የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ በግብፅ እና በኳታር የቀረበውን ሀሳብ ተስማምቻለሁ ቢልም እስራኤል ግን ያን ያህል ፍላጎት አላሳየችም::
የሐማስ ንቅናቄ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ ኢስማኤል ሃኒዬህ ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱራህማን አልታኒ እና ከግብፅ የስለላ ሚኒስትር አባስ ካሜል ጋር በስልክ ተገናኝተው ሐማስ ስምምነቱን መቀበሉን አሳውቀው ነበር።
የእስራኤል መንግሥት በበኩሉ የሐማስ ሃሳብ ከእስራኤል አስፈላጊ መስፈርቶች የራቀ ቢሆንም በእስራኤል ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ልዑካንን ወደ ሸምጋዮቹ እንደምትልክ አሳውቋል::
የሐማስ ምክትል መሪ ካሊል አልሀያ ለአልጀዚራ አረብኛ ቋንቋ እንደተናገሩት የኳታር እና የግብፅ ሀሳብ የእስራኤል ጦር ከጋዛ መውጣት እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እንዲሁም የታገቱ እስራኤላዊያንን እና የፍልስጤም እስረኞችን መለዋወጥን ያካትታል። .
ሀሳቡ ሦስት ደረጃዎችን ያካተተ ሲሆን ስምምነቱ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጦርነት እንዲያበቃ የሚያደርግ እና በሐማስ የታገቱትን እስራኤላዊያን እና በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን መልቀቅን እንደሚያካትት አልጀዚራ ዘግቧል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ እስራኤል የጦር ካቢኔዋ በራፋህ የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ማፅደቁን አሳውቋል:: “የጦር ካቢኔዉ እስራኤል ታጋቾቻችንን ለማስለቀቅ እና ሌሎች የጦርነቱን አላማዎች ለማራመድ በራፋህ ላይ የምታደርገውን ዘመቻ እንድትቀጥል በአንድ ድምፅ ወስኗል” ሲል የኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
እ.አ.አ በጥቅምት 7 ቀን 2023 ሐማስ በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት 1ሺህ 400 ያህል እስራኤላዊያንን ሲገድል 250 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ጋዛ በግዳጅ ተወስደዋል። ከእነዚህ በግዳጅ ሐማስ ከወሰዳቸው ውስጥ በግምት 100 ያህሉ በጋዛ ውስጥ በሕይወት እንዳሉ ሲታመን ሌሎች ተለቀዋል ወይም ተገድለዋል ይባላል።
አሜሪካ በበኩሏ ባለሥልጣናቷ ሐማስ ለተኩስ አቁም ሃሳብ የሰጠውን ምላሽ እየገመገሙ ነው ብላለች:: ነገር ግን ስለ ስምምነቱም ሆነ የፍልስጤም ቡድን በትክክል ምን እንደተስማማ ምንም አይነት መረጃ አልሰጠችም።
አልጀዚራ እንደዘገበው ስምምነቱ ውስብስብ ሲሆን እያንዳንዳቸው ለስድስት ሳምንታት (42 ቀናት) የሚቆዩ ናቸው:: በመጀመሪያዉ ምዕራፍ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ያለው ጦርነት በጊዜያዊ ተኩስ ማቆም እንዲሁም የእስራኤል ጦር ወደ ምሥራቅ ብዙ ህዝብ ከሚበዛባቸው የጋዛ አካባቢዎች ርቆ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ያለውን ድንበር መልቀቅ ይኖርበታል። የእስራኤል የጦር ጀቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በጋዛ ላይ በየቀኑ ለ10 ሰዓታት እና እስረኞች በሚፈቱባቸው ቀናት ለ12 ሰዓታት መብረር ያቆማሉ።
ሐማስ በመጀመሪያ ደረጃ 33 ምርኮኞችን (በሕይወት ያሉ ምርኮኞች ወይም የሞቱትን አስከሬን) ቀስ በቀስ ይለቃል። ምርኮኞቹ ሴቶች ፤ ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው፣ የታመሙ ወይም ከ19 ዓመት በታች የሆኑ እና ወታደር ያልሆኑ በቅድሚያ ይለቀቃሉ። ለእያንዳንዱ እስረኛ (ሲቪል እስረኛ) በሕይወት እያለ ለተፈታ እስራኤል ያሰረቻቸውን 30 ፍልስጤማውያንን ትፈታለች። በሐማስ ለተፈታ ለእያንዳንዱ ሴት ወታደር ደግሞ እስራኤል 50 ፍልስጤማውያንን ትፈታለች።
የእስራኤሉ ወታደራዊ ኃይል ከጋዛ መውጣት ደግሞ የተፈናቀሉ የፍልስጤም ሲቪሎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ያስችላቸዋል:: ይህም ሐማስ ምርኮኞችን ሲፈታ ቀስ በቀስ የሚከናወን ይሆናል። በተናጥል ስምምነቱ በጋዛ የመልሶ ግንባታ ሥራ እና የእርዳታ ፍሰት መጀመር እንዳለበት እንዲሁም “UNRWA” እና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ሲቪሎችን ለመርዳት እንዲሠሩ ይፈቀድላቸዋል ።
በሁለተኛዉ የስምምነት ደረጃ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በቋሚነት ማቆም እና እስራኤላውያን ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣት አለባቸው የሚል ነው:: በዚህ ጊዜ በጋዛ በምርኮ የተያዙ ወታደሮችን ጨምሮ የቀሩትን እስራኤላውያን ወንዶች ሁሉ የሚያካትት ሌላ እስረኛ መለዋወጥ ይኖራል። እስራኤላውያን በምላሹ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ የፍልስጤም እስረኞችን ይለቃሉ።
ሦስተኛው ምዕራፍ በሁለቱም ወገኖች የታሰሩ እስረኞች እና የአስከሬኖችን አፅም መለዋወጥ ነው። ይህ ደረጃ ለጋዛ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚፈጀውን የመልሶ ግንባታ እቅድም ያጠቃልላል::
እንደሚታወቀው እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ አካባቢ ወታደራዊ ዘመቻ ልታደርግ ስትዘጋጅ፣ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ቢያጋጥማትም ከሰሞኑ በምሥራቅ ራፋህ የሚገኙትን ፍልስጤማውያን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፋለች።
የሐማስ ምክትል መሪ ካሊል አል-ሀያ እንዳስቀመጡት ኳሱ በእስራኤል ሜዳ ላይ ነው። ይሁንና ሐማስ ስምምነቱን ከተቀበለ በኋላ በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሐማስ የተስማማበት ስምምነት እስራኤል ከዚህ በፊት ስትወያይበት የነበረውን ሀሳብ እንዳልሆነ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤሉ የቀኝ አክራሪው የብሄራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር ስምምነቱን ውድቅ ለማድረግ እና በራፋህ ጥቃት ለመፈጸም ወዲያውኑ ነበር በማህበራዊ ሚዲያ የወጡት።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ስምምነቱ የእስራኤልን ፍላጎት ያልጠበቀ ቢሆንም ተደራዳሪዎችን ለማግኘት ልዑካንን ወደ ካይሮ እንደሚልኩ ተናግረዋል።
አክለውም የእስራኤል የጦር ካቢኔ በሐማስ ላይ ወታደራዊ ጫና ለማሳደር በራፋህ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ለመቀጠል በአንድ ድምፅ መስማማቱንም አስታውቀዋል:: ይህን ተከትሎ ያለፈው ሰኞ ምሽት (ግንቦት 6 /2024) ከባድ የእስራኤል የአየር ጥቃት በደቡባዊ ጋዛ ተፈፅሟል።
አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው የእርዳታ ቡድኖች በራፋህ ለተጠለሉ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ፍልስጤማውያን አስከፊ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል። ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በድንገት የተቀበለው እስራኤል አንድ መቶ ሺህ የሚያህሉ ፍልስጤማውያን ከምሥራቃዊ ራፋህ ሰፈሮች እንዲወጡ ካዘዘች በኋላ ነው።
የእስራኤል ጦር በምሥራቅ ራፋህ በሐማስ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያካሄደ መሆኑን ገልጿል። ብዙም ሳይቆይ የእስራኤል ታንኮች ራፋህ ገብተው ከራፋህ ጎረቤት ግብፅ ጋር 200 ሜትሮች (ያርድ) ርቀት ላይ እንደደረሱ የፍልስጤም የደኅንነት ባለስልጣን እና የግብፅ ባለስልጣናት ተናግረዋል። እስራኤል ወረራውን ያካሄደችው የሐማስ ታጣቂዎች በራፋህ መሻገሪያ አካባቢ በሞርታር ጥቃት አራት የእስራኤል ወታደሮችን ከገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ የታገቱ ቤተሰቦች በቴላቪቭ ተቃውሟቸውን በማሰማት መንግሥት ስምምነቱን እንዲቀበል ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በጋዛ ዙሪያ ያሉ ፍልስጤማውያን የሐማስን ውሳኔ እንደሰሙ ነበር ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ ጎዳና የወጡት። ሆኖም ግን አንዳንድ ፍልስጤማዊያን ይህ ስምምነት በአንድ በኩል ብቻ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል:: ብዙዎች ተስፈኛ ሆነው ቢቆዩም ፍልስጤማውያን ይህ የጦርነቱ መጨረሻ እንዳልሆነ ያውቃሉ:: በተለይ እስራኤል በራፋህ ቦምብ ማዝነቡን ስትቀጥል ማለት ነው።
በዋይት ሀውስ እና በስቴት ዲፓርትመንት የሚገኙ የአሜሪካ ባለስልጣናት ሐማስ ስምምነቱን መቀበሉን አስመልክቶ በጋዜጠኞች ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ነገር ግን የስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር እና የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ምንም አይነት ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆኑም።
አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ኔታንያሁ በራፋህ ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር በሚጠይቁ ጠንካራ በፖለቲካ መስመር አጋሮቻቸው ግፊት እየደረሰባቸው ሲሆን ስምምነቱን ከፈረሙ ስልጣናቸውን ሊያጡ እንደሚችል እየተነገረ ነው:: በተቃራኒው የታጋቾቹ ቤተሰቦች ከእስር እንዲፈቱ ከስምምነት እንዲደርሱ ጫና እያደረጉባቸው ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን አስቸኳይ ስምምነት እንዲደረግ ያለፈው ሰኞ ምሽት በሀገሪቱ ዙሪያ ሰልፍ ወጥተዋል። ቴል አቪቭ በሚገኘው የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ተቃዋሚዎች ተሰባስበው ነበር። በእየሩሳሌም ወደ 100 የሚጠጉ ተቃዋሚዎች “ደሙ በእጃችሁ ነው” የሚል ባነር ይዘው ወደ ኔታኒያሁ መኖሪያ ዘምተዋል።
እስራኤል “ራፋህ በጋዛ ውስጥ የመጨረሻው ጉልህ የሐማስ ምሽግ ነው “ያለች ሲሆን ኔታንያሁ እንደተናገሩት በከተማዋ ላይ የሚካሄደው ጥቃት ታጣቂዎቹ ወታደራዊ አቅማቸውን መልሰው መገንባት እንደማይችሉ ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ሆኖም እስራኤል በራፋህ የምታካሂደው ኦፕሬሽን ዓለም አቀፍ ማስጠንቀቂያ እና ተቃውሞ አስነስቷል። ከ34ሺህ በላይ ሰዎችን በገደለው እና ግዛቱን ባወደመ የእስራኤል ዘመቻ ተጨማሪ የዜጎች ሞት እንደሚያስከትል የእርዳታ ኤጀንሲዎች አስጠንቅቀዋል። በጋዛ ሰርጥ ያሉ ፍልስጤማውያንን በሕይወት እንዲቆዩ የሚያደርገውን ከራፋህ ላይ የተመሰረተውን የሰብአዊ እርዳታ ተግባር ሊያበላሽ ይችላልም ብለዋል።
የእስራኤል ወታደሮች ለፍልስጤማዊያን ሙዋሲ ወደ ሚባል የባህር ዳርቻ ጊዜያዊ ካምፕ እንዲሄዱ ነግረዋቸዋል። እስራኤል መጠለያውን እንዳሰፋች እና ድንኳን፣ ምግብ፣ ውሃ እና የመስክ ሆስፒታሎችን ማካተቱን ገልጻለች።
ወደ 450ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ተፈናቅለው ሙዋሲ ውስጥ ተጠልለዋል። UNRWA በመባል የሚታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች እርዳታ ሲደርግላቸው ቆይቷል ብሏል።
ሲኤንኤን በበኩሉ እንደዘገበው ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ጥረት በዚህ ሳምንት አሁንም የሚቀጥል ሲሆን አንዳንድ የእስራኤል ባለሥልጣናት በምሥራቃዊ ራፋህ ላይ የተሰጠው የመልቀቅ ትእዛዝ ሐማስ አቋሙን እንዲለውጥ ጫና እንደሚያሳድር ተናግረዋል::
የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬህ በእለቱ በሰጡት መግለጫ ቡድኑ ከሸምጋዮች ጋር ቋሚ የሆነ የተኩስ ማቆም እና የእስራኤል ወታደሮችን ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ መውጣትን የሚያካትት ስምምነት ላይ ለመድረስ አሁንም ፍላጎት አለው ብለዋል ። እስራኤል በበኩሏ ሐማስ እስኪጠፋ ድረስ በጋዛ ላይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደምትቀጥል ትናገራለች።
የቀድሞ የእስራኤል ዲፕሎማት አሎን ፒንካስ “የእገታ ስምምነት የለም፤ ምክንያቱም በግልጽ የሚታይ ሁለቱም ወገኖች አንዱ አንደኛውን አይፈልጉም” ሲሉ ለ ሲኤንኤን ተናግረዋል።
ጦርነቱ በዚህ ሁኔታ ካበቃ ሐማስ በእግሩ በመቆም ብቻ ድል ሊያገኝ ሲችል እስራኤል ደግሞ እንደተሸነፈች ይቆጠራል:: ይህ ልዩነት ስምምነትን ይከላከላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀኝ እስራኤላውያን ሚኒስትሮች ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ሃሳብን እንዳይቀበሉ አሳስበዋል::
እ.ኤ.አ. በ2014 በእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ወቅት በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የእስራኤል እና የፍልስጤም ድርድር ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የሰሩት ፍራንክ ሎወንስተይን “ሁለቱም ወገኖች የሚፈልጉት የፖለቲካ ህልውናቸውን የሚያረጋግጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ብቻ ነው” ብለዋል።
እስራኤል ሐማስ እጅ ከሰጠ እና ታጋቾቹን አሳልፎ ከሰጠ ጦርነቱ ሊያቆም ይችላል ስትል ታጣቂ ቡድኑ ደግሞ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም ፤ ይልቁንም ህልውናውን የሚያረጋግጥ እና በጋዛ ላይ ቁጥጥርን የሚቀጥልበትን ስምምነት ለማድረግ መርጧል ።
ፒንካስ ጦርነቱ የኔታንያሁን የስልጣን እድሜ ቢያራዝምም እርግጠኛ መሆን ግን አይቻልም ብለዋል። በተቃራኒው እ.ኤ.አ. በሚያዚያ 15 እና 17 መካከል በእስራኤል ዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት (IDI) የተካሄደ የህዝብ አስተያየት እንዳመለከተው 58 በመቶ የሚሆኑ እስራኤላውያን ኔታንያሁ “በጥቅምት 7 ውድቀት ምክንያት ከስልጣናቸው የሚለቁበት ጊዜ ደርሷል ብለው ያምናሉ።
የእስራኤል የቀኝ አክራሪ ብሄራዊ ደኅንነት ሚንስትር ኢታማር ቤን ጊቪር እስራኤል የጦርነት አላማዋን ከማሳካቷ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ከኔታንያሁ ጥምረት እንደሚለቁ ዝተዋል።
አንድ ከፍተኛ የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣን ለሲኤንኤን ከሰሞኑ እንደተናገሩት እስራኤል ስለ ራፋህ የሰጠችው ማስጠንቀቂያ በተኩስ አቁም ንግግሩ ውስጥ ካለመሻሻል ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው ብለዋል። እስራኤል በሐማስ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከረች ነው ብለዋል ባለሥልጣኑ። በተጨማሪም ባይደን አሜሪካ እስራኤል በራፋህ ከምታደርገው ዘመቻ ጋር ተያይዞ የተወሰነ የጦር መሳሪያ ወደ እስራኤል እንደማትልክ አሳውቀዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እስራኤል በራፋህ ጥቃት እያደረሰች ትገኛለች::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም