የሕግ የበላይነት

0
190

የሕግ የበላይነት ተረጋግጠ የሚባለው የመንግሥት ባለሥልጣናት ውሳኔዎች እና የሚፈጽሟቸው ተግባራት ሕግን ብቻ መሠረት አድርገው ሲከናዎኑ መሆኑን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ይገልጻል፡

ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ የሚባሉት መንግሥታዊ አካላት የዜጐችን ሰብአዊ መብቶች እና ነፃነቶች ያለአንዳች ማወላወል ሲያከብሩ እና ዜጐችም ግዴታቸውን ሲወጡ የሕግ የበላይነት ተረጋግጧል ይባላል ብለዋል- የማዕከሉ የአስተምህሮ እና ሥልጠና ዳይሬክተር::

ዳይርክተሩ አቶ ዘውዱ ደምሴ የሕግ የበላይነትን አስመልክቶ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት የሕገ የበላይነት ከፍ አለ ለማለት ቢያንስ አምስት መሠረታዊ መስፈርቶች መሟላት ይኖርባቸዋል::

የሕዘብን እና የመንግሥትን አደራ የተቀበሉ ባለሥልጣናት ተግባሮቻቸውን በዘፈቀደ ሳይሆን የሀገሪቱን ሕግ እና ደንቦች አስከብረው ሳያዛንፉ ማከናዎን አንደኛው መለኪያ ሲሆን ሁሉም ዜጐች በዘር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋ፣ በኑሮ ደረጃ እና በሥልጣን ልዩነት ሳይደረግባቸው እንዲተዳደሩ እና እንዲዳኙ በማድረግ የእኩልነት መብታቸውን ማረጋገጥ ደግሞ ሁለተኛው መስፈርት ነው::

ሕገ ወጥነት እና ሥርዓት አልበኝነትን አስወገዶ ሰላም እና መረጋጋት የሠፈነበት ሥርዓት መፍጠርም ሌላኛው ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በሕግ ሂደት ውስጥ ያለ አድልኦ በፍትሀዊነት ለዜጐች ፈጣን አገልግሎት ከትክክለኛ እና ተገቢ ውሳኔ ጋር መስጠትም አራተኛው የሕግ የበላይነት ማሳያ ነው ብለዋል::

ዜጐች በተፈጥሮ የተቸራቸውን በሕይወት የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ ሀብት የማፍራት እና የመሳሰሉት ሰብአዊ መብቶች እንዳይገሰሱ እና እንዲከበሩላቸው ማድረግን አምስተኛው የሕግ የበላይነት ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ አቶ ዘውዱ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማንኛውም ሰው ከማህበራዊ እና መንግሥታዊ ሕግጋት በታች መሆኑን የሚያመላክተው መርህም የሕግ የበላይነትን አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል::

ማንኛውም ዜጋ እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያረጋግጠው የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ መሆኑን ያሰመሩበት አቶ ዘውዱ ይኸው መርህ በአንድ በኩል የመንግሥት እና የሕዝብ ባለሥልጣናት ስልጣናቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በሌላ በኩል ደግሞ የዜጐች መብት እና ነፃነቶች እንዲከበሩ እና ዜጐችም ግዴታዎቻቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያደርግ ድንጋጌ መሆኑን አስታውቀዋል::

ከነዚህ ድንጋጌዎች በመነሳት ታዲያ ሕግ አውጪው ፓርላማ ያወጣቸውን እና ያፀደቃቸውን ሕግጋት አፈፃፀም በመከታተል፣ ሕግ አስፈፃሚው መንግሥታዊ አካል ከቸልተኝነት፣ ከዘፈቀደ አሠራር እና ከአድሏዊነት ፀድቶ በመሥራት፣ ሕግ ተርጓሚውም ለሙያው ሥነ ምግባር ለመገዛትና ፍትህን ለማስከበር፣ ዜጐች ደግሞ ግዴታዎቻቸውን በመወጣት እና ከሥርዓት አልበኝነት በመታቀብ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን መረባረብ ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑ ሲሰመርበት ይገባል! የአሚኮ መልዕክት ነው::

(ጌታቸው ስንታየሁ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here