የላቲን ነፃ አውጭ

0
213

“የላቲን ጆርጅ ዋሽንግተን” ይሉታል። በቬንዙዌላ፣ ኮሎምቢያ፣ በኢኳዶር፣ በፓናማ፣ ፔሩ እና በቦሊቪያ እንደ ብሔራዊ ጀግናቸው ይቆጥሩታል። ለላቲን ሀገራት ውህደት ሕይወቱን የታገለ አብዮተኛ፣ ጀግና የጦር መሪ፣ ፖለቲከኛ ነበር። ሲሞን ጆሴፈስ አንቶኒዮ ዲ ላ ሳንቲሲማ ትሪንዳድ ቦሊቫር  ፕላሲዮስ ፖንቴ ብላንኮ ይባላል።  ወይም ደግሞ ነፃ አውጪው ሲሞን ቦሊቫር ይባላል።

ላ ፑብላ ዲ ቦሊቫር ከተሰኘች አንድ አነስተኛ የስፔን መንደር ነው የዘር ሀረጉ የሚመዘዘው። አባቱ ከካስቴሉ ንጉሥ ፈርናንዶ 3ኛ እንዲሁም ከሳቮይ መስፍን አሜዶ 4ኛ የሩቅ ዝምድና አላቸው። በወንድ ወገን ደግሞ ከ ዲ አርዳንዛ ቤተሰብ ነው የመጣው።

ስፔን አብዛኛውን የላቲን አሜሪካ የቅኝ ግዛት ስታቋቁም፣ የሲሞን ቦሊቫር ቤተሰብ የስፔን መንግሥት ታማኝ በመሆን ወደ ላቲን በማምራት በ17ኛው ክፍለ ዘመን ገደማ በቬንዙዌላ ላይ ሰፈሩ።

በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ ከሚጠቀሱ ቀደምት መስራቾች መካከል አንዱ የቦሊቫር ቤተሰብ ነው። እንደ መስራችነታቸው ታዲያ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ የመሪነትን ክብር ተቀዳጅተዋል። አባቱና ዘመድ አዝማዱ በርካታ ሀብት ያካበቱ፣ የሰፋፊ ርስት ባላባቶች ነበሩ። በካራካስ የሚገኙት የሸንኮራ ሰፋፊ ማሳዎች እና የመዳብ ማእድን ቁፋሮ ቦታዎች የቦሊቫር ቤተሰብ ንብረት ነበሩ።

በ1778 ዓ.ም አባቱ ዩአን ቪሴንቴ ቦሊቫር ይ ፓንቴ እና በ1784 ዓ.ም የእናቱ ማሪያ ዲ ላ ኮንሰብሲዮን ፓላስየስ ይ ብላንኮ ያለ ግዜያቸው መሞታቸውን ተከትሎ የ16 ዓመት ታዳጊው ሲሞን ቦሊቫር ትምህርቱን ለመጨረስ ወደ ስፔን እንዳመራ ታሪኩ ያስረዳል። በዚያም ማርቆስ ዴል ቶሮ ከተባለ የካራካስ ቤተሰብ ወገን የሆነችውን ሚስቱን ማሪያ ቴራሳ ሮደሪጌዝ ዴል ቶሮንቶ አላይስ ከተባለች ወይዘሮ ጋር በ1794 ዓ.ም ተጋባ።

በኋላም ሚስቱን ይዞ ወደ ቬንዙዌላ ተመለሰ። ይሁን እንጂ ከስምንት ወር በኋላ የሚስቱ ጤና በመቃወሱ ገና በጧቱ በሞት የተለየችው። ከወላጆቹ ሀዘን ያፅናናችው ሚስቱም ስትሞት የቦሊቫር ሀዘን መሪር ሆነ። ከዚህ ከባድ ሀዘን ገለል ብሎ መቆየት ሳይሻል እንደማይቀር የተሰማው ቦሊቫር ወደ አውሮፓ በመመለስ በስፔን ቆይታ አደረገ።

በ1800 ዓ.ም የፈረንሳዩ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ ስፔንን ወረረ። በዚህ ታሪካዊ ክስተት ነበር የላቲን አሜሪካ የነፃነት እንቅስቃሴ የጀመረው። ናፖሊዮን የስፔን ንጉሥ ከያዘ በኋላ በስፔን እና ቅኝ ግዛቶቿ ላይ የገዛ ወንድሙን ጆሴፍ ቦናፓርቴን ሾመ።  የናፖሊዮን እርምጃ የስፔንን ሕዝብ በማስቆጣቱ በመላዋ ስፔን አመፅ ተቀጣጠለ። በተለያዩ ከተሞችም ወታደራዊ ጁንታዎች ፈነዱ።

ናፖሊዮን  የስፔን ቅኝ ግዛቶችን ድጋፍ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ አለመሳካቱ ሌላው ውድቀቱ ነበር። አንዳንድ የላቲን ሀገሮች የስፔንን ፈለግ በመከተል ከስልጣን በተወገደው የስፔን ንጉሥ ስም የሚመራ ወታደራዊ ቡድኖችን ለማቋቋም ፈለጉ። ለበርካታ ስፔናውያን ሰፋሪዎች ግን እነዚህ አጋጣሚዎች ከስፔን ጋር ያላቸውን ትስስር የማቋረጥ እድል መኖሩን የተገነዘቡበት ሁኔታ ተፈጠረ።

ሲሞን ቦሊቨር ነገሮች በእንዲህ እያሉ በ1800 ዓ.ም ከስፔን ወደ ቬንዝዌላ ተመለሰ። ብዙም ሳይቆይ ሲሞን ቦሊቨር ለብዙ አመፃች ምክንያት የሆነውን በመጨረሻም ነፃነት ያሳካውን የካራካስ አርበኞች ማኅበረሰብን ተቀላቀለ እና መሪ ሆነ።

በሚያዚያ 11 ቀን 1802 ዓ.ም ላይ የስፔናውያን አስተዳደር በይፋ ስልጣኑን ተከለከለ እና ከቬንዙዌላ ተወገደ። ወታደራዊው አማፂ ቡድንም ስልጣን ያዘ። የካራካስ አማፂ ቡድን ሲመሰረትም ቦሊቨር የኮሎኔልነት ማዕረግ አገኘ እና ወደ እንግሊዝ የሚላከው የዲፕሎማሲ ልዑክ አካል ሆኖ ተመረጠ። ልዑኩን እየመራ የሄደው ቦሊቫር በሐምሌ ወር ለንደን ደረሰ። የተሰጠው ተልዕኮ የአብዮታዊ ቅኝ ተገዥዎችን መከራ ለእንግሊዝ መንግሥት ለማስረዳት፣ ለዚህ ደግሞ እውቅና ለመጠየቅ እና የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ድጋፎች ለማግኘት ነበር። ድርድሩ አልተሳካም።

በዚሁ ዓመት ሲሞን ቦሊቫር ከእንግሊዝ ወደ ቬንዝዌላ ተመለሰ። በመጋቢት 1804 ዓ.ም የትውልድ ሀገሩ መዲና ካራካስ ለ10ሺዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት በሆነ በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመታች። ጉዳቱ ከካራካስ ብቻ በመከሰቱ ከፈጣሪ ቁጣ ጋር በማያያዝ ኅብረተሰቡ የነፃነት ተዋጊዎቹን ወደ ማውገዝ ገባ።

የስፔን ቅኝ ገዢ ሰራዊት የጦር አዛዥ ዩአን ዶሚንጎ ዲ ሞንቫርድ ይህን እንደ ጥሩ አጋጣሚ መጠቀም የቬንዝዌላን ሪፐብሊክ በድጋሜ በቀላሉ ተቆጣጠረ። በዚህ ወቅት የሪፐብሊኳ ፕሬዚደንት ፍራንሲስ ዲ ሚራንዳ ለስፔን እጅ መስጠቱ ተሰማ።

ሲሞን ቦሊቫር በወቅቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ጠቀሜታ ባላት የወደብ ከተማዋ ፖርቶ ካቤሎ መሽጎ ነበር። ነገር ግን እየገፋ የመጣውን የስፔን ኃይል መቋቋም ስላልቻለ ቦሊቫር ራሱን እና ሰራዊቱን በሕይወት ለማስመለጥ  ተገደደ።

ትግሉን ለመቀጠል ቦሊቫር ወደ ኒው ግራናዳዋ ካርታጌና ተሰደደ። በዚህ ወቅት ነበር ቦሊቫር ዲ ካርታጌና የተሰኘ ማኒፌስቶውን የፃፈው። በማኒፌስቶውም ለመጀመሪያው የቬንዙዌላ ሪፐብሊክ መፍረስ ምክንያት የጠንካራ መንግሥት አለመኖር መሆኑን ያስቀመጠበት እና ስፔንን ከላቲን አሜሪካ ለማስወገድ አንድ የተባበረ አብዮታዊ ትግል እንዲፈጠር ጥሪ አቀረበ።

በኒው ግሪናዳ አርበኞች በሚያገኘው ድጋፍ እየታገዘ ቦሊቫር ቬንዙዌላን ዳግም በእጁ ለማስገባት ተንቀሳቀሰ። እልህ አስጨራሽ በሆነ የውጊያ ዘመቻ የስፔን ታማኞችን በስድስት የውጊያ አውዶች ደመሰሰ እና በ1805 ዓ.ም ሐምሌ መጨረሻ ላይ ካራካስ በድል አድራጊነት ገባ። የነፃ አውጭነት ክብር አገኘ እና ፖለቲካዊ አመራር ሆነ። ሆኖም የሕብረቱ ድጋፍ ስላልነበረው በ1804 ዓ.ም ቦሊቫር በድጋሜ በስፔኖች ሊሸነፍ በቃ። በዚሁ ሁለተኛው የቬንዙዌላ ሪፐብሊክ ፈረሰ።

ቦሊቫር ወደ ኒው ግሪናዳ ተሰደደ፣ በዚያም በአሁኗ ኮሎምቢያ ውስጥ በተካተተችው ቦጎታ ያለን አንድ ተገንጣይ አንጃ እንዲያስወግድ ተልእኮ ተሰጠው እና አሳካው። ከዚያም ካርታጊናን ከበበ ነገር ግን አብዮታዊ ኃይሎችን አንድ ማድረግ አልቻለም። እናም ወደ ጃማይካ ሸሸ።

ከዚያም ወደ ሀይቲ በማምራት ሞቅ ያለ የወዳጅነት አቀባበል አገኘ። የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ አግኝቶም ወደ ቬንዝዌላ ተመለሰ።

ቦሊቫር በቬንዝዌላ ጠንካራ ይዞታ ለማግኘት ብዙ ይጥር ነበር። ነገር ግን አልተሳኩም። ከዚያም እጅግ ድፍረት የሚጠይቅ እቅድ አዘጋጀ። በክረምት ወቅት ለጥ ያለውን ሰፊ ሜዳ ማቋረጥ እና የኤንደስ ተራሮችን መውጣት እና በቦጎታ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀም ይኖርበታል። ረጅሙ ጉዞ በፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም ቦሊቫር በፍፁም አልተበገረም። ለሰባት ቀናት ያህል እስከወገባቸው በውሃ ተውጠው አስር ትላልቅ ወንዞችን እያቋረጡ ገሰገሱ። ሜዳውን ሲያቋርጡ በርካታ አርበኞች በርሀብ፣ በበሽታ እና በድካም ብዛት መንገድ ላይ ሞተው ቀርተዋል። የተረፈውን ሰራዊት ይዞ በሰኔ ወር ከባዱን እና የመጨረሻውን ፈተና የኤንደስ ተራሮች መውጣት ተያያዙት፤ 1300 ጫማ ከፍታ ያለውን የፒስባን ተራራ መውጣት ግድ ነበር። ስፔኖች በዚህ ጥቃት ይመጣል ብለው በፍፁም አይገምቱምም። የተራራውን ጉዞ ፈረሶቻቸውንም እንኳ አልተቋቋሙትም፣ እንዲሁም ወደ አንድ ሺህ ወታደሮች ሞተው በዚያው ቀርተዋል። ነገር ግን ቦሊቫር እና የተረፉ ወታደሮች ዘመቻውን ቀጠሉ። የኤንደስን ተራሮች ያንቀጠቀጡት ቦሊቫር እና ወታደሮቹ ድንገት በስፔን ግዙፍ ሰራዊት ላይ በነሐሴ 1811 ዓ.ም ላይ ደርሰው እንደ መብረቅ ወረዱበት። በርካታ ወታደሮችንም ማረኩ። ስፔኖች ቦጎታን ለቀው ሸሹ። በሁለተኛው ቀንም ቦሊቫር ቦጎታን ተቆጣጠረ።

ቦሊቫር ኒው ግሪናዳን በ1811 ዓ.ም ነፃ ካወጣ በኋላ በ1813 ዓ.ም ቬንዝዌላን እና ፓናማን፣ በ1814 ዓ.ም ኢኳዶርን፣ ፔሩን በ1816 ዓ.ም እና ቦሊቪያን በ1817 ዓ.ም ከስፔን ቅኝ አገዛዝ ነፃ አወጣቸው። ከዚያም ቬንዝዌላ፣ ኒው ገራናዳ፣ ፓናማ እና ኢኳዶር በአንድ ተካተው ታላቁ ኮሎምቢያ የሚባል ትልቅ ሀገር ተመሰረተ፣ ፕሬዝደንቱም ሲሞን ቦሊቫር ሆነ። የፔሩ እና የቦሊቪያ ፕሬዚደንትም ራሱ ሲሞን ቦሊቫር ሆነ። በዚህ ታላቅ የነፃነት ትግል የስፔን የረጅም ዘመን ቅኝ አገዛዝ በመላው ደቡብ አሜሪካ አከተመ።

ከነፃነት በኋላ ሲሞን ቦሊቫር በላቲን አሜሪካ አንድ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር ትልቅ ርዕይ የነበረው ታላቅ አርበኛ ነበር። ነገር ግን እቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል። ይሁን እንጂ እርሱ በሰራው ስራ እንደ ቬንዝዌላ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ቦሊቪያ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር ለሚባሉ ሀገሮች መመስረት ምክንያት ሆኖል። እርሱ በመላው ላቲን ብሔራዊ ጀግና የሆነ እና ብሔራዊ እና ባህላዊ ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል። ቦሊቪያ እና ቬንዝዌላ ስማቸውን ያገኙት ከእርሱ ስም ነው። የሁለቱ ሀገራት ገንዘብም በስሙ ይጠራሉ። የቬንዝዌላ ገንዘብ ቦሊቫር በሚል፣ የቦሊቪያው ገንዘብ ደግሞ ቦሊቪያኖ በሚል መጠሪያ ለክብሩ ተሰይሞለታል። የተወለደበት ቀንም ሐምሌ 17 ቀን በሁሉም የላቲን ሀገራት የሲሞን ቦሊቫር ቀን በሚል እስከዛሬ ይከበራል።

ምንጭ- history.com

– Botanical.com

– National geography.com

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here