ከአርሴናል የተገፉት…

0
247

የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሴናል ከ20 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እየተፎካከረ ይገኛል። በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንዲቆይ ደግሞ የስፔናዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ ሚና ላቅ ያለ ነው። ዴቪድ ራያ ምንም እንኳ አልፎ አልፎ ስህተቶችን ቢሠራም በኤምሬትስ ካለፉ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች ተርታ ግን ይሰለፋል። ራያ ባሳለፍነው ክረምት ወራት ነበር ከብሬንትፎርድ አርሴናልን በውሰት ውል የተቀላቀለው።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ምን አልባት በዋንጫ ታጅቦ ዓመቱን የሚያጠናቅቅ ከሆነ ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩት የቡድን ተጫዋቾች መካከል አብሮ ስሙ ይነሳል። ግብ ጠባቂው ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በ14 ጨዋታዎች መረቡን አላስደፈረም። ይህ ቁጥራዊ መረጃም የፕሪሚየር ሊጉ ቀዳሚው ግብ ጠባቂ ያደርገዋል። ገና ከወዲሁ የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ እንደሚያጠናቅቅ ትልቅ ግምት አግኝቷል።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው እግሊዛዊው ግብ ጠባቂ አሮን ራምስዴል ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ ብዙ የመሰለፍ ዕድል አላገኘም። የ25 ዓመቱ እንግሊዛዊ በብሄራዊ ቡድኑ ያለውን ቦታ ላለማጣት ቀጣይ በሚከፈተው በክረምቱ የዝውውር ወቅት ወደ ሌላ ክለብ ያመራል ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታም ዴቪድ ራያ ኤምሬትስ ከደረሰ በኋላ ያለባቸው የግብ ጠባቂ ችግር እንደተቀረፈ ያምናሉ።

አርሴናል ኳስን ከኋላ መስርቶ ሲጫወት ራያ ከተጫዋቾች ጋር የሚያደርገው ቅብብል የተሻለ ነው። በዚህ ምክንያትም የመጀመሪያ ተመራጭ ለመሆን በቅቷል። አሮን ራምስዴልም ከአርሴናል ጋር ያለው እህል ውሃ እንዳበቃ እየተነገረ ይገኛል። ክለቡ አርሴናልም የመውጫ በሩን እንደሚከፍትለት ይጠበቃል።

አርሴናል ከግብ ጠባቂዎች ጋር በተያያዘ ያለው ታሪክ ደግሞ ምናልባት ራምስዴልን ይበልጥ ኤምሬትስን እንዲለቅ ይገፋፋዋል።ከዚህ በፊት በኤምሬትስ ተጠባባቂ ወንበርን ያሞቁ የነበሩ ግብ ጠባቂዎች አርሴናልን ለቀው አሁን ላይ የተሳካ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ። በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊጉ ብቻ አራት የቀድሞ የአርሴናል ግብ ጠባቂዎች  የክለቦቻቸው  ወሳኝ ተጫዋች ሆነዋል።

አርጀንቲናዊው ግብ ጠባቂ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ በወጣትነቱ ነበር ኤምሬትስ የደረሰው። የ31 ዓመቱ ግብ ጠባቂ በ12 ዓመታት የኤምሬትስ ቆይታው 38 ጨዋታዎችን አድርጓል። በ16 ጨዋታዎች ደግሞ ግብ ሳይቆጠርበት ከሜዳ ወጥቷል። አርሴናል ተጫዋቹን ለሰባት የተለያዩ ክለቦች በውሰት ውል ከሰጠው በኋላ በመጨረሻ ለአስቶንቪላ በ20 ሚሊዮን ፓውንድ አሳልፎ ሽጦታል።

በ2022 እ.አ.አ ቪላ ፓርክ ከደረሰ በኋላ ከምርጥ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል። አርጀንቲናዊው ግብ ጠባቂ በመጀመሪያ አንድ መቶ የአስቶንቪላ ጨዋታው በ34 ጨዋታዎች መረቡን ባለማስደፈር የክለቡ ባለክብረወሰን መሆን ችሏል።

ማርቲኔዝ አርሴናልን ለቆ ቪላ ፓርክ ከደረሰ በኋላ ለአርጀንቲና ወሳኝ ግብ ጠባቂ በመሆን በ2021 ከሀገሩ ጋር የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን አሳክቷል። በ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫም ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ዋንጫውን አንስቷል። በግዙፉ የእግር ኳስ መድረክ የውድድሩ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማትንም መውሰዱ ይታወሳል። በውድድር ዓመቱ ባሳየው ድንቅ ብቃት የ2022 ምርጥ የፊፋ ግብ ጠባቂ ተብሎ በመመረጥ የያሺን ዋንጫ ሽልማትን ወስዷል። በዚህ ዓመትም ቢሆን አስቶንቪላ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት እያደረገ ባለው ትግል የግብ ጠባቂው ሚና የጎላ ነው። ዘንድሮ ካደረጋቸው 32  ጨዋታዎች በስምንቱ ግብ ሳይቆጠርበት ከሜዳ መውጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ማርቲኔዝ ለአውሮፓ ውድድሮች ርቆ የነበረውን አስቶንቪላ የግብ በር እየጠበቀ በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ለግማሽ ፍጻሜ አብቅቷቸዋል:: አሁን ላይ የእንግሊዝ ክለቦች ከአውሮፓ መድረክ ተጠራርገው ሲወጡ አስቶንቪላ ብቻ እንግሊዝን ወክሎ እየተፋለመ መሆኑም የሚታወቅ ነው::

ሌላው በኤምሬትስ ተጠባባቂ ወንበርን አላሞቅም በማለት ክለቡን ለቆ የወጣው እና ድንቅ ግብ ጠባቂ መሆኑን በፉልሀም ያስመሰከረው በርንድ ሌኖ ነው። አርሴናል ሌኖን በ2018 እ.አ.አ ነበር ከባየር ሊቨርኩሰን ያስፈረመው። በአራት ዓመታት የኤምሬትስ ቆይታው በአንድ መቶ አንድ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። ከ2022 እ.አ.አ ጀምሮ ደግሞ በሌላኛው የለንደን ክለብ ፉልሀም ቤት ይገኛል።

በርንድ ሌኖ ፉልሀምን በስምንት ሚሊዮን ፓውንድ ነበር የተቀላቀለው። በዚህ ዓመትም በፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ከሚባሉ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ ነው። ካደረጋቸው 33 ጨዋታዎች በዘጠኙ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣቱን የፕሪሚየር ሊጉ ድረገጽ መረጃ አመልክቷል። ከቀድሞው የቡድን አጋሩ ፒትር ቼክ በቅርብ ሆኖ መማሩ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዳገዘው መናገሩን ዘሰን አስነብቧል። የአሮን ራምስዴል ኤምሬትስ መድረስ ጀርመናዊውን ሌኖ ሰሜን ለንደንን ለቆ እንዲወጣ እንዳስገደደው ጭምር ተዘግቧል።

ፖላንዳዊው ግብ ጠባቂ ሉካስ ፋቢያንስኪም ከ2007 እስከ 2014 እ.አ.አ በሰሜን ለንደኑ ክለብ ማሳለፉ አይዘነጋም። በሰባት ዓመታት ቆይታው 32 ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያደረገው። በመጨረሻው ዓመት የአርሴናል ቆይታው ከክለቡ ጋር የኤፍኤ ዋንጫን ማንሳቱ የሚታወስ ነው። ሀገሩን ፖላንድም ከ2006 እስከ 2021 እ.አ.አ አገልግሏል። ከአስር ዓመት በፊት ፋቢያንስኪ ከአርሴናል ጋር ያለው የውል ስምምነት በመጠናቀቁ በወቅቱ ፕሪሚየር ሊግ ይጫወት የነበረውን ስዋንሲ ሲቲ ተቀላቅሏል። ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ በ2018 ለንደን ስቴዲየም በመድረስ ዌስትሀምን እያገለገለ ይገኛል።

ፋቢያንስኪ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ለዌስትሀም 182 ጨዋታዎችን አከናውኗል። በያዝነው የውድድር ዘመን ግን በተለያየ ምክንያት ብዙ የመሰለፍ ዕድል አላገኘም፤ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ብቻ ያከናወነ ሲሆን በአንዱ ብቻ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱ በታሪክ ማህደሩ ተመዝግቧል። ዌስትሀም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎን ለማግኘት በሚያደርገው ፉክክር የግብ ጠባቂው የፋቢያንስኪ ሚና የማይናቅ አለመሆኑን ቁጥሮች ይናገራሉ።

አሜሪካዊው ግብ ጠባቂ ማት ተርነርም በኤምሬትስ አንድ ዓመት ማሳለፉ አይዘነጋም:: ተርነር በ2022 እ.አ.አ ከሜጀር ሊግ ሶከሩ ክለብ ኒው ኢንግላንድ ሪቮሊሽን ነበር አርሴናልን የተቀላቀለው:: ይሁን እንጂ በአንድ ዓመት የአርሴናል ቆይታው አንድም ጊዜ በነጥብ ጨዋታዎች ሳይሰለፍ ወደ ኖቲንግሀም ፎረሰት አቅንቷል::

በወዳጅነት ጨዋታዎች ባሳየው ምርጥ አቋም ግን ከአሰልጣኙ ሚኬል አርቴታ ሳይቀር ሙገሳን አግኝቶ እንደነበር አይዘነጋም:: የበርንድ ሌኖ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ሰሜን ለንደን የደረሰው ተርነር ራምስዴል ክለቡን ሲቀላቀል ልክ እንደ ሌኖ ሁሉ እርሱም አርሴናልን ለመልቀቅ ተገዷል::

በአርሴናል ቤት ካለፉ ባለተሰጥኦ ግብ ጠባቂዎች መካከል ሌላኛው ፖላንዳዊ ዎቺ ሽዝኒ አንዱ ነው። በ16 ዓመቱ ከሀገሩ ፖላንድ የአርሴናል ወጣት ቡድንን የተቀላቀለው ሽዝኒ የዋናውን ቡድን ሰብሮ ለመግባት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። በ2009 እስከ 2017 እ.አ.አ የአርሴናልን ዋናው ቡድንን አገልግሏል። የማይጠበቁ ኳሶችን በማዳን እና ቡድኑን በማበረታት የሚታወቀው ሽዝኒ እ.አ.አ. በ2013/14 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ መመረጡ አይዘነጋም።

ነገር ግን በ2015 እ.አ.አ የፒተር ቼክ ኤምሬትስ መድረስን ተከትሎ በውሰት ውል ክለቡን ሊለቅ ተገዷል። የጣሊያኑን ክለብ ሮማን ለሁለት ዓመታት ያህል በውሰት ውል ካገለገለ በኋላ በ2017 እ.አ.አ. በቋሚ ዝውውር ጁቬንቱስን መቀላቀል ችሏል።

ሽዝኒ በአርሴናል የእግር ኳስ ህይወቱ 181 ጨዋታዎችን ሲያደርግ በ72 ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረበትም። ጂያንሉንጂ ቡፎን ከአሮጊቶቹ ቤት መሰናበቱን ተከትሎ ነው ሽዝኒ ቱሪን የደረሰው። ከጁቬንቱስ ጋር የጣሊያን ሴሪኤ እና ሌሎችንም ዋንጫዎች ያነሳ ሲሆን የሴሪኤው ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማትንም አሳክቷል። ሀገሩ ፖላንድ የአውሮፓ፣ የዓለም ዋንጫ እንድትሳተፍ ያደረገው አስተዋጽኦም ላቅ ያለ ነው። በዚህ ዓመት በሴሪኤው 29 ጨዋታዎችን ሲያደርግ በ13ቱ ግብ አልተቆጠረበትም።

ኮሎምቢያዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ኦስፒናም በኤምሬትስ አራት ዓመታትን ተጫውቶ አሳልፏል። 70 ጨዋታዎችን አድርጎ በ37ቱ መረቡን አለማስደፈሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ኦስፒና በደጋፊዎቹ ዘንድ እምነት ከሚጣልባቸው ተጫዋቾች መካክል አንዱ መሆን ችሎ ነበር።

የፒተር ቼክ ከቼልሲ ወደ አርሴናል መምጣት ግን ብዙ የመሰለፍ ዕድል እንዳያገኝ ምክንያት ሆኗል። በመጨረሻም ልክ እንደ ሼዝኒ ክለቡን ለመልቀቅ ተገዷል። ፍጹም ቅጣት ምት በማዳን የሚታወቀው ኦስፒና ሁለት የኤፍ ኤ እና የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫ ካሳካ በኋላ በ2019 በፈረንጆች የኔፕልሱን ክለብ ናፖሊን በውሰት ውል ተቀላቅሏል። ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ ናፖሊን በመልቀቅ ወደ ሳውዲ ተጉዞ አልናስርን እያገለገለ ይገኛል።

ታዲያ አሮን ራምስዴልም   በአርሴናል ቤት ትኩረት ተነፍገው ክለቡን ከለቀቁ በኋላ በሌሎች ክለቦች  ምርጥ ብቃታቸውን ያሳዩትን ከላይ የጠቀስናቸውን ግብ ጠባቂዎች ፈለግ ይከታላል? ወይስ በኤምሬትስ ይቆያል? ጥያቄው ወደ ፊት ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።

ዘሰን እና የፕሪሚየር ሊጉ ድረገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here