በታሪካዊቷ ጎንደር፣ በአስደማሚው የፋሲለደስ ግቢ እየተንሸራሸርን አብረን እንድንቆይ በአክብሮት ጋበዝኳችሁ።
ጎንደር የተቆረቆረችው በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደነበር ይነገራል። በንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ የተቆረቆረችው ውቢቷ ጎንደር እስከ 1854 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት መዲና በመሆን ያገለገለች እድሜ ጠገብ ከተማ ናት። በአንድ አፈ ታሪክ እንደሚገለፀው አንድ መነኩሴ ናቸው አሉ ለንጉሡ በ”ገ” ቃል በሚጀምር ስፍራ መናገሻውን እንዲገነባ በነገሩት መሰረት ጎንደር ላይ ዋና ከተማውን እንደገነባ ይነገራል። ታዲያ ጎንደር ከተቆረቆረች ጀምሮ በርካታ ቤተ መንግሥቶች፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ ቤተ መጻህፍት፣ የግለሰብ እና የመንግሥት ህንፃዎች ተገንብተውባት እናገኛለን።
በ16ኛው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ ጎንደር ዋና ከተማቸው እንደሆነች በማወጅ ቋሚ ከተማ መስርተዋል። ከዚያ በፊት ነገሥታት መኖሪያቸውን ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅሱ እና በድንኳንም ይኖሩ ነበር። ይህ ልማድ የቀረውም ንጉሥ ፋሲለደስ ጎንደርን በ1628 ዓ.ም መዲናቸው አድርገው በቆረቆሩበት ጊዜ ነበር። ፋሲል ግቢ ብለውም እንደ ሰየሙት ታሪክ ያስረዳል።
ታዲያ አሁን በዚህ ታሪካዊ ግቢ ዓፄ ፋሲለደስ የገነቡትን ቤተመንግስት ጨምሮ ተከታትለው የነገሱት ነገሥታት የየራሳቸውን ቤተመንግሥት ገንብተው ያለፉባቸው አሻራዎች በግቢው ይገኙበታል። ዐፄ ዮሀንስ፣ እያሱ፣ ባካፋ፣ ዳዊት ሦስተኛ እንዲሁም እቴጌ ምንትዋብ የገነቧቸው ይጠቀሳሉ። በ70ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚገኘው የፋሲለደስ ግቢ ዙሪያውን 900 ሜትር ርዝመት ባለው ግንብ ታጥሯል።
አሁን ንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ ያስገነቡትን ቤተመንግሥት በመጎብኘት እንጀምር። የቤተመንግሥቱ ህንፃ ንድፍ የትም ዓለም የሌለ የኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነ በአንድ ወቅት በጎበኘሁበት ወቅት አስጎብኛችን ነግሮናል። ቢሆንም የወቅቱን የመካከለኛውን ዘመን የኪነ ህንፃ ጥበብ የተከተለ እጅግ ውብ ቤተ መንግሥት ነው። ለንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ የግል መኖሪያቸው ነበር።
ፋሲል ግንብ ምድር እና ፎቅ ያሉት ሲሆን ምንም እንኳን ለሕዝብ እይታ ክፍት የሆነው የመጀመሪያው ክፍል ቢሆንም እስከዛሬ ድረስ በሙዚየምነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በዋናው ወለል ላይ የመጀመሪያው ክፍል የፍርድ መስጫ ክፍል ነበር፤ በመቀጠል የወንዶች የግብር ክፍል እና የሴቶች የግብር ክፍል ቀጥለው ይገኛሉ። በሁለተኛው ፎቅ የንጉሥ ፋሲለደስን የመልበሻ ክፍል ጨምሮ የመዝናኛ ስፍራን አካቷል። እንዲሁም ግቢውን በተሻለ መልኩ ማየት የሚያስችል ማማ አለው።
ሁለተኛው ቤተመንግስት የዐፄ ዮሀንስ ነው። ዐፄ ዮሀንስ የንጉሥ ፋሲለደስ ልጅ ናቸው። በደንብ የሚታወቁበት ጉዳይ ግብር ባለማስከፈላቸው እና በእንስሳት መብት ቀደምት ተሟጋች መሆናቸው ነው። በግንቡ ጀርባ አንድ ደወል አሰቅለው ነበር። ፍትህ እንደተጓደለ ያመነ ማንኛውም ሰው እንዲደውለው ይደረግና የደዋዩን ጥያቄ ለመመለስ ለፍርድ ይቀመጣሉ።
ዐፄ ዮሐንስ የመንግሥት ሥራቸውን የሚያስኬዱበት ግንብ በዚሁ ግቢ ከፋሲል ግንብ ቀጥሎ ተገንብቶ እናገኛለን። ህንፃው በመጀመሪያው ፎቅ ቤተመጻሕፍት ያለው እና በሁለተኛው ፎቅ የንጉሡ እንግዳ መቀበያ ክፍሎች አሉት።
የዐፄ ዮሐንስ ልጅ ዐፄ እያሱ ደግሞ የራሳቸውን የቤተመንግሥት ህንፃ ገንብተዋል። ህንፃው ከዋናው ከፋሲል ግንብ ጀርባ የሚገኝ ሲሆን ውስጡ በብር፣ በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮች እና በዝሆን ጥርስ ያጌጠ ነው። ከአባታቸው ዐፄ ዮሐንስ በተለየ አባካኝ ስለነበሩ ወጪያቸውን ለመሸፈን ሲሉ ግብር ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን እና ከግብፅ ይሰበስቡ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
ቀጣዩ ንጉሥ ዳዊት ሳልሳዊ ሲሆኑ ባስገነቡት የቤተመንግሥት ኮምፕሌክስ የሙዚቃ አዳራሽ አበርክተዋል። አዳራሹ ወፈር ባለ የድንጋይ ግድግዳ የተከፈለ ሲሆን በግራ በኩል ያለው መንፈሳዊ መዝሙር ይዘመርበታል። በቀኝ በኩል ያለው ክፍል ደግሞ ዓለማዊ የሙዚቃ ድግስ የሚዘጋጅበት ነው። አዳራሹ በአራቱም አቅጣጫ ወደ አዳራሹ የሚያስገቡ ሁለት ደረጃዎች እና ሁለት በሮች ነበሩት።
የአንበሳ ቤት ሌላው በፋሲል ግቢ ከሚገኙ የጥንት አሻራዎች አንዱ ነው። በውስጡ ባለጥቁር ጋሜ አንበሶች ይኖሩበት ነበር።.
ዐፄ በካፋ ደግሞ በግቢው ጀርባ ስሜን ምእራብ በኩል አንድ ትልቅ ቤተመንግስት ያስገነቡ ሌላው የዘመኑ ታላቅ ንጉስ ነበሩ። የግብር አዳራሽ እና የፈረሶች ማረፊያ አዳራሽ አሰርተዋል። የፈረሶች ማደሪያ ለእያንዳንዱ ክፍል ያለው ሲሆን እንደ ባለቤቶቻቸው ማእረግ ክፍሉ ይለያያል።
እቴጌ ምንትዋብ የዐፄ በካፋ ሚስት ስትሆን በጎንደሮች ዘመን የባሏን ሞት ተከትላ ለአርባ ዓመታት ያህል እንደገዛች ይነገርላታል። በፋሲል ግቢ ውስጥ የራሷ ቤተመንግስት ነበራት። ከእርሷ መኖሪያ አጠገብም የቀጭን ፈታዮች ትምህርት ቤት ከፍታ እንደነበር ታሪክ ዋቢ ነው።
ቤተመንግሥቷ ከፋሲል ግቢ ጀርባ በኩል የተገነባ ነው። ሁለት ፎቆች ያሉት ከኖራ ድንጋይ የተሰራ ውብ ህንፃ ነው።
12ቱ በሮች
የፋሲል ግቢ 900 ሜትር በሚረዝም ግንብ የታጠረ ሰፊ ግቢ ሲሆን አስራ ሁለት በሮች አሉት። አንደኛው የፊት በር ወይም ጃንተከል በር ይባላል፣ ወደ አደባባይ ተክለ ሀይማኖት ቤተክርስቲያን ያስወጣል። ሌላው ወንበር በር ወይም የዳኞች በር ይባላል። ሶስተኛው በር ተስካር በር ሲሆን በዐፄ ዳግማዊ እያሱ ዘመን በተካሄደ ጦርነት የወደመ አንድ ድልድይ ነበረው። ሌላው አዛዥ ጥቁሬ በር ሲባል ከአደባባይ ተክለ ሀይማኖት ቤተክርስቲያን ጋር በአንድ ድልድይ የተገናኘ ነበር። አደናግር በር በቀጭን ፈታዮች በኩል ካለው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ጋር በአንድ ድልድይ የተገናኘ ነበር። ኳሊ በር ከእልፍኝ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መግቢያ ቀጥሎ ያለ በር ነው። እምቢልታ በር የሚባለው ደግሞ የሙዚቀኞች መግቢያ ነው። ሌላው እልፍኝ በር የሚባለው ሲሆን ከፋሲል ግቢ የግል መኖሪያዎች ጋር የሚያገናኝ ነው። ሌላው ባልደራስ በር ወይም የፈረሰኞች አዛዦች መግቢያ ይባላል። ራሶች የሚገቡበት ደግሞ ራስ በር እና የቋራ ሰዎች የሚገቡበት ቋረኞች በር ሌላው በር ነው። እርግብ በር ወይም ቀጭን አሸዋ በር፤ እንዲሁም እንኮየ በር የሚባለው ሌላው በር ሲሆን የእቴጌ ምንትዋብ እናት የልእልት እንኮይ መግቢያ እንደሆነ ይነገራል። የመጨረሻው ከግምጃ ቤት ማሪያም ቤተክርስትያን ግቢ ጋር የሚያገናኘው ደግሞ ግምጃ ቤት ማርያም በር ይባላል።
በአጭሩ የፋሲል ግቢ እስካሁን የጥንቱን ታሪክ ነጋሪ ብዙ ቅርሶችን ይዞ ቢገኝም ከእድሜ መብዛት እና ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ተፅእኖዎችን ተቋቁሞ የመቀጠል ጥንካሬ እያጣ ይመስላል። በ1971 ዓ.ም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ በመባል የተመዘገበው የፋሲለደስ ግቢ የቤተመንግሥት ሕንፃዎች አሁን አደጋ ላይ ናቸው። ተረባርቦ አፋጣኝ ጥገና ማድረግ ካልተቻለ በአጭር ጊዜ ልናጣቸው እንችላለን። ትኩረት ለፋሲለደስ እያልኩ አበቃሁ።
ምንጭ፡-ዩኔስኮ ካልቸራል ሄሪቴጅ፣ታዲያስ ጎንደር ታደሰ ጸጋ፣
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም