“የሴቶች ኑሮ እና ሚና ድሮ በተሰፋው አስተሳሰብ ልክ አይቀረፅ”

0
312

“በልጅነቴ  የፈለኩትን ነገር እንድሆን አባቴ የሰጠኝ ነፃነት በምንም ነገር ውስጥ ሳልፍ ሰው ምን ሊለኝ ይችላል የሚል መጠራጠር ሳይፈጠርብኝ የፈለኩትን መንገድ እንድሄድ ረድቶኛል፡፡” ስትል የምትገልፀው የማህበራዊ አምድ የዚህ ሳምንት እንግዳችን ወ/ሮ ሃምሳል ወርቁ ናት፡፡

በአቡነ ጎርጎርዮስ ቤዛ ብዙሃን አፀደ ህፃናት የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ የ(ሰርቪስ) ሹፌር ወ/ሮ ሃምሳል ሱሪ እና ሸሚዝ ለብሳ ኮፍያ  አድርጋ ለሚመለከታት ሰው የወንድ አለባበስ እና ቁመና ያላት ናት፡፡

ወ/ሮ ሃምሳል ትውልድ እና እድገቷ በባሕር ዳር ከተማ ሲሆን የታዳጊነት ዕድሜዋን  በመረብ ኳስ እና በብስክሌት ስፖርተኝነት  አሳልፋለች፡፡ በክልሉ ስፖርተኛ በነበረችበት ጊዜ በመላው አማራ ስፖርቶች በባሕር ዳር ፣ በዞኖች ፣ በወረዳዎች እና   በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውራ የመወዳደር እድልም እንዳገኘች ትገልፃለች፡፡

ወ/ሮ ሃምሳል በታዳጊነት ጊዜዋ  በቤት ውስጥ ከቤተሰቦቿ የነበራት ማበረታታት በተለይም ወላጅ አባቷ “ከቤቴ ስወጣ ሊገጥመኝ የሚችለውን ችግር ቀድሜ ተረድቼ ራሴን እንዳበረታ እና ማንም ከፈለኩት ህልም እንዳያስቀረኝ ስላበረታታኝ ያሰብኩትን ከመሥራት ወደኋላ ብዬ አላውቅም” ስትል ራሷን ትገልፃለች ፡፡ ከልጅነቷ ጀምራ  በመኪና ስትጓዝ እንዴት እንደሚያሽከረክሩ ታስተውል እንደነበረ የምታነሳው ሃምሳል ሹፌር የመሆን ፍላጎት አድሮባት ስለነበር ሀለተኛ ደረጃ ትምህቷን በፖሊ ቴክኒክ ሙያና ስልጠና ኮሌጅ በአውቶሞቲቭ ተምራለች፡፡

ወደ አሽከርካሪነት (ሹፍርና) ሥራ የገባችው ግን በ2001 ዓ.ም ነው ፤ በወቅቱ በነበራት 2ተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ የባጃጅ ሹፌር በመሆን ለአንድ ዓመት ሰርታለች፡፡ ከ2001 ዓ.ም በፊት ለትንሽ ጊዜ ቢሆንም የባጃጅ ሹፌር የነበረች ሲሆን ሃምሳል በምትሠራበት ወቅት ግን ብቸኛዋ ሴት የባጃጅ ሹፌር እሷ ብቻ ነበረች፡፡ በቀጣዩ ዓመት ግን ወደ ማሰልጠኛ ተቋም በመግባት ከባጃጅ እስከ ደረቅ አንድ ላሉ ተማሪዎች ማሰልጠን ጀመረች፡፡

ውሎዋ ከወንዶች ጋር ቢሆንም የተለየ ችግር ገጥሟት እንደማያውቅ የምትገልፀው ሃምሳል በሥራዋ የተለየ የምትለው ፈተናም ገጥሟት እንደማያውቅ ትናገራለች ፤ ከሹፍርና በኋላ   የሠራችበት መንጃ ፍቃድ የማሰልጠን ሥራ ግን ሰዎችን እንደመጡበት አካባቢ ፣ ሁኔታ እና ባሕሪ መረዳት እና ማስረዳት ስለሚጠይቅ ከባድ እንደነበረ እና ያንን ተቋቁማ ከ10 ዓመት በላይ እንደሠራች ታነሳለች፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የቤዛ ብዙሃን አፀደ ህፃናት  ሰርቪስ ሹፌር ሆና እየሠራች ነው፡፡

በፊት በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት ሹፍርና የወንድ ሥራ ነው የሚል ስለነበር  ሴቶች ሥራውን እንዲፈሩት አድርጓል፡፡ለዚህ ሙያ ወደ ስልጠና ከሚመጡ ሴቶች ያየችውም ችግር ፍራቻን ነው፡፡ ከተማሩ እና ከሰለጠኑ በኋላ ግን የማሽከርከር ብቃታቸው ከፍተኛ የሚሆነው የሴቶቹ ነው ምክንያቱም ሴቶች ነገሮችን በትኩረት ስለሚሠሩ እና ስለሚያስተውሉ ነው ፤ የሚል ሃሳቧንም ገልጻለች ፡፡ እዚህ ጋር እኛም አንድ አብነት ለመጥቀስ ያህል ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ሲሸጡ በሴት የተነዱ ከሆነ ዋጋቸው ይጨምራል፤ ምክንያቱ ደግሞ ሴቶች ለመኪና አያያዝ ያላቸው ጥንቃቄ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

“የኔ የግል ተሞክሮዬ የሹፍርና ሥራ ስጀምር ከሞተር ፣ባጃጅ ፣ ህዝብ አንድ፣ ደረቅ አንድ፣ ደረቅ ሁለት እያልኩ በደረጃ ስላወጣሁት ብዙ ፈተና አልገጠመኝም፤ ከባድም አይደለም” ትላለች፡፡

የወንድ አለባበስ ስላላት እና ከወንዶች ጋር በመዋሏ አግብታ ልጅ ትወልዳለች ብለው የማያምኑ ብዙ እንደነበሩ አንስታ ከስፖርተኝነቷ ጀምሮ የምትለብሰው አለባበስ ስለነበረ እና ለሥራዋ ምቾት ስለሚሰጣት አለባበሷ አሳስቧት እንደማያውቅ ትገልፃለች፤ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት መሆኗን ሲሰሙ ደግሞ ‘ሴት ሁኚ እንጂ ’ የሚል አስተያየት ከመሰንዘር ወደኋላ ባይሉም የኔ አስተያየት  ሁል ጊዜም “ሰው በሥራው እና በሥነ ምግባሩ እንጂ በአለባበሱ አይገለፅም የሚል ነው፡፡” ብላለች፡፡

ሰው ትዳር የሚመሰርተው አመለካከቱን መዝኖ ነው እንጂ አለባበስን መሰረት አድርጎ ባለመሆኑ ቀለል የሚለውን ልብስ መልበሷ አሳፍሯትም እንደማያውቅ ነው የምትናገረው፡፡

በሥራው አለም የወንድ የሴት የሚል ነገር እንደሌለ የምታምነው ሃምሳል ሥራ የፍላጎት  ነገር መሆኑን መረዳት ይገባልም ትላለች፤  “በማህበረሰቡ ሴትን አትችልም ብሎ አሳንሶ መሳሉ በሴቶች ችሎታ የለኝም የሚል ፍራቻን ስላሳደረ እንጂ አቅምን መሰረት ያደረገ ፍረጃ አይደለም” ትላለች-አምሳል፡፡

አምሳል ለምሳሌ የምታነሳው የሹፍርና ሥራ ንቁ እና አስተዋይ ሰው ይፈልጋል፤ ፈሪ ሰው ቶሎ ስለሚደነግጥ ለሥራው አይመከርም፤ ሴትም ትሁን ወንድ በዚህ ሥራ ውስጥ ሲገቡ  ፍሪሲዎን፣ ፍሬን፣ ነዳጅ እና ለማሽከርከር የሚያግዙ ሌሎች ነገሮችን  ለማቀናጀት ጭንቅላታችን ምን ማድረግ አለበት ብሎ ማስተዋል ይጠይቃልም ትላለች፡፡

ምንም ነገር በአንድ ቀን እንደማይመጣ የምታምነው ሃምሳል ብዙ ሴቶች ወደ ሥልጠና ሲመጡ ከፍተኛ ፍራቻ ቢኖርባቸውም በሂደት የተማሩትን በመለማመድ ውጤታማ ሆነዋል፡፡

አሁን ብዙ ቦታ የባጃጅ፣ አውቶሞቢል እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ የሚሠሩ በርካታ ሴቶች መታየታቸው ብቻ ሳይሆን ውጤታማ ባለሙያነታቸውንም አስመስክረዋል፡፡

ሴትነት የጥንካሬ ተምሳሌት እንጂ የጠባቂነት ማሳያ እንዳልሆነ የምታምነው ሃምሳል ሁለቱንም ልጆቿን አርግዛ ለዘጠኝ ወራት ሥራዋን እንደሠራችም ትገልፃለች፡፡

ወላጆች ልጆች በራስ መተማመን እንዲኖራቸው አድርገው መቅረፅ አለባቸው፡፡ የተፈጥሮ ልዩነቶችን መቀበል አለብን፤ ሴቶች ከወንዶች በተፈጥሮ የምንለይባቸውን ነገሮችን መቀበል አለብን፤ ይሄ ልዩነታችን ፀጋ ነው፤ ያለበለዚያማ ሴት እና ወንድ ሆነን መፈጠር ባላስፈለገን ነበር። ነገር ግን አሁን ያለው የማህበረሰቡ አመለካከት የተመሰረተበት በፊት የነበሩ የኑሮ ሁኔታዎች ላይ ነው።

ድሮ በነበረው አኗኗር ይመቻል ያሉትን ሥርዓት ሰርተዋል፤ ጥያቄአችን መሆን ያለበት ድሮ ለምን እንዲህ ሆነ ሳይሆን ዛሬ ነገሮች እና ሁኔታዎች ስለተቀየሩ የሴቶችን ኑሮ እና ሚና ድሮ በተሰፋው አስተሳሰብ ልክ አይቀረፅ የሚል ነው።  በወቅቱ ወንዱ እንደ ብቸኛ የገቢ አስገኚ ተደርጎ ቢቆጠር ከሴት ይልቅ ወንዶች አድነው እና አርሰው ቤተሰባቸውን ይመግቡ እንደነበር  ሀቅ ነው።  አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሴቶች በሁሉም መስክ ከወንድ እኩል ድርሻ መውሰድ ስለሚችሉ የነበረው አስተሳሰብ ይቀየር ኑራችንም ይህን መሰረት አድርጎ ይዋቀር፤ ይህንን ስንል የዱሮውን መውቀስ ላይ ሳይሆን ዛሬን መቀየር ላይ ነው  ትኩረታችን መሆን ያለበት፤  ቤተሰብም ልጆቹን ሲያሳድግ ይህንን ጠንካራ ስነ ልቦና ገንብቶ የማሳደግ ሃላፊነቱን በመወጣት ዛሬ ጀምሮ ሊሠራው የሚገባው የቤት ሥራ እንደሆነም ሃምሳል ሃሳቧን አጋርታናለች።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here