“ዲያመንድ ሊግ” እና ኢትዮጵያውያን

0
175

በአትሌቲክሱ ዘርፍ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የግል ውድድሮች መካከል አንዱ ነው። የመድረኩ አሸናፊ አትሌቶች ዳጎስ ያለ ሽልማት የሚያገኙበት ጭምር ውድድር ነው- የዋንዳ ዲያመንድ ሊግ ውድድር።  ይህ ግዙፍ የአትሌቲክስ መድረክ በተለያዩ ከተሞች የሚደረግ የአንድ ቀን የዙር  ውድድር ነው።

የ2024ቱ የዋንዳ ዲያመንድ ሊግ ውድድር በቻይና ዣሚን ከተማ ነው የተጀመረው። የሁለተኛው ዙር ውድድርም በዚያው በቻይና ሻንጋይ ከተማ ነው የተደረገው። ውድድሩ ከዚህ በፊት ከግንቦት ወር ጀምሮ እስከ መስከረም ይደረግ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ባልተለመደ መልኩ ቀደም ብሎ በያዝነው ሚያዚያ ወር ተጀምሯል።

በዚህ መድረክ ከወትሮው በተለየ አትሌቶች በ15 ዙሮች የሚፎካከሩ ይሆናል። ከአራቱም የዓለም ማዕዘን የተውጣጡ አትሌቶች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ነው እየተፎካከሩ ያሉት። ከእነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚገኙበት ሲሆን ባለፉት ሁለት ዙሮችም ድል ቀንቷቸዋል።

በዣሚን በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ውድድር በሴቶች አንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል። የባለፈው ዓመት የመድረኩ የአምስት ሺህ ሜትር ርቀት አሸናፊዋ እና የዲያመንድ ዋንጫ ተሸላሚዋ ጉዳፍ ፀጋዬ ዘንድሮም በአንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀት የመጀመሪያውን ዙር አሸንፋለች።

የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ሯጯ ጉዳፍ ርቀቱን ስታሸንፍ የተለያዩ ክብረ ወሰኖችን በማሻሻል ጭምር ነው። ርቀቱን ለመጨረስ የፈጀባት ጊዜም ሦስት ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ ከ30 ማይክሮ ሴኮንድ ነው። ጉዳፍ በውድድሩ መጨረሻ በዚህ ርቀት አሸናፊ በመሆን የዲያመንዱን ዋንጫ ይወስዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች በቀዳሚነት ትቀመጣለች። ብርቄ ኃየሎም፣ ወርቅነሽ መሰለ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በወንዶች አምስት ሺህ ሜትር ለሜቻ ግርማ ውድድሩን በበላይነት አጠናቋል። የሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል ሯጩ ለሜቻ አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ረጅም ርቀት አዙሯል። በዚህ ርቀትም ገና ከወዲሁ ስኬታማ እንደሚሆን ፍንጭ ሰጥቷል። ለሜቻ ፉክክሩን በበላይነት ማጠናቀቁ  አትሌቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ያመለክታል።

በዚሁ ርቀት ይሁኔ አዲሱ አምስተኛ ሆኖ ሲጨርስ ኩማ ግርማ ደግሞ ስምንተኛ ሆኖ ነው ያጠናቀቀው። የሴቶች ሦስት ሺህ ሜትር መሰናክልም በመጀመሪያው ዙር ነበር የተከናወነው። ኢትዮጵያውያኑ ሎሚ ሙለታ እና ፍሬህይወት ገሰሰ በቅደም ተከተል አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃን  ይዘው ነው ያጠናቀቁት።

በሻንጋይ በተደረገው በሁለተኛው ዙር የዲያመንድ ሊግ ውድድርም በሴቶች አምስት ሺህ ሜትር ርቀት ኢትዮጵያውያኑ ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው ገብተዋል። መቅደስ ዓለምሸት ፉክክሩን በበላይነት ያጠናቀቀች ሲሆን 14 ደቂቃ ከ36 ሴኮንድ ከ70 ማይክሮ ሴኮንድ ርቀቱን ለመጨረስ የፈጀባት ጊዜ ነው። አያል ዳኛቸው ሁለተኛ፣ ለተሰንበት ግደይ ሦስተኛ እና ውብርስት   አስቻለ አራተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች። አሳየች አይቸው ደግሞ ስድስተኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው።

በተመሳሳይ በወንዶች አምስት ሺህ ሜትር የቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊው ሰለሞን ባረጋ የውድድሩን ክብረወሰን በመስበር ጭምር አሸንፏል። 12 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ65 ማይክሮ ሴኮንድ ሰለሞን ርቀቱን ለመጨረስ የወሰደበት ጊዜ ነው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ቢኒያም መሀሪ ደግሞ የራሱን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል። ኩማ ግርማ አራተኛ፣ ንብረት ክንዴ ደግሞ ስምንተኛ ሆነው ነው ያጠናቀቁት።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ መድረክ በሁለቱም ፆታዎች ውጤት የሚያመጡበት ውድድር የአምስት ሺህ ሜትር ርቀት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ታዲያ ዘንድሮም ገና ከወዲሁ በሁለቱም ፆታዎች ውጤታማ መሆናቸውን እያስመሰከሩ ናቸው። ሀገራችን በዋንዳ ዲያመንድ ሊግ መሳተፍ የጀመረችው በ2010 እ.አ.አ እንደገና በአዲስ መልኩ በተጀመረበት ወቅት ነው።

በወቅቱ በአምስት ሺህ ሜትር ርቀት የተሳተፈው ኢማና መርጊያ በዋንዳ ዲያመንድ ሊግ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አሸናፊ መሆን ችሏል። የቀድሞው አትሌት ከአንድ ዓመት በኋላም በተመሳሳይ ርቀት በተከታታይ አሸናፊ የሆነ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጭምር ነው።

የኢማና መርጊያን ፈለግ በመከተል ሙሀመድ አማንም በ2012 እ.አ.አ 800 ሜትር ርቀት አሸናፊ በመሆን የዲያመንድ ዋንጫውን ወስዷል። ሙሀመድ አማን በዲያመንድ ሊጉ በ800 ሜትር  ውጤታማ የሆነ ብቸኛው አትሌት ነው። ሀገራችን በምትታወቅበት የአምስት ሺህ ሜትር ርቀት ግን በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ በመድረኩ አሸናፊ ሆነዋል። እ.አ.አ በ2015 ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ በ2016 ሀጎስ ገብረ ህይወት፣ በ2018 ሰለሞን ባረጋ እና በ2021 በሪሁ አረጋዊ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች ናቸው።

በሴቶች አበባ አረጋዊ ዲያመንድ ሊጉን ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊት ናት። በ2012 እ.አ.አ አንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀትን ማሸነፏ ያታሪክ ማህደሯ ያሳያል። በአምስት ሺህ ሜትር በአውሮፓውያን የጊዜ ቀመር አቆጣጠር በ2013 መሰረት ደፋር፣ በ2015 ገንዘቤ ዲባባ፣ በ2016 አልማዝ አያና እና በ2023 ጉዳፍ ፀጋዬ ማሸነፋቸውን ታሪክ ይነግረናል።

በሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል ደግሞ ህይወት አያሌው በ2014 እ.አ.አ እና ወርቅውሃ ጌታቸው በ2022ቱ የዲያመንድ ሊግ ውድድር ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው። በዲያመንድ ሊጉ ኢትዮጵያውያን መሳተፍ ከጀመሩበት ባለፉት 14 ዓመታት በረጅም እና በመካከለኛ ርቀት በየ ዓመቱ ቢያንስ አንድ ኢትዮጵያዊ አትሌት አሸናፊ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

መድረኩ የግል ውድድር በመሆኑ በርካታ አዳዲስ አትሌቶች ወደ ፊት በመምጣት ራሳቸውን የሚያሳዩበት እና የሚጠቅሙበት ጭምር ነው። የቀድሞው ጎልደድን ሊግ የአሁኑ የዋንዳ ዲያመንድ ሊግ እ.አ.አ በ1998 ነው የተጀመረው። በተለያዩ ሰባት የአውሮፓ ከተሞች በመም እና በሜዳ ተግባራት መጀመሩን ጭምር የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ መረጃ ያስነብባል። እንደ ዓለም አትሌክቲክስ ድረገጽ መረጃ ለ12 ዓመታት ያህል በዚህ መንገድ ተከናውኗል። እ.አ.አ ከ2010 ጀምሮ  የስያሜ ለውጥ በማድረግ በአዲስ ቅርጽ ውድድሩ እየተከናወነ ዘንድሮ ላይ ደርሷል።

የዲያመንድ ሊግ ውድድር ከቀድሞው ጎልደን ሊግ በስም ብቻ ሳይሆን በዓላማም ይለያያል። ጎልደን ሊጉ የተጀመረው በአትሌቲክሱ ዘርፍ አውሮፓውያን አትሌቶችን ለማበረታት ታስቦ እንደ ተጀመረ ታሪክ ያስረዳል። ዲያመንድ ሊጉ ግን በአራቱም የዓለም ማዕዘን የሚገኙ ሁሉንም አትሌቶች ያሳትፋል። የዲያመንድ ሊጉ ውጤት አያያዝ ከሌሎች መድረኮች የተለየ ሲሆን በየ ዙሩ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ውጤት እና ነጥብ በመጨረሻ አሸናፊ የሆኑትን ይለያል።

በአንድ ዙር አንደኛ ደረጃን ይዞ ለሚያጠናቅቅ አትሌት ስምንት ነጥቦችን ያገኛል። ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለሚጨርስ ደግሞ ሰባት ነጥቦችን ያገኛል፤ ሦስተኛ ደረጃን ለሚይዝ ስድስት ነጥቦችን ያገኛል። በዚህ መልኩ እየቀነሰ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ለሚጨርሱ ስፖርተኞች ነጥብ የሚያገኙ ይሆናል። በዚህ መሰረትም በሁሉም ዙሮች ከፍተኛ ነጥብ የሚያስመዘግቡ አትሌቶች ሽልማት ይበረከትላቸዋል። በየ ስፖርት ዓይነቱ ውድድሩን በበላይነት ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች የ30 ሺህ ዶላር ገንዘብ እና የዲያመንድ ዋንጫ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ለሚጨርሱ 12ሺህ ዶላር፣ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ የሰባት ሺህ ዶላር ሽልማትን ያገኛሉ። እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁት አትሌቶች የሽልማቱ ተቋዳሽ ይሆናሉ። በተጨማሪም በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ያለምንም ማጣሪያ እንንዲሳተፉ ፈቃድ (ዋይልድ ካርድ ) ይሰጣቸዋል።

በዘንድሮው መድረክ ገና ከወዲሁ አስደናቂ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውድድሩ መጨረሻ ምን ዓይነት ውጤት ያስመዘግባሉ የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል። ሦስተኛው ዙር የዲያመንድ ሊግ ውድድር እ.አ.አ የፊታችን ግንቦት 10 በኳታር ዱሃ የሚከናወን ይሆናል። አጠቃላይ ውድድሩ ግን 15ኛ በሆነቸው ቤልጂየም ብራስልስ ከተማ የፊታችን መስከረም ወር ይጠናቀቃል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here