የጥቁር ሕዝብ የነጻነት አባት ተብለው የሚጠሩት ኔልሰን ማንዴላ ትምህርት በዓለም ላይ ለሚከወኑ ማናቸውም ነገሮች ቀዳሚው መሳሪያ መሆኑን ንግግራቸው ያስረዳል:: ከበርካታ ንግግራቸው ውስጥ “ትምህርት ዓለምን ሊለውጡበት የሚችሉበት መሳሪያ ነው፤ ዜጎች እስካልተማሩ ድረስ ማንም ሀገር በእውነት ማልማት አይችልም” የሚሉት ይጠቀሳሉ:: እኛም ሀገራት ትምህርትን ለዕድገታቸው እንዴት ቁልፍ መሳሪያ አድርገው እንደተጠቀሙበት ልናስነብባችሁ ወደናል::
ትምህርት የሀገራት የዕድገት ጣሪያ ማረጋገጫ፣ የምርታማነት መሰላል፣ የሰላም እና ደኅንነት መሰረት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር መንገድ፣ የባህል እና ወግ ዘብ፣ የገጽታ ግንባታ መነጸር… ተደርጎ ይወሰዳል። የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚም ሆነ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ውጤታማ አድርጎ ለመጓዝ የሚያስፈልገው የሰለጠነ የሰው ኀይል መገኛ ትምህርት ብቻ መሆኑ ለዚህ ቀዳሚው ማረጋገጫ ነው:: ለማንኛውም ዘርፍ ብቁ ዕውቀት እና ክህሎት ያለው የፈጠራ ባለሙያ ለማፍራትም ትምህርት መሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው:: ነገር ግን ለተቋማቱ የሚሆነውን ብቁ የሰው ኀይል ለማፍራት ደረጃቸውን የጠበቁ እና በአስፈላጊ የትምህርት ግብዓት የበለጸጉ የትምህርት ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል። ይህም ከፍተኛ በጀትን ይጠይቃል። ለዚህም መንግሥት የራሱን ድርሻ መወጣት እና የተለያዩ ባለሐብቶችን በማስተባበር መሥራት ይገባዋል።
ትምህርት ፈጠራ እና ምርምር እንዲዳብር እና እየሰፋ እንዲሄድ ያበረታታል። እንደ ሚዲየም የመረጃ ድረ ገጽ ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት ያላቸው ሀገራት ብዙ ተመራማሪዎችን፣ ሳይንቲስቶችን እና ሥራ ፈጣሪዎችን አፍርተዋል። ይህም የቴክኖሎጂ ዕድገታቸውን እንዲያረጋግጡ ከማድረግም ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽቅድድም ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው መረጃው ያትታል:: ለአዳዲስ ግኝቶችም አስተዋፅዖ የሚያደርግ ትውልድ ገንብተዋል። ወደ ፊት ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ችግሮችን ቀድመው በመለየት መፍትሄዎችንም ይጠቁማሉ። ይህም ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ዕድገት ልዩ አበርክቶ እንደሚወጣ ተመላክቷል።
ዛሬ ላይ የዓለም ሀያላን የተባሉት አሜሪካ፣ ጃፓን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የድህነት አዙሪትን ሰብረው ተረት ያደረጉት ለትምህርት ሥርዓቱ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው ነው:: በአንድ ሀገር ያለው የተማረ የሰው ኅይል እየጨመረ ሲሄድ ድህነት እየቀነሰ፣ ዕድገት እየጨመረ እንደሚሄድ የመረጃ ድረ ገጹ በማሳያነት ያነሳል:: ይህ የሚሆነው ግን ሀገራት ለትምህርት ሥርዓቱ በሰጡት ትኩረት ልክ ሰፊ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር፣ በሥራው ልክ ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ እና ለግላዊ የሥራ ዕድል ትኩረት የሚሰጥ ትውልድ መገንባት ሲቻል ብቻ እንደሆነ ድረ ገጹ በጽሑፉ ጠቁሟል:: በቂ እና ብቁ የሰለጠነ የሰው ኅይል ያላቸው ሀገራት የኢንቨስትመንት ቀዳሚ መዳረሻ ናቸው:: ይህም የኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ የሰለጠነ የሰው ኅይልን አቅፎ የሚጓዝ በመሆኑ ሁሉም የትምህርት ዘርፉን እንዲደግፍ ያበረታታል።
የዓለም ሀገራት የዛሬ ላይ ዕድገታቸውን ያረጋገጡት ለጤና እና ደኅንነት ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው እንደሆነም ጽሑፉ ይጠቁማል:: ጤናው የተጠበቀ ማኅበረሰብን ለመፍጠር የጤና ተቋማትን ተደራሽነት ከማስፋትም በላይ ሁሉም ለራሱ የጤና ባለሙያ እንዲሆን የሚያደርግ የትምህርት ሥርዓት በመገንባታቸው እንደሆነ ጽሑፉ ይጠቁማል።
ትምህርት በጤና ውጤቶች ላይ በጎ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ጽሑፉ በስፋት ያትታል። የተማሩ ሰዎች ስለጤንነታቸው በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ማድረጋቸው፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን መከተላቸው፣ የጤና አጠባበቅ መረጃን እና አገልግሎቶችን በተሻለ ሁኔታ የማግኘት አዝማሚያ እንዲኖራቸው ያላቸው ዕድል ሰፊ መሆኑን በማረጋገጫነት አንስቷል።
ትምህርት በጤናው ዘርፍ ያለውን አበርክቶ ለመመልከት ባደጉት እና በታዳጊ ሀገራት መካከል ያለውን የዕድሜ ጣሪያ መመልከት በቂ ነው:: ጥናት እና ምርምር በማድረግ የሚታወቀው ማክሮ ትሬንድስ (macrotrends.net) ድረ ገጽ በፈረንጆቹ 2024 ይዞት በወጣው መረጃ መሠረት የአፍሪካውያን አማካይ የዕድሜ ጣሪያ 64 ዓመት ሲሆን የአውሮፓ 79 እና የኤሲያ 74 ሆኖ ተመዝግቧል::
ያደጉት ሀገራት በመጓጓዣ/በትራንስፖርት/፣ በኀይል፣ በከተማ ፕላን እና በሌሎችም የመሰረተ ልማት አውታሮች ውጤታማ ፕሮጀክቶችን ያከናወኑት ለትምህርት ጥራት በሰጡት ልዩ ትኩረት እንደሆነም ይታመናል። በተለያዩ ዘርፎች ብቁ የሆኑ የተማሩ ዜጎችን ለማፍራት ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ ዛሬ የቀዳሚነት ውለታን እየከፈላቸው ይገኛል።
ጠንካራ የትምህርት ሥርዓትን የገነቡ ሀገራት ያላቸው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ከፍተኛ እንደሚሆንም ይታመናል። ዛሬ እንደ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኢራን የመሳሰሉ ሀገራት በጦር መሳሪያ፣ በሕዋ ምርምር፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎችም ዘርፎች ያላቸው ተወዳዳሪነት የመጣው ጥራት ያለው ተግባር ተኮር የትምህርት ሥርዓትን ዕውን በማድረጋቸው ነው። በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ለመሳተፍ፣ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እና በፍጥነት ከሚለዋወጠው ኢኮኖሚያዊ እና የቴክኖሎጂ አዝማሚያዎች ጋር ለመላመድ የተሻሉት የተማረ የሰው ኅይል ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ኔልሰን ማንዴላ “ንጹሀን ዜጎች በሚሞቱባቸው ሀገራት መሪዎች ከአዕምሯቸው ይልቅ ደማቸውን እየተከተሉ ነው” በሚል ንግግራቸውም ይታወቃሉ:: ይህም ንግግር የሚገልጸው ትምህርት ለሰላም ያለውን አበርክቶ ነው:: ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኅይል ባለባቸው ሀገራት ልዩነቶችን መነሻ አድርገው የሚነሱ ግጭት ወይም አለመረጋጋቶች በዋናነት የሚፈቱት በንግግር እና በውይይት ሲሆን በታዳጊ ሀገራት ላይ ያለው አሁናዊ አካሄድ ሳይቀር በነፍጥ ሆኖ ይስተዋላል::
የዛሬዎቹ ሀገራት ትምህርትን ለማኅበራዊ መረጋጋት እና ትስስር በስፋት እንደተጠቀሙበት የሚዲየም ድረ ገጽ መረጃ ዋቢ ነው:: ውስጣዊ ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ የመረዳዳት፣ የመከባበር እና የመቻቻል ባህልን አዳብረውበታል። የሀገራቸውን ምስጢር ለማንም አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም፤ በብሄራዊ ጠቅማቸው ፈጽሞ አይደራደሩም፤ ለባህል እና ለወጋቸው ልዩ ቦታን በመስጠት ሀገራቸው በሌላኛዎቹ ሀገራት ተመራጭ እና ተወዳጅ እንዲሆኑ አድርገዋል:: አሜሪካ ለዚህ አብነት ተደርጋ ትነሳለች::
ያደጉት ሀገራት ልክ እንደ ታዳጊ ሀገራት ትምህርትን ለሥራ ማግኛ፣ ለኑሮ መግፊያ ብቻ አድርገው አልወሰዱትም፤ የፖለቲካ ግንዛቤ ማሳደጊያ ጭምር አድርገው እንጂ:: ይህም ለፖለቲካ ብቁ የሆነ ሁሉ ተሳትፎ እንዲያደርግ አግዟቸዋል:: ዛሬ አሜሪካን ጨምሮ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት የሚያደርጓቸው ምርጫዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይከናወናሉ፤ ለሕዝብ ድምጽ መከበር ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ:: ከዚህ በተጨማሪም ሀገራት ትምህርትን ዜጎች መብቶቻቸውን፣ ኃላፊነቶቻቸውን እና ግዴታቸውን በሚገባ ማሳወቅ ላይ ሰርተውበታል:: ይህም ውስጣዊ አንድነታቸውን አስጠብቀው ለልማት እና ለሀገራዊ ዕድገት እንዲተጉ አድርጓቸዋል::
አፍሪካ ወረድ ስንልም ኢትዮጵያ ትምህርትን የዕድገት መሠረት አድርገው እየሠሩበት ነው? የሚለውን ጉዳይ በተወሰነ መንገድ እንቃኝ:: የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው:: ለአብነት የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በፈረንጆቹ ሰኔ 29 ቀን 2023 ከትምህርት ሚኒስቴር አገኘሁት ብሎ እንደዘገበው በኢትዮጵያ ካሉት 50 ሺሕ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ እና ከ86 ከመቶ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹነት የሌላቸው እና በጥራታቸውም ከደረጃ በታች ናቸው::
ሀገሪቱ ከአሁን ቀደም የነበረው የትምህርት ሥርዓት ችግር የነበረበት መሆኑን በማጤን አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ አድርጋለች:: የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተሰጠው ትኩረትም ሌላው አበረታች ጉዳይ ሆኖ የሚነሳ ነው:: እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ምናልባትም ሀገሪቱ ትምህርትን የዕድገት መሠረት አድርጋ ለመሥራት ያቀደች ይመስላል::
ትኩረት ተደርጎ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ:: የመጀመሪያው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ ነው:: ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው ግን ሀገሪቱ በተደጋጋሚ እያጋጠማት ያለው የሰላም መናጋት ነው:: በመሆኑም የትምህርት ተደራሽነትን ከጥራት ጋር ማረጋገጥ፣ ተደጋጋሚ ግጭቶችን በሰላማዊ ስምምነት መቋጨት ይገባል::
ኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥሯ እየጨመረ እየሄደ ባለበት በዚህ ወቅት ተምሮ ሥራ ያጣው ወጣት ቁጥር እየጨመረ መሄዱ እንደ ሀገር የተሰጠው የትምህርት ትኩረት ግቡን እንዳያሳካ ያደርገዋል:: በአንድ ሀገር ያለው ሥራ አጥነት እየጨመረ ሲሄድ ቀጣናው ወደ አለመረጋጋት እንደሚሸጋገር እ.ኤ.አ 2021 በአውስትራሊያ ሚዲያ ኤስ ቢ ኤስ ሐሳባቸውን ያጋሩት ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያው ባይሳ ዋቅወያ አስታውቀዋል:: ጸሐፊው ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ የወጣት ሀገር፣ ለዚህም ማሳያ ያደረጉት 65 በመቶ ወይም 72 ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝቧ ዕድሜው ከ24 ዓመት በታች መሆኑን ነው:: በአንጻሩ ተምረው ሥራ ያጡት ቁጥር አሥራ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑ ደግሞ የኢትዮጵያን የወጣት ትውልድ ምድርነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ እንደሚያደርገው ገልጸዋል:: በመሆኑም ሀገራዊ ዕድገትን በትምህርት ለማሳካት ሲታሰብ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ከማፍራት በተጨማሪ ተምረው ላጠናቀቁትም የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም