አስጊው የጠፈር ላይ ስብርባሪ

0
178

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ከተማ የግለሰብን መኖሪያ ቤት ጣሪያ ቀዶ የገባው ሰባት መቶ ግራም የሚመዝን ቁስ የጠፈር ላይ ስብርባሪ መሆኑን የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ማዕከል /ናሳ/ ማረጋገጡን ያሁ ድረገጽ አስነብቧል::

መጋቢት ወር 2016 ዓ.ም መጀመሪያ ምንነቱ ያልታወቀ ብረት የፍሎሪዳ ኗሪውን አሌሀንድሮ ኦቴሮ መኖሪያ ቤት ጣሪያ ቀዶ መግባቱን ድረ ገፆች አስነብበዋል:: ቁሱ ምን እንደሆነ አልተለየም። ከየት እንደተወረወረ በውል አልታወቀም።  በሰው ላይ  አደጋ አለማድረሱም ተገልጿል።

የጠፈር መርምር ማዕከሉ በሰበሰበው ማስረጃ ቁሱ በመጀመሪያ ላይ በ2021 እ.አ.አ ከምህዋር መውጫ ጣቢያ የተወረወረ አሮጌ ባትሪ ወይም የኃይል ቋት ቅሪት ሊሆን እንደሚችል የሰጠው ቅድመ ግምት በናሙና ፍተሻ ትክክል መሆኑን አረጋግጧል::

ማዕከሉ ቁሱ 700 ግራም ክብደት እንዲሁም 10 ሴንቲ ሜትር ርዝመት የብረት እና “ኢንኮኔል” ቅጥይ መሆኑንም ነው ያስታወቀው::

የምርምር ማዕከሉ ስብርባሪ ቁሱ በከባቢ ዓየር ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዴት ሳይሰባበር እንደቀረ ለማወቅ ምርምሩን ለመቀጠል ማቀዱንም ይፋ አድርጓል:: ውጤቱን መነሻ በማድረግም ወደፊት የሚሰሩ የጠፈር መንኩራኩሮችን ለማሻሻል እንደሚሠራ ነው ማዕከሉ ያስታወቀው::

“ARS technica” የተሰኘ የዜና ማሰራጫ ባወጣው ዘገባ  ስብርባሪው የጃፓን የጠፈር ምምር ተቋም ከሚገለገልባቸው ባትሪዎች አሰራር ጋር የሚዛመድ መሆኑን አመላክቷል::

ከጠፈር የተወረወሩ ስብርባሪዎች ባለፈው 2022 እ.አ.አ በአውስትራሊያ የበግ  እርባታ ጣቢያ ላይ ወድቀው ነበር። በቅርቡም ቻይና ከአገልግሎት ውጪ የሆነ የጠፈር መንኩራኩር ወደመሬት እንዲወረወር ማድረጓን በመጥቀስ አብነቶችን አስነብቧል – ድረ ገጹ::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here