ነፃ ፍቅር እና መስዋዕትነት

0
558

በምዕራቡ ዓለም ሚያዝያ ወር በገባ በሁለተኛው ሳምንት እሁድ “የእናቶች ቀን” በሚል እናትን በማወደስ እና ልዩ ምስጋና በማቅረብ በድምቀት የማክበር እና የማሰብ ባህል የተለመደ ነው። የእናቶች ቀን የእናቶችን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እና መስዋዕትነት ለማክበር እና ለማድነቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ልዩ ቀንም ነው። ይህ በዓል በተለያዩ ባህሎች ውስጥ የእናቶች አማልክቶች ሲሰግዱበት ከነበረው ከጥንት ጀምሮ የሚመጣ ብዙ ታሪክ አለው።

በዘመናችን የሚከበረው  የእናቶች ቀን ግን በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከአሜሪካ የመጣ ነው። በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ሰላማዊ ታጋይ አና ጃርቪስ ይህንን ቀን እ.ኤ.አ በ1908 እንዲከበር ያደረገችው  የእናቷን አስተዋፅኦ ለማስታወስ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ከ40 የሚበልጡ ሀገራት ይህን ልዩ ቀን ያከብራሉ።

የእናቶች ቀን እንደየ አካባቢው ሊለያይ ቢችልም አብዛኞቹ ሀገራት በግንቦት ወር ሁለተኛ እሁድ ያከብራሉ። ሆኖም እንደ እንግሊዝ እና አየርላንድ ያሉት ደግሞ  ከፋሲካ በፊት ባለው በዐብይ ጾም አራተኛው እሁድ ያከብራሉ።

የእናቶች ቀን እናቶች ለልጆቻቸው እድገት እና ደህንነት የራሳቸውን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው  የሚከፍሉትን ስፍር ቁጥር የሌለው መስዋዕትነት  ለማሳየትም ነው።

በርካቶች  በእናቶች ቀን የመልካም ምኞት መግለጫ ካርዶችን ጨምሮ የተለያዩ ስጦታዎችን በማበርከት ለእናቶቻቸው ያላቸውን አድናቆት እና ፍቅር ያሳያሉ። ከዚህ በተለየም አንዳንዶች  እናቶቻቸውን ለማክበር እንደ ቤተሰብ በመሰብሰብ ልዩ ምግብ በመጋበዝ አብረው ጥሩ ጊዜ ማሳለፍን ይመርጣሉ።

የእናቶች ቀን በሕይወት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ልዩ ክስተት ነው። ብዙ ጊዜ የእናቶች ቀን በሕይወት ውስጥ በብዙ መልኩ የበለፀጉ ድንቅ ሴቶችን ለመገንዘብ እድል ይሰጣል የሚለው እ.ኤ.አ 2023 የእናቶች ቀን አከባበርን ተከትሎ የወጣው (thelearningapps.com) ዘገባ ነው ።

የእናቶች ቀን በዋናነት እናቶችን በማክበር ላይ ያተኮረ ቢሆንም በሕይወታችን እናትን በመተካት  ልጆችን ተንከባክበው ያሳደጉ የሌሎች ሴቶችን አስተዋጾ ማድነቂያም ቀን  ነው። ይህም ልጆችን የሚደግፉ እና  ለትልቅ ደረጃ ያበቁ ሴት አያቶችን፣ አክስቶችን እና ታላላቅ እህቶችን ይጨምራል።

በኲር ጋዜጣም ዘንድሮ የእናቶች ቀንን (ወር) ስናስብ የበርካታ ልጆችን ባህሪ ቀርፀው እና አንፀው ለዓለም የሚያበረክቱ የኤስ ኦ ኤስ እናቶችን ልንዘክር ወደናል::

የሰሜኑን የሀገራችንን ድርቅ ተከትሎ ለችግር ተጋላጭ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በመስጠት የዛሬ 50 ዓመት ሥራውን የጀመረውንና በኋላም ፊቱን ወደ ቤተሰብና ማህበረሰብ ልማት ያዞረው ኤስ ኦ ኤስ ከ30 ሺህ በላይ ሕጻናት እና ወጣቶች ሁለንተናዊ ድጋፍ እና እንክብካቤ ያደርጋል::

በባሕርዳር ከተማ የሚገኘው የኤስ ኦ ኤስ መንደር የዛሬ 24 ዓመት ሲመሰረት ገና በሰላሳ እድሜ መጀመሪያ  ሥራ ከጀመሩት ከወ/ሮ እናት አድማሱ ጋር ቆይታ አድርገናል::   ወይዘሮዋ እንደሚሉት ሥራ እንደ ጀመሩ ሁለት ልጆችን እንደ እናት ለማሳደግ ተረከቡ:: በሁለት ልጆች የተጀመረው የእናትነት ሕይወታቸው  ቀስ በቀስ አስር  ደረሱ::

ሴቶች ቢወልዱም ባይወልዱም በውስጣቸው የእናትነት ስሜት እንዳላቸው ወ/ሮ እናት ያምናሉ:: ወይዘሮዋ  ልጆችን እንደየ ባሕሪያቸው አንፆ ማሳደግ ብዙ ፈተና ያለው ግን ደስ የሚል ተግባር እንደሆነም ያነሳሉ::

እናትነት ቀላል የሚባል ፈተና እንዳልሆነ የሚያነሱት ወ/ሮ እናት በሌሊት ልጆች ሲታመሙ  እንቅልፍ ማጣቱ እና ባህሪያቸው ሲቀያየር መጨነቁ የቀን ተቀን ተግባራቸው  ነው:: ሥራ በጀመሩ\ ወቅት “ልጆቻቸው” ሲያለቅሱ እና ሲቸገሩ አብሮ ማልቀስ እና መከፋት ቢኖርም በሂደት ግን እናትነት ለልጆች የችግሮችን መልካሙንም ሆነ መጥፎውን ጎን እያሳዩ መውጫ መንገዱን የማመላከት ተግባር መሆኑን መገንዘብ ችለዋል:: በአጠቃላይ እናትነት ከልብ መሰጠትንም ይጠይቃል ይላሉ::

አሳዳጊ እናቶች የቤተሰብ የማዕዘን ድንጋይ ናቸውና በወደፊት በልጆች አኗኗር ላይ ጉልህ ተፅእኖ አላቸው። ልጆች በራሳቸው  የሚተማመኑ ምርጥ ሥሪት እንዲሆኑ   አድርጎ ማሳደግ   ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅር፣ ድጋፍ እና መመሪያ ይፈልጋሉ ።

ወ/ሮ እናት እንደ ሚሉት የልጆች የጉርምስና ጊዜ ደግሞ አንዳንዱ ልጅ የገጠመውን፣ ያየውን እና የተሰማውን ያወራል::   ሌላው ልጅ ደግሞ አለባበሱን፣ የባህሪ ለውጡን  እና ብቸኝነቱን ተመልክቶ በግል ማነጋገር እና ችግሩን መካፈል ይጠይቃል::

በኤስ ኦ ኤስ መንደር በሳምንት አንድ ቀን ቤተሰብ ሁሉ የሚሳተፍበት ውይይት ይደረጋል:: ልጆች ከሰዎች ጋር ማውራት የማይፈልጉትን ነገር ደግሞ በግል ማማከር እና ማውራት ፍቅርን መለገስ እንደሆነ ወ/ሮ እናት ያምናሉ::

ከመንደሩ ከወጡ በኋላ የሚገጥማቸውን ማህበራዊ ሕይወት እንዲለማመዱ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ወ/ሮ እናት ጠቁመዋል:: በመንደሩ ያሉ እናቶች ወ/ሮ እናትን ጨምሮ  ልጆቻቸውን የውጭውን የሕዝቡን እንቅስቃሴ ያስቃኙዋቸው እንደነበር ወ/ሮ እናት ያስታውሳሉ::  ይህ መሆኑ ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ  ያለውን ግራ መጋባት ይቀንስላቸዋል::

ወ/ሮእናት እንደሚያስታውሱት የመጀመሪያ ልጃቸው አዋሳ ዩንርሲቲ በገባችበት ወቅት በየቀኑ ደውላ ካላወራቻቸው እንባ እንባ ይላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ወይዘሮዋ እንደሚሉት አሁን ላይ መጀመሪያ ተረክበው ካሳደጓቸው 10 ልጆች ውስጥ ዘጠኙ ሥራ ላይ ናቸው:: ትዳር መሠርታ አዲስ አበባ ላለችው ልጃቸው ደግሞ በዓመት በርበሬ እና ሽሮ አዘጋጅተው በመላክ የእናትነት ኃላፊነታቸውን እየተው ናቸው::

ልጆች በየትኛውም እድሜ  የእናቶች ሃሳብ እና ኃላፊነት እንደሆነ የሚያነሱት ወ/ሮ እናት ብዙ ጊዜ አብረው በመቆየታቸው ፊታቸውን ተመልክተው  ስሜታቸውን መገንዘብ እንደሚቻልም ነው የገለፁት::

በየዓመቱ የእናቶች ቀንን ማክበር የማህበረሰቡን እና የቤተሰብን እሴት ለማጉላት ፣ እንደ ቤተሰብ ለመሰባሰብ እና ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናክር ያነሳሳል የሚሉት ወ/ሮ እናት፤ “ልጆቼ ብዙ ነገር የግል ፍላጎት እና ሕይወት መስዋት የከፈልኩባቸው በመሆኑ ዛሬም አድገዋል  በቃኝ  የማይባሉ ናቸው”ሲሉ አብራርተዋል::

ተምረው ሥራ ሲያጡም ከልጆቹ በላይ ወላጅን የሚያስጨንቀው “የልጆቹ ማረፊያ ምን ሊሆን ይችላል?” የሚለው የልጆቻቸው ቀጣይ እጣ ፈንታ ደግሞ የየእለት ሕይወታቸው አካል እንደሆነ ያነሳሉ:: በመጨረሻም  የእናቶች ቀን ሲከበር የእናትነት፣ የቤተሰብ እና የማህበረሰብ በሕይወታቸው  ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ እና እንድናደንቅ በመሆኑ እነዚህ ልጆችን የሚያንፁ እናቶች ልናመሰግን ወደድን።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here