አሜሪካዊው አልፍሬድ ብሌሽክ በመቶ ስድስት ዓመት ዕድሜያቸው ከረዳታቸው ጋር ተጣምረው በዘጠኝ ሺህ ጫማ ከፍታ ሲበር ከነበረ አውሮኘላን በመዝለል ዳግም ለክብረወሰን መብቃታቸውን ዩፕአይ ድረገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
በ2020 እ.አ.አ አልፍሬድ ብሌሽክ በ103 ዓመታት ዕድሜያቸው ከአውሮኘላን በመዝለል በዕድሜ አንጋፋ ዘላይን ክብረ ወሰን ይዘው ነበር:: ሆኖም ከሦስት ዓመታት በኋላ በ2022 እ.አ.አ ሲዊዲናዊቷ ሩት ሊንኒያ ኢንግጋርድ ላርሰን የተባለች ሴት በ103 ዓመት ከ259 ቀናት በሆነው ዕድሜዋ ከአውሮፕላን ተወርወራ በመዝለሏ ክብረወሰናቸውን ለመንጠቅ ችላለች::
አልፍሬድ ብሌሽክ ዳግም የተነጠቁትን ክብረ ወሰን ለማስመለስ የቴክሳስ ገዢ ከሆኑት ግሬግ አቦት ከተባሉ ሰው ጋር ተጣምረው ለመዝለል ስምምነት ላይ ደረሱ:: ይህንኑ ተከትሎ ህዳር 27 ቀን 2023 እ.አ.አ በዘጠኝ ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ከሚበር አውሮኘላን ከአጋራቸው ጋር ተጣምረው ተወረወሩ::
አልፍሬድ ብሌሽክ በአጋራቸው እየተመሩ 5500 ጫማ ላይ ሲደርሱ “ፓራሹት” ወይም ዣንጥላቸውን መዘርጋት ቻሉ:: በዚሁም የተነጠቁትን ክብረ ወሰን አሻሽለው ለማስመለስ ችለዋል::
አዛውንቱ ሲጠባበቋቸው ለነበሩ ተመልካቾች እና ጋዜጠኞች “የማትችል ከመሰለህ ራስህን ዝቅ አድርገህ ተመልክተኸዋል ማለት ነው:: እያንዳንዱ ሰው ከሚያስበው በላይ አቅም አለው:: ዋናው ነገር ለመሞከር መወሰን ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም