የውጤታማነት ለውጡ እስከ ህዋሳት የሚዘልቀው

0
145

የጤና ተመራማሪዎች ቡድን በእንስሳት ላይ ባደረገው ሙከራ እና ጥናት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሁሉም የአካል ክፍሎች ላይ እስከ ህዋሳት የሚዘልቅ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ መረጋገጡን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ በሚያዝያ ወር መጨረሻ ለንባብ አብቅቶታል::

በአሜሪካ የማሳቹሴት እና የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ቀደም ብሎ የአካል ብቃት ለሰውነት ጠቃሚ ከመሆኑ ባሻገር በአይጥ ላይ ባደረጉት  ምርምር በ19 የአካል ክፍሎች ላይ እስከ ህዋሳት የሚዘልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አረጋግጠዋል::

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለበሽታ የመጋለጥ አጋጣሚን ይቀንሳል:: ተመራማሪዎች ይህን እውነታ ቢረዱም በህዋሳት ደረጃ እንዴት ለውጡ እንደሚገለጥ በውል አልተገነዘቡም ነበር:: ለዚህ ደግሞ አብዛኛዎቹ ጥናቶች ያተኮሩት በአንድ አካል፣ ፆታ፣ ጊዜ እና ውስን የመረጃ ምንጭ መነሻ ያደረጉ በመሆናቸው እንደሆነ ነው የተብራራው::

በመሆኑም የተመራማሪዎች ቡድኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በአይጦች ላይ /በመሮጫ ማሽን ላይ እንዲሮጡ በማድረግ/ የመመራመር እና ውጤቱን የመቀመር ተግባርን ከውኗል:: እንዲሁም እንደልብ፣ አንጐል፣ ሳንባ በመሳሰሉት ህብረ ህዋሳት ድረስ ዘልቆ አጥንቷል:: በውጤቱም የተመለከቷቸው የአካል ክፍሎች በአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሽታ የመከላከል፣ ለጭንቀት ምላሽ መስጠት፣ የጉበት፣ የልብ ህመም እና የሰውነት ክፍል መጐዳትን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ደርሰውበታል::

የተሰበሰበው መረጃ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ፍንጭ የሚሰጥ ሆኖም አግኝተውታል- ተመራማሪዎቹ:: ለአብነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጉበት በስብ የመሸፈን አጋጣሚ እንዲቀንስ ማድረጉን ተረድተዋል:: ይሄ ደግሞ በራሱ በአልኮል መጠጥ ሳቢያ ከሚመጡ የጉበት በሽታዎች ውጪ ላሉት ፈውስ ለመሻት በር ከፋች መሆኑን ነው ያሰመሩበት- ተመራማሪዎቹ::

የተመራማሪዎቹ ቡድኑ ግኝታቸው ወደፊት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት ለማይችሉም ያደረጉትን ጥረት ያገኙትን ውጤት በመቀጠል ወይም በመቅዳት ለችግሩ ተጠቂዎች ፈውስ ማግኘት እንደሚያስችላቸው እምነታቸው መሆኑን ነው ያረጋገጡት::

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ክፍሎች ላይ እስከ ህዋሳት የሚያሳድረውን ለውጥ ለመመርመር የተሰበሰበው በርካታ መረጃ በቀጣይ ለሚደረግ ትንተና እና አዳዲስ ግኝቶች በር ከፋች መሆኑን ነው በማጠቃለያነት ያሰመሩበት- ተመራማሪዎቹ::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here