ያቤሎ ብሔራዊ ፓርክ

0
256

 

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በ565 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ውስጥ የሚገኝ ማራኪ መዳረሻ ነው፡፡ የፓርኩ ስፋት ሁለት ሺህ አምስት መቶ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ በመልካምድራዊ አቀማመጡም ዝቅተኛው 1 ሺህ 400 ፣ ከፍተኛው 2000 ሜትር ከመሬት ወለል በላይ ሲሆን  አማካዩም 1 ሺህ 700 ሜትር ነው።

የአየር ንብረቱ መካከለኛ ወይም ደጋማ ነው። ዓመታዊ የሙቀት መጠኑ ዝቅተኛው 13 ከፍተኛው 25 ዲግሪ  ሴንቲግሬድ፣ አማካዩ 19 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ተለክቷል፡፡

የያቤሎ አካባቢ አማካይ ዓመታዊ የዝናብ መጠኑ 700 ሚሊ ሜትር ሲሆን ዝናብ የሚያገኘው በሚያዚያ እና ግንቦት ወራት ነው።

በፓርኩ ከፍተኛ መልካምድር አቀማመጥ ባላቸው ጉብታዎች ቀደም ብሎ የጥድ ዛፍ በርከት ብሎ ይታይ ነበር፤ ዛሬ ያ አይታይም፡፡

ያቤሎ ብሔራዊ ፓርክ የበርካታ አእዋፍ ዝርያዎች፣ የአጥቢ እንስሳት እና የዱር አራዊት መሸሸጊያ ነው፡፡  210 የአእዋፍት ዝርያዎች ተመዝግበዋል። በቀጣናዉ ግርማ ማገስ ካላቸው አእዋፍ ሰጐን ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም፡፡

ከአጥቢ እንስሳት የሜዳ አህያ፣ ሚዳቋ በፓርኩ ክልል በርከት ብለው ከሚታዩት መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

የያቤሎ ብሔራዊ ፓርክ በአብዛኛው በደን መጨፍጨፍ የተጐዳ ቀጣና ነው፡፡ ከዱር እንስሳቱም በሕገወጥ አደን ሰጐን እና አነር በእጅጉ ዝርያቸው መመናመኑን ነው የድረ ገፆች ጽሑፍ ያስነበበው፡፡

ፓርኩ ቀናትን ቆይቶ ለመጐብኘት ድንኳን የተዘረጋባቸው ጣቢያዎች አሉት፡፡ ጣቢያዎቹ ድንቅ ምቹ የዕይታ አማራጭ እና በቅርበት ለመመልከት ማስቻልን ታላሚ አድርገው ነው የተዘጋጁት፡፡

ጐብኚዎች በፓርኩ ክልል አርፈው በየድንኳኖቹ ተቀምጠው እና ተኝተው የዱር እንስሳትን እንቅስቃሴ የአእዋፍን ጥኡም ዝማሬ መስማት ያስችላቸዋል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኢትዮጵያን ዋይልድ ላይፍ እና ኦል አፍሪካን ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here