በደቡብ ዋልታ ግግር በረዶ ንጣፍ መካከል በሚገኘው ኤርባስ ተራራ አናት የሚንፈቀፈቀው እሳተ ገሞራ በቀን ስድስት ሺህ ዶላር የሚያወጡ የወርቅ ቅንጣቶችን ወደ ገፀ ምድር እንደሚወረውር ኤን ዲ ቲ ቪ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::
በበረዶ የተሸፈነው ደቡብ ዋልታ በ2017 እ.አ.አ በተደረገ ጥናት 138 እሳተ ገሞራዎች አሉት:: ከነዚህ መካከል ዘጠኙ ንቁ ማለትም በፍንዳታ ላይ ያሉ ናቸው:: 3 ሺህ 794 ሜትር ከፍታ ያለው ኤርባስ ተራራ በፍንዳታ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል::
ኤርባስ ተራራ የሮዝ ደሴቶችን ከፈጠሩት ሦስት እሳተ ገሞራዎች አንዱ ነው:: በ1841 እ.አ.አ በቀጣናው የተንቀሳቀሰው መርከበኛ ጂምስ ክላርክ ሮዝ ደሴትን በማግኘቱ ሮዝ ደሴት በስሙ ተሰይሟል:: ኤርባስም ከመርከቦቹ የአንዱን ስያሜ መያዙ ነው በድረ ገፁ የተሰነደው::
በሮዝ ደሴት አቅራቢያ ባማክሙርዶ ጣቢያ፣ የሰፈሩ የአሜሪካ ተመራማሪዎች በኤርባስ ተራራ አናት የሚንፈቀፈቀውን እሳተ ገሞራ በመከታተል ላይ መሆናቸው ነው የተመላከተው:: እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ የሳተላይት /መንኮራኩር/ ምስሎች የቀለጠ የአለት ሀይቅ ምስል እያሳዩ መሆናቸው ተጠቁሟል:: እሳተ ገሞራው እንፋሎት እና የቀለጠ አለት እንደሚያስወነጭፍ አልፎ አልፎም ቋጥኝ አለት እንደሚወረውርም ነው ድረ ገፁ ያስነበበው::
ከእሳተ ገሞራው አፍ ከሚፈተለከው ቅላጭ መካከል ስብርባሪ መስታዎት መሰል የወርቅ ቅንጣቶችን አስወንጭፎ እንደሚያዘንብም ነው የተረጋገጠው::
እሳተ ገሞራው በቀን እስከ 80 ግራም የወርቅ ስብርባሪ ወይም ብናኞችን እንደሚረጭ ነው ባለሙያዎቹ ያስቀመጡት:: የወርቅ ስብርባሪው ወደ ገንዘብ ሲለወጥ በቀን ስድስት ሺህ ዶላር እንደሚያወጣ ነው ድረ ገፁ በማጠቃለያነት ያሰፈረው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም