መፍትሔ ያልተገኘለት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ ድፍን አንድ ዓመት ሞልቶታል። እ.አ.አ ሚያዚያ 15 ቀን 2023 በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደተባባሰ ቀጥሏል። ሀገሪቱ በሁለት ስልጣን ፈላጊ ተፋላሚ ኃይሎች እየታመሰች ትገኛለች።
ላለፉት 12 ወራት በቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል። በሺህዎች የሚቆጠሩት ህይወታቸውን አጥተዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ተፈናቅለዋል፣ በተመሳሳይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ መረጃ ያሳያል።
እንደ ኢንተርናሽናል ክራይስስ መረጃ አሁን ላይ አብዛኛው የሱዳን ግዛቶች ፈርሰዋል። ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሀገሪቱን ለሁለት ከፍለዋታል። በጄኔራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመረው የሱዳን ጦር የሀገሪቱን የምዕራብ ክፍል ተቆጣጥሮታል። የመሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ጦር ደግሞ የምሥራቁን ክፍል ነው የተቆጣጠረው። ምንም እንኳ የሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የስልጣን ሽኩቻ የቆየ ነው ቢባልም እርቅ ለማውረድ እና የሲቪል የሽግግር መንግስት ለመመስረት እ.አ.አ በ2021 የሠላም ድርድር ጀምረው እንደ ነበር መረጃዎች አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ወደ ብሔራዊ ጦሩ ለማስገባት ቀነ ገደብ መቀመጡን ተከትሎ አል-ቡርሃን እና ሃምዳን ዳጋሎ ጦር ተማዘዋል። እ.አ.አ በ2019 የዑመር ሀሰን አልበሽርን መንግስት በመቃወም በጋራ ከስልጣኑ ካስወገዱት ከሁለት ዓመታት በኋላ ግንኙነታቸው ሻክሮ ሱዳንን ለእርስ በእርስ እልቂት እና ፍጅት ዳርገዋታል። ጦርነቱን ቀድሞ ያስጀመረው ማን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ ባይሆንም ጦሱ ግን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሱዳናውያን ተርፏል።
ሱዳን እ.አ.አ በ1956 ከቅኝ ግዛት ተላቃ ነፃነቷን ካገኝች በኋላ ይህ ዓይነት አስከፊ ችግር ገጥሟት አይውቅም። ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ በመሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው ጦር አብዛኛውን የካርቱምን ክፍል በመቆጣጠር ሲዋጋ እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል። እንደ አልጀዚራ መረጃ ሃምዳን ዳጋሎ ይዞታውን በካርቱም ካሰፋ በኋላ የሱዳንን ዋና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ወስዷል። የወሰደው የነዳጅ ማጣሪያም ሌላውን የሀገሪቱ ክፍል ለመቆጣጠር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ አግዞታል።
በወርሀ ጥቅምት እና ህዳር 2023 እ.አ.አ የዳርፉርን ምዕራባዊ ክልል መቆጣጠር ችሏል። ሳይውል ሳያድር ደግሞ በኮርዶፋን ክልል አዲስ ጥቃት በመክፈት በርካታ ሱዳናውያንን ለችግር ዳርጓል። ጦርነቱ በተፋፋመበት በገዚራ ግዛት የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን በመተው ተሰደዋል። በመሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች እና ግዛቶችን የማስተዳደር ፍላጎት ግን አልነበረውም። ይሁን እንጂ በጦር ኃይሎች የሚፈጸመው ግድያ፣ ፆታዊ ጥቃት እና ዝርፊያ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩትን ሱዳናውያን በማስቆጣት አል-ቡርሃንን እንዲደግፉ በር ከፍቷል።
በሃምዳን ዳጋሎ የማያቋርጥ ድብደባ የተፈጸመበት የአል-ቡርሃን ጦር በመጨረሻ አጻፋዊ ምላሽ ሰጥቷል። በኢራን ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮኖች) የታገዘ ጥቃት በመፈጸም የሱዳን ጦር የኦምዱርማንን ሰፊ ቦታዎች ድጋሚ መያዝ ችሏል። አሁንም በዚህ ግጭት ውስጥ የነበሩ ንጹሀን ለከፋ ችግር ተዳርገዋል። ከተሞች ወድመዋል፣ የጅምላ መፈናቀሎችም ተከስተዋል፣ የንግድ እንቅስቃሴ እና የግብርና ሥራ በመቆሙ የሀገር ውስጥ የምርት እጥረት አጋጥሟል። በዚህ ሳቢያም ሱዳን ለዜጎቿ የምድር ሲኦል ሆናለች።
ባለፉት 12 ወራት በቀጠለው የእርስ በእርስ ግጭት ከ14 ሺህ በላይ የሱዳናውያን ህይወትን ቀጥፏል። ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት የሀገሪቱ ዜጎች ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት ሴቶች እና ህፃናት ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት ሀገር ተሰደዋል። ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ ሲሆኑ 18 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ መረጃ ያሳያል።
በ2023 ዓ.ም ጥቅምት ወር ግጭቱ በዳርፉር መባባሱን ተከትሎ በህዳር ወር በቀን ከ3ሺህ በላይ ሱዳናውያን የደቡብ ሱዳንን ድንበር ያቋርጡ እንደነበር ተዘግቧል። መዳረሻቸውም ቻድ ውስጥ ወደ ሚገኝው የስደተኞች ጣቢያ ነበር። መካከለኛው አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳም ስደተኞችን ከተቀበሉ ሌሎች ሀገራት መካከል ይገኙበታል። ግጭቱ ያሳሰባት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሜሪካዊቷ ሲንዲ ማካኒ ለ16 ዓመታት ያህል የዘለቀው የዳርፉር ጦርነት በዓለማችን አስከፊ የነበረ ቢሆንም የሱዳን ሕዝብ ዕርዳታ ማግኘቱን ግን ታስታውሳለች። አሁን ግን የሱዳን ሕዝብ ተረስቷል ብላለች ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ።
መንግስታዊ ያልሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶችን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው በቀጣዮቹ ወራት 230 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት፣ ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ዕርዳታ ካላገኙ በርሃብ ህይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ጠቁሟል። ግጭቱ መባባሱ እና ውስብስብ ቢሮክራሲ መኖሩ ዕርዳታዎች ቶሎ እንዳይደርሱ አድርጓቸዋል።
የነዳጅ እና የወርቅ ሀብቷን ለመዝረፍ ያሰፈሰፉ የውጪ ኃይሎች በግጭቱ ተሳታፊ መሆናቸው የጦርነቱን መልክ በመቀየር በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት እንዳያገኝ አድርጎታል። ባለፉት አስር ዓመታት ከተካሄዱ አውዳሚ ጦርነቶች መካከል ይህ የሱዳን ጦርነት በቀዳሚነት ይቀመጣል። አል- ቡርሃን የሃምዳን ዳጋሎን ጦር ለመውጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የአጋሮቹ ጥምረት እየተማመነ ነው። ሳውዲ አረቢያ፣ ግብጽ እና ኢራን የሱዳንን ጦር ከሚደግፉት መካከል ይገኙበታል። ምንም እንኳ በተደጋጋሚ ከደሙ ንጹህ እንደሆኑ ቢናገሩም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እየደገፉ ናቸው በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ኤርትራ እና ኢትዮጵያም የፈጥኖ ደራሹን ኃይል የሚመራውን ሃምዳን ዳጋሎ ደጋፊ ናቸው፡፡ ሞስኮም በሱዳን በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት እጇን አስገብታለች ተብሏል። ገዳዩ የዋግነር ቡድን የሃምዳን ዳጋሎ ጦርን ይደግፋል በሚል አሜሪካ አቤቱታዋን አሰምታለች።
ዋሽንግተን በሱዳን የሚገኙት ወርቅ ቆፋሪ ሩሲያውያን ባለሀብቶች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ብቻ ሳይሆን ከዩክሬን ጋር እየተደረገ ላለው ጦርነትም ድጋፍ እያደርጉ ነው ስትል ክስ አቅርባለች። የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ባሳለፍነው መስከረም ወር ከጄኔራል አል- ቡርሃን ጋር በአየርላንድ በጋራ የፀጥታ ችግሮቻቸው ላይ ተወያይተው እንደነበር ይታወሳል። ፕሬዝደንት ዘለንስኪ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ድጋፍ የሚደረግላቸው ከሩሲያ መሆኑን ተናግሯል።
ዘለንስኪ ይህን ይበሉ እንጂ ዘ ዎል ስትሬት ጆርናል፣ ሲኤን ኤን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት የዩክሬን ተዋጊ ኃይሎችም በሱዳን ግዛት እንደሚገኙ ዘግቧል። ሰው አልባ አውሮፓላኖችን(ድሮኖችን) እና በምሽት መዋጋት የሚችሉበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የአል-ቡርሃንን ጦር እያገዙት እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት- ጦርነቱንም የውክልና ጦርነት ሲል ገልጾታል።
የእርስ በእርስ ጦርነቱን ለማስቆም እስካሁን አራት ያህል ስምምነቶች እና ውይይቶች ቢደረጉም አንዳቸውም ግን ለፍሬ በቅተው ለሱዳናውያን ዘላቂ እፎይታን አልሰጡም። እ.አ.አ ሚያዚያ 16 ቀን 2023 በሱዳን ጉዳይ ላይ የአረብ ሊግ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል። በተመሳሳይ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ደግሞ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፎ ነበር። ግንቦት 20 ቀን 2023 እ.አ.አ በጅዳ ውይይቱ ሰብአዊ ዕርዳታውን ለማሳለጥ የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ በሱዳን ጉዳይ ውይይት የተደረገው ሐምሌ 13 ቀን 2023 እ.አ.አ በግብጽ ካይሮ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።
አሁን ደግሞ አሜሪካ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ተፋላሚ ኃይሎች ተኩሳቸውን አቁመው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲነጋገሩ ድጋሚ አደራዳሪዎች ሆነዋል። የኢጋድ እና የተባበሩት መንግስታት ልዑክ አዲስ ተሿሚዎች ጠንካራ ድርድር እንዲደረግ ግፊት ያሳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል። አል-ቡርሃን እና ሃምዳን ዳጋሎ በቀጣይ ግንቦት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ለድርድር ለመቀመጥ ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል። አሜሪካ እና ሳውዲ አረቢያ ደግሞ የሠላም ድርድሩን የሚመሩት ሀገራት ናቸው።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአል-ቡርሃን ሠራዊት በጦር ሜዳ እያስመዘገበ ባለው ድል ምክንያት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ ፍቃደኛ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል። የግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከጅዳው ድርድር መገፋታቸው በሪያድ እና በአቡ ዳቢ መካከል ያለው ጥላቻ ሰፍቶ ቀጣናውን ይበልጥ እንዳይረብሸው ስጋትን አሳድሯል።
የሱዳንን ሕዝብ ለመታደግ ሚያዚያ 15 ቀን 2024 እ.አ.አ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የሰብአዊነት ኮንፍረንስ ተደርጓል። በኮንፍረንሱ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ የፈራረሰውን የሱዳን መንግስት ማቋቋም፣ ዜጎች ወደ ቤት ንብረታቸው እንዲመለሱ እና አስቸኳይ ስብአዊ ዕርዳታዎች እንዲደረጉ የሚሉ ሀሳቦች ተነስተው ምክክር ተደርጎባቸዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም