዴ ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን ምልክት ነውና ይህ የነፃነታችን ምልክት እንዳይጠፋ እስከ መጨረሻዋ ጠብታ ደማችንን እያፈሰስን ብንሞትም ለስማችን እና ለታሪካችን ትልቅ ክብር ነው” ያሉት ጃንሆይ  ሰራዊቱ   በብስለት እንዲዋጋ በመግለፅ በጦር ሜዳ  መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች ሁሉ ዘርዝረው በማሳሰብ ጦሩን በድል ተመለስ ብለው ሸኝተዋል።

በሰሜኑ ግንባር የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሰራዊት በሶስት ክፍለጦር ተዋቀረ። አንደኛው ክፍል በራስ እምሩ እዝ ስር የተሰለፈው ነበር። የግራ ክፍሉን እንዲሸፍን እና በሽሬ ግምባር ጣሊያንን እንዲዋጋ ታዝዟል። መሀሉን ይዞ በተምቤን ግንባር እንዲዋጋ የተመደበው ደግሞ በራስ ስዩም መንገሻ እና በራስ ካሳ ኃይሉ የሚታዘዘው ሠራዊት ነበር። በቀኝ በኩል አምባራዶም ተራራማ ስፍራን ይዞ እንዲዋጋ የተሰየመው ሰራዊት በጦር ሚንስትሩ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ የሚመራው ሰራዊት ነበር።

ዱቼ ሙሶሎኒ በመላው ኢትዮጵያ የክተት ጥሪው መተላለፉን እንደሰማ በሁሉም ግንባሮች ወረራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በይፋ ለጠቅላይ አዛዡ ጄኔራል ዲ ቦኖ ትእዛዝ አስተላለፈ። በዚህ ሁኔታ የተንቀሳቀሰው የጣሊያን ጦር የመጀመሪያ ውጊያውን በሽሬ ግምባር በራስ እምሩ ከሚመራው የጎንደር እና የጎጃም  ጦር ጋር አደረገ። በቆራጥ አመራራቸው የሚደነቁት ራስ እምሩ ጦራቸውን በሚገባ አስተባብረው የጠላትን ጦር አስጨነቁት። የፋሽስት ተዋጊ ጀቶች በሰማይ በሚያዘንቡት ቦምብ፣ በምድር በሚርመሰመሱት ዘመናዊ ታንኮች እና መትረየሶች ያልተበገረው የራስ እምሩ ጦር ጠላትን እያጨዱ ከመሩት። የጣሊያንን ሰራዊት በየውጊያ አውዱ እየከበቡ አተራመሱት። የሙሶሊኒ ጦር ታንኩን ሳይቀር እየተወ ነፍሱን ለማዳን ፈረጠጠ።  በዚህ ጦርነት እስከ አስር ታንኮች እና ሁለት ዘመናዊ መድፎቻቸው በርካታ የጠላት ጦር ተማርኳል፣ በርካቶች ሙት እና ቁስለኛው ሆነዋል።  የአድዋ ጀግኖችን ታሪክ ደግመው ጣሊያን ዳግም አንገት እንዳትደፋ የሚል ከፍተኛ ስጋት በጣሊያን ሰፈር ሰፈነ። በዚህ የተደናገጠው የሙሶሊኒ ጦር የአየር ድብደባውን በማጠንከር የመርዝ ጋዝ ማዝነቡን ተያያዘው። ይሁን እንጂ የራስ እምሩ ጦር ይህን ሁሉ መአት ተቋቁሞ እስከ ደም ጠብታ ተጋደለ። በመጨረሻ ግን የመርዝ ተጋዙ በማየሉ አልበገሬው የራስ እምሩ ጦር የማታ ማታ ለማፈግፈግ ተገደደ።

የተምቤኑ ግንባር ሌላው ከባድ ትንቅንቅ የተደረገበት የውጊያ አውድ ነበር። በራስ ስዩም መንገሻ እና ራስ ተካሳሽ ሀይሉ አዝማችነት የአባቶቹን ገድል የደገመው የኢትዮጵያ ጦር የውጊያ ብቃት እዚህም በተግባር የታየበት ነው። ኢትዮጵያውያን በምድር ውጊያ ፍፁም እንደማይሸነፉ ጠላት በተግባር ያረጋገጠበት ነበር።

መቀሌን ለመያዝ የጣሊያን ጦር በአየር ሽፋን እየተሰጠው በምድር በዘመናዊ ታንኮች እየታገዘ ቢዋጋም ምሽጉ ድረስ እየተወረወሩ ለነፃነት የሚዋደቁትን የራስ ስዩምን እና ራስ ካሳን ወታደሮች ብርቱ ክንድ መቋቋም ከበደው። የኢትዮጵያ ጀግኖች በጨበጣ ሳይቀር እየተዋደቁ የጠላትን ቅስም ሰበሩት። የፋሽስቱ ጦር የአድዋ አሳፋሪው ሽንፈት እንደሚገጥመው ስለተረዳ በሙሶሎኒ ትእዛዝ ወሳኝ የአሰላለፍ ለውጥ ለማድረግ ተገደደ። ጦርነቱን ሲመራው የነበረውን ዲ ቦኖን ሽሮ በጨካኝነቱ የተመሰከረለትን ማርሻል ባዶሊዮን ለመሾም ተገደደ። ከዚህ በኋላ የጦርነቱ መልክ ተቀየረ። በአየር የሚደረገው ድብደባ በመርዝ ጋዝ ስርጭት ጭምር ታጀበ። ያም ሆኖ የራስ እምሩ ጦር በቁርጠኝነት እየተፋለመ ከተዋጋ በኋላ የማታ ማታ ለማፈግፈግ ተገደደ። እናም በብዙ መስዋእትነት መቀሌ በፋሽስት እጅ ወደቀች።

ሁለቱ ራሶች የጠላትን የኃይል ሚዛን አዛብተው ሙሶሎኒንና ሮምን ያስደነገጡ ጀግና የጀግኖች መሪ ነበሩ።

በአምባራዶም ግንባር ራስ ሙሉጌታ የሚያዝዙት የኢትዮጵያ ጦር የጠላትን ጦር የውጊያ ብቃት፣ የኢትዮጵያውያንን ለሀገር ፍቅር የመዋደቅ የቁርጠኝነት ልክ ለጠላት አስተማሩት። ሽማግሌው የጦር አበጋዝ ለማርሻል ባዶሊዮ ምትሀት ሆኑበት። የጠላትን አሰላለፍ እያነበቡ በፍጥነት በሚቀያይሩት የውጊያ ስልቶች ራሱን ማርሻል ባዶሊዮን ግራ እስኪጋባው አራወጡት። እስከመጨረሻው ሕይወቱን ሰጥቶ እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊታቸውን እያዋጉ ቢያስጨንቁት ከአየር የመርዝ ጋዝ እያዘነበ ከሽንፈት ራሱን አዳነ። የኢትዮጵያ ሰራዊት በጀግንነት ሲዋደቅ በመርዝ ጋዙ ተፈታ።

የመጨረሻው ትእይንት ማይጨው ላይ ሆነ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ራሳቸው የተገኙበት ወሳኝ ጦርነት መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም ቀኑን ሙሉ ተደረገ። ወደ ሰባ ተዋጊ ጀቶች የተሳተፉበት ዘግኛኝ ጦርነት ነበር። 36ቱ በኢትዮጵያ ጦር ተመትተው የተከሰከሱ ሲሆን ከእነዚህ አንዱ የራሱ የሙሶሊኒ ልጅ ቤቶሪዮ ተመትቶ የወደቀበት ይገኝበታል። እነዚህ አውሮፕላኖች እየተመላለሱ 35 ቶን የሚመዝን ቦምብ እና የመርዝ ጋዝ አዝንበዋል።

ባዶሊዮ ስለ ጦርነቱ ለሙሶሊኒ ቴሌግራም አደረገ፦ “በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት አለቀ። በማይጨው እየተዋጋን የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂት ወታደሮች በቀር የተረፈ የለም።” ብሎት እንደነበር መሪራስ አማን በጥንቷ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ አስፍረውታል። በመጨረሻም ሰራዊቱ ተበተነ። ጣሊያን መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ማሸነፉን ለዓለም አወጀ። ከዚያም ለአምስት ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ የበቀል ግፍ ፈፀመ።

በመጨረሻ ሚያዚያ 27 ቀን 1936 ዓ.ም አርበኞች ሀገራቸውን ከወራሪ አጽድተው ቀይ ቢጫ አረንጓዴ የክብር ሰንደቅዓላማቸውን በክብር ዳግም ሰቀሉ። ድሉ የጣሊያን የቅኝ ግዛት ህልም ዳግም የመከነበት፣ ወራሪው ዳግም የሽንፈት ካባ የተከናነበበት፣ ኢትዮጵያ በልጆቿ ክቡር መስዋእትነት ሁሌም ተከብራ እና ተፈርታ የምትኖር የአልበገሬ ጀግኖች መፍለቂያነቷን ዳግም ለዓለም ያረጋገጠችበት ነበር። ኢትዮጵያን ሲሉ በየዘመናቱ ውድ ሕይወታቸውን እየሰጡ ለታደጓት ለእነዚያ ጀግኖች ሚያዚያ 27 ቀን መታሰቢያ ሆኖ ይዘከራል። መልካም የአርበኞች መታሰቢያ ቀን፣ አበቃሁ።

ምንጭ – ተክለፃዲቅ መኩሪያ፣

የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ-መሪራስ፣

አማን በላይ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ-አባ ጋስፓሪኒ የኢትዮጵያ ታሪክ፤

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here