“የክህደት ስሜት ተሰምቶናል” ሲሉ ሐሳባቸውን ይጀምራሉ። እኒህ ሰው አቶ ዘውዱ ደሳለ ይባላሉ። የሕወሓት ታጣቂዎች በራያ የሚገኙ ወረዳዎችን በወረራ መያዛቸውን ተከትሎ ተፈናቅለው በቆቦ ይገኛሉ። ተፈናቃዩ ለበኩር በስልክ በሰጡት አስተያየት “ሚያዚያ የእርሻ ወቅታችን ነው። ሆን ተብሎ በዚህ ሰዓት እንድንወረር የተደረገው በቀጣይ ዓመት ምርት አልባ እና ስደተኛ እንድንሆን ነው” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሞኑን እንዳስታወቀው የሕወሓት ታጣቂዎች በፈጸሙት ወረራ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል። በከፋ ችግር ውስጥም ይገኛሉ። እየደረሰባቸው ያለውን ችግር በስልክ የነገሩን አቶ ዘውዱም “በከፋ ችግር ውስጥ ነን። ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ተስፋ እየቆረጠ ነው” ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ዋስትና ማጣቱን ነው ያነሱት።
ሕወሓት ታጣቂዎቹን አሁንም እያስገባ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪው ጦርነት ለማንም አዋጭ አለመሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም በተለይ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል።
እንደ አቶ ዘውዱ ማብራሪያ በወረራ በተያዙ አካባቢዎች የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በታጣቂዎቹ ተዘርፈዋል።
በመጨረሻም መንግሥት ቃል በገባው መሠረት የአማራ ማንነታቸው እንዲረጋገጥላቸው ነው ያሳሰቡት።
ሌላው ሐሳባቸውን በስልክ ያካፈሉን ተፈናቃይ አቶ መንገሻ ኪዳኑ ከላይ የተነሱትን ሐሳቦች ሙሉ ለሙሉ ይጋራሉ። ችግሩም በተለይ በሴቶች፣ በሽማግሌዎች እና በሕጻናት ላይ የከፋ መሆኑን ተናግረዋል።
የእርሻ ወቅት መሆኑን በማንሳትም መሬታቸው ጦም እንዲያድር መገደዳቸውን አክለዋል። ይህ በመሆኑ ደግሞ ችግሩ በቀጣይ ዓመት እንዲከፋ ያደርገዋል ብለዋል። በመሆኑም አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ከተፈናቀሉት ባሻገር በርካቶች በወረራ በተያዙ አካባቢዎች (በቀያቸው) ይገኛሉ። በስልክ ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉንም ጠይቀናቸው ነበር። ነገር ግን ለደህንነታቸው እንደሚሰጉ ነው የነገሩን። ነዋሪዎቹ እንዳሉት የሕወሓት ታጣቂዎች ከባድ በደል እየፈጸሙባቸው ነው።
ለዘመናት ሲጠይቁት የነበረው የማንነታችን ይከበር (ይረጋገጥ) ጥያቄያቸው መፍትሔ እንደሚሰጠው ተስፋ አድርገው እንደነበር በማንሳትም በአሁኑ ወቅት ግን ተስፋቸው ባዶ ሆኖ ለዳግም ስቃይ መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ታጣቂዎቹ በወረራ አካባቢውን ከያዙ ጀምሮ ሀብት እና ንብረት እየዘረፉ፣ ነዋሪውንም እያንገላቱ እንደሚገኙ ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም እየዘረፉ እና እያወደሙ መሆኑን ነው የነገሩን። በአጠቃላይ ሕዝቡ እየደረሰበት ባለው በደል ምክንያት ተከድተናል የሚል ስሜት እንዳደረበት አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በራያ እና አካባቢው የተፈጸመውን ወረራ ተከትሎ ሁኔታው እንደሚያሳስበው የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል። ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪም መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን የእንግሊዝ እና አሜሪካ ኤምባሲዎች ውጥረቱ እንደሚያሳስባቸው አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት ሁለቱም ወገኖች ግጭት ከማባባስ እንዲታቀቡ እና የንጹሃንን መፈናቀል እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የፌደራል መንግሥት እና ሕወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የጠየቁት ሊቀ መንበሩ ለአወዛጋቢ ቦታዎች መፍትሔ ይሰጣል ያሉት የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ወረራውን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም “ካለፈ ስሕተተ አለመማር የመጀመሪያውን ስሕተት ከመሥራት የባሰ ነው” ሲል ነው ያስጠነቀቀው። ካለፈው ስሕተታቸው ሳይማሩ ዛሬም ተመሳሳይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉትን ሁላችንም ተባብረን አደብ ማስገዛት ይኖርብናል። ከትዕግሥት በኋላ የሚከሠት ሕግ የማስከበር ሥራ ያደረሰውን አስከፊ ውጤት ከቅርቡ ታሪካችን ልንማር ይገባልናል” ብሏል።
በመግለጫው እንደተብራራው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጦርነትን በፖለቲካዊ መፍትሔ የመቋጨት ባሕልን አምጥቷል። ይህም ለትውልድ የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክትን ከቂም ጋር ላለማውረስ የተደረገ ውሳኔ መሆኑን ነው የገለጸው።
በሌላ በኩል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከአላማጣ እና የራያ ወረዳዎች ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል። ከተፈናቃዮቹ መካከልም 42 ሺህ የሚሆኑት በሰሜን ወሎ ቆቦ ከተማ እንዲሁም ከስምንት ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና ከተማ ሰቆጣ ተጠልለው እንደሚገኙ አክሏል። ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉም በሏል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም