የሰላም በሮች ሲከፈቱ የዕድገት ጮራ ይፈነጥቃል!

0
183

ችግሮች ውለው  ባደሩ ቁጥር   ሌላ  ችግር እየወለዱ  ክልላችንም ሆነ ሀገራችን ከቀውስ ነፃ አልሆኑም።  በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ቀውሱን ለመፍታት የኃይል ርምጃ እንጂ ግልፅ፣ አሳማኝ፣ አሳታፊ እና አግባቢ  ፖለቲካዊ መንገድ  ሲመረጥ አይስተዋልም።

ችግርን ማቃለል፣ መካድ፣ ለችግሩ ሦስተኛ ወገንን ተጠያቂ ማድረግ፣ “እኔ ብቻ ነኝ ልክ!’ ብሎ የማሰብ አደገኛ አዝማሚያም አለ።  በዚሁ  የተሳሳተ መንገድ ምክንያት  ሕግ እና ፍትሕ፣ ንግግር እና ድርድር የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ ጎራ ለይቶ መተኳኮስ  የፖለቲካ ማስፈፀሚያ ሲሆን ይስተዋላል። በመሆኑም ግድያ፣ እገታ፣ እስር፣ ፍረጃ፣ ጥርጣሬ፣ ዋስትና ማጣት… አማራ ክልልን ጨምሮ እንደ ሀገር ዛሬም ቀጥሏል።

የአማራ ክልል ለዘጠኝ ወራት በዘለቀ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ይገኛል። በዚህ  ጊዜ አንድ ጊዜም የሁሉንም አሸናፊነት የሚያረጋግጥ ንግግር ተሰምቶ አያውቅም። “ና ተማረክ!… ና መሣሪያ አውርድ!… ና የኔን ሐሳብ ተቀበል!… ና በኔ መስመር ተሰለፍ! …” የሚል ትእዛዛዊ አካሄድ በዝቶ ታይቷል። ይህም ቁጣ እና እልህ በመቀስቀስ  የበለጠ ቀውስ እና ምስቅልቅልን ፈጥሯል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የውሸት የመረጃ ፍሰቱ ከጦርነቱ ባላነሰ ሁኔታ የማህበረሰባችንን ደኅንነት ፈትኗል፤ ጥርጣሬውን ጨምሮታል። ይህም በሕዝብ እና በመንግሥት  መካከል ሊኖር የሚገባውን ጠንካራ ግንኙነት አላልቶታል።

ሀገር እንደዚህ በሆነች ጊዜ መውጫው መንገድ ውይይት፣ ፍትሐዊነትን ማስፈን፣ ሕዝብ የሚገዛው እና ሕዝብን የሚጠቅም አጀንዳ ማምጣት፣ የንግግር እና የእርቅ  መርሀ ግብር መዘርጋት ተገቢ ነው።  ግጭቱ በዋለ ባደረ ቁጥር ያንዲት ሀገር ዜጎችን ሕይዎት እያጠፋ፣ ሀብት ንብረትን እያወደመ፣ የሀገርን አቅም እየቀነሰ፣  ስለሆነ ስለሰው፣ ስለወገን እና ስለሀገር ሲባል የሰላም በሩ  ሳይውል ሳያድር ሰፋ ብሎ ሊከፈት ይገባል።

ጎራ ለይቶ ርስ በርስ ከመወጋገዝ መደማመጥ፣ መግባባት፣ በውሸት እና በሴራ የተፈጠረው ችግር ለማንም እንደማይበጅ አውቆ ችግሩን ተሾልኮ ለማለፍ ከመሞከር ይልቅ ለእውነቱ ቀርቦ  ለመፍትሄው በጋራ መቆም ያስፈልጋል። ያ ካልሆነ ነገሩ ሁሉ ውኃ ወቀጣ ሆኖ ዜናው ሁሉ ግጭት፣ ሞት፣ የሀብት ንብረት ውድመት፣ ስደት… ብቻ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል።

በርስ በርስ መተኳኮስ ከውድመት እንዲሁም ውድቀት በስተቀር ፈፅሞ ማትረፍ ስለማይቻል  የንግግር እና የድርድር በሮች እንዲከፈቱ፣ ለግጭቱ መፈጠር መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች በውል ተለይተው ምላሽ እንዲሰጣቸው ማድረግ ያስፈልጋል።   ሰላምን የማይሻ፣ በሀገሩ የደኅንነት ዋስትና አግኝቶ መኖር የማይፈልግ ማንም ዜጋ የለም።  በመሆኑም ይህ እውነታ ሊጤን፣  የሁሉም ሰብዐዊ ፍላጎት ለሆነው  ሰላም  ሁሉም ወገን  ሊተጋ ግድ ይላል! ይህ ሲሆን የሰላም በሮች ይከፈታሉ፤ የሰላም በሮችን መከፈት ተከትሎም ሁሉም የሚሻው የዕድገት ጮራ ይፈነጥቃል።

(የሺሃሳብ አበራ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here