ስደተኞች እና አዲሱ ሕግ

0
192

ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በሕገ ወጥ መንገድ ቀይ ባሕርን አቋርጠው ከሚያልፉ ስደተኞች መካከል ስምንት ሺህ ያህል በየዓመቱ ይሞታሉ። ወይም የደረሱበት አይታወቅም። የተረፉት ደግሞ ወደ አውሮፓ የተለያዩ ሀገራት በመድረስ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ በመጠለያዎች ለረጅም ጊዜያት እየተጉላሉ የሚገኙ ብዙዎች ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አውሮፓዊያን በተለይ ከአፍሪካ በሚመጡ ስደተኞች መማረራቸውን በተደጋጋሚ ሲያስታውቁ ቆይተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ከአፍሪካ እና ከሌሎች የዓለም ሀገራት በተለያዩ ምክንያት በሕገ ወጥ መንገድ ጥገኝነት የጠየቁ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመመለስ እንግሊዝ ሕግ ማፅደቋን ቢቢሲ ዘግቧል።

እንደ ዘገባው ከሆነ ሕጉን ለማጽደቅ ለሁለት ዓመታት ያህል ብዙ ሲያወዛግብ ነው የቆየው። ከብዙ ክርክር በኋላ ታዲያ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ እንግሊዝ የገቡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የሚያስችለውን ሕግ በሀገሪቱ ፓርላማ ጸድቆ ሕግ ሆኗል።

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ሕጉ ተግባራዊ ሆኖ ሐምሌ 2016 ዓ.ም ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

ይህ ሕግ  ኢንግሊሽ ቻናል ተብሎ በሚጠራው የውኃ አካል በኩል በጀልባ በሕገ ወጥ መንገድ እንግሊዝ የደረሱ ስደተኞችን በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የሚያስችል ነው።

በርካታ ስደተኞች ከአፍሪካ ሜዲትራኒያን ባሕርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ በሕገ ወጥ መንገድ በአደገኛ ሁኔታ ይጓዛሉ። ከዚህም በተጨማሪ የምሥራቁ መስመር እየተባለ በሚጠራው በቀይ ባሕር እና በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ። በዚህም በርካቶች ይሞታሉ። ከሞት የተረፉት ደግሞ የተለያዩ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል።

እንግሊዝ አንዷ የስደተኞች መዳረሻ ናት፤ ከሁለት ዓመታት በፊት የስደተኞችን ሁኔታ ለማየት ወደ ሩዋንዳ ሊወሰዱ እንደሚገባ የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ ብዙ ሲያከራክር ቆይቷል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ከሀገራቸው ተሰደው ወደ እንግሊዝ የገቡትን ጥገኝነት ጠያቂዎችን መፍትሔ ለመስጠት የቀረበው አማራጭ የስደተኞችን ዓለም አቀፍ መብት የሚጥስ ነው በሚል ሲወገዝም ቆይቷል፤ በቅርቡ በፓርላማ ፀድቆ ለትግበራ በዝግጅት ላይ መሆኑ መነገሩ ታዲያ ዓመገናኛ ብዙኃን የሰሞኑ ወሬ ሆኗል።

አዲስ በጸደቀው ሕግ መሠረት ስደተኞች ለእንግሊዝ የሚያቀርቡት የጥገኝነት ጥያቄ የሚታየው ሩዋንዳ ተወስደው ነው፤ የጥገኝነት ጥያቄያቸው አዎንታዊ መልስ የሚያገኝ ከሆነ ደግሞ ስደተኞቹ እዚያው እንዲቆዩ ይፈቀድላቸዋል። ነገር ግን የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካላገኜ ግን ስደተኞቹ ሌላ ምክንያት በማቅረብ በሩዋንዳ አልያም በሌላ ሦስተኛ ሀገር የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ።

የእንግሊዝ ባለሥልጣናት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡትን ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ መላካቸው በፈረንሳይ በኩል በጀልባ ወደ ግዛታቸው የሚደረግ ጉዞን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ይላሉ።

ቢቢሲ እንደዘገበው በሀገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አማካይነት ይህን ሕግ በተደጋጋሚ ለማስጸደቅ እና ተግባራዊ ለማድረግ እንግሊዝ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

የእንግሊዝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ወራት በፊት ይህ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ ዕቅድ ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ትክክለኛ ስጋት ያላቸውን ሰዎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተገደው እንዲመለሱ እና አደጋ ላይ እንዲወድቁ ሊያደርግ እንደሚችል አሳስቦ እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ ቡድኖችም የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ አነስተኛ ወደ ሆነባት ሩዋንዳ ስደተኞችን መላክን አጥብቀው እንደሚቃወሙት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ይህን ተከትሎ የእንግሊዝ መንግሥት ከሩዋንዳ ጋር የስደተኞችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ተጨማሪ ስምምነት ደርሶ፣ ሩዋንዳ ለስደተኞች ደኅንነቷ የተጠበቀ ነው ሲል ደምድሟል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ እንግሊዝ ለሩዋንዳ 370 ሚሊዮን ፓውንድ ትከፍላታለች። ይሁን እንጂ ከሩዋንዳ ውጭ ከሌሎች ሀገራት ጋር እንግሊዝ ተመሳሳይ ስምምነት ለማድረግ ያደረገችው ሙከራ እንዳልተሳካ ዘግቧል።

የዘጋርዲያን ዘገባ እንደሚያስረዳው ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመጠርነፍ መመሪያ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል።  በርካታ ጥገኝነት ጥያቄዎችንም ያስወግዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከብዙ ጭቅጭቅ እና ክርክር በኋላ የፀደቀው ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ ውሳኔ ሕገ ወጥ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ ግዛቶች የሚያደርጉትን ጉዞ ይቀንሳል ተብሏል።  ነገር ግን የስደተኞችን  ደኅንነት ከግምት ያላስገባ ና በሚል እየተተቸ ነው።

ደኒሳ ዴሊክ የተባሉት የእንግሊዝ የአድቮኬሲ ኦፍ ኢንተርናሽናኒል ኮሚቴ ዳይሬክተር በሰጡት አስተያየት “ሕጉ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ መላክ ውጤታማ ያልሆነ፣ አላስፈላጊ በሆነ መልኩ ጨካኝ እና ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ አባካኝ ነው” ብለዋል።

የእንግሊዙ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሴክሬታሪያት ጀምስ ክሌቨርሊ እንደተናገሩት ደግሞ፣ ሕጉ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ እንግሊዝ የሚገቡ ጀልባዎችን ለማስቆም የተወሰደ ወሳኝ ውሳኔ ነው።

ጀምስ ክሌቨርሊ አክለውም “የመጀመሪያውን በረራ ለማከናወን አስፈላጊውን ሁሉ እያደረግን ነው። ለዚያም ነው እየሠራን ያለነው። አሁን ስደተኞችን የያዘው የመጀመሪያው አውሮፕላን እንዲበር ለማድረግ ቀን  እና ሌሊት በመሥራት ላይ ነን” ሲሉ መናገራቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here