የአማራ ብሔራዊ ክልል በተፈጥሯዊ ሀብት፣ በአስደናቂ መልክአምድራዊ አቀማመጥ፣ በታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች የታደለ ነው:: ሆኖም ክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የመሬት መራቆት እና የእንስሳትም ሆነ የእጽዋት መመናመን ተስተውሎበታል::
ክልሉ ለተስተዋሉበት ችግሮች መፍትሄ ለመሻት የተለያዩ ጥረቶች እየተካሄዱ መሆኑ ነው የተጠቀሰው:: ከመፍትሔዎቹ መካከልም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ለነዋሪዎች ዘላቂ ጥቅም የሚሰጥበትን ዘዴ ለመዘርጋት ፓርኮች፣ የተከለሉ ጥብቅ ቦታዎች እና እርጥበት አዘል መሬት አስተዳደር ወሳኝ መሆናቸው ታምኖበት ወደ ተግባር ተገብቷል::
ከተግባራቱ መካከልም የባሕር ዳር ዓባይ ወንዝ ሚሊኒዬም ፓርክን የክልሉ መንግሥት ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 59/2008 አስተዳደሩን እና ድንበሮቹን አጽድቋል::
ፓርኩ 4 ሺህ 729 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት እና 32 ኪሎ ሜትር ርዝመት ተለክቷል:: ይህም ከባሕር ዳር ጣና ሐይቅ ዓባይ ወንዝ ተለይቶ ከሚወጣበት እስከ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ ድረስ ያለውን ቀጣና የሚሸፍን ነው::
ፓርኩ ሲመሰረት ከዓባይ ወንዝ እስከ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ በወንዙ እና ዳርቻው የሚገኝ የብዝሀ ህይወት ሀብት በቀጣናው በሚኖሩ ነዋሪዎች እና ከፋብሪካዎች ከሚወጣ በካይ ውጋጅ መጠበቅ ቀዳሚው ዓላማ አድርጓል:: በተጨማሪም ሀብቱን በአካባቢው ነዋሪዎች ተሣትፎ በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፉን ለምስረታው መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች በሁለተኛነት ተጠቅሷል::
የፓርኩን መስህብ እና ገጽታ በፊልም ለመቅረጽ የተለየ ወይም የተቆረጠ ክፍያ የለም:: ሆኖም በአውሮፕላን ቀረፃ ለማድረግ ከሲቪል አቪዬሽን የበረራ ፈቃድ ማግኘት ግድ መሆኑን ድረ ገፆች አስነብበዋል:: አብራሪውም ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የተመሠከረ ፈቃድ ያለው መሆን እንዳለበት ተሰምሮበታል::
ፊልም ለመቅረጽ የሚፈልግ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ማመልከቻውን ለመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አመልክቶ ከውጪ ሚዲያ እውቅና እንዲያቀርብ በሕግ ይገደዳል::የመረጃ ምንጫችን ፊልም ፊክሰር ዶት ኮም እና ሊፕ.ዩኤንፒ ዶት ኮም ናቸው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም