በባሕር ዳር ከተማ ዋና ዋና መሥመሮች የተሰማሩ ታክሲዎች እና ባለሦስት እግር/ባጃጆች/ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ ነዋሪውን እያማረረ ነው:: አቶ ዓለሙ መስፍን ከተገልጋዮች አንዱ ናቸው:: እርሳቸው እንዳጫወቱን ቤት ሠርተው አባይ ማዶ መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመታት አስቆጥረዋል:: ግለሰቡ ከበፊቱ በላቀ ማንኛውም እንቅስቃሴያቸው በታክሲ ነው::
አቶ ዓለሙ እንደሚሉት በታክሲ ሲመላለሱ በፊት ባለታክሲዎችም ሆኑ ባለ ባጃጆች ታሪፍ የሚጠይቁት መንግስት የተመነውን ክፍያ ነበር:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በከተማዋ ለአጭር እና ለረዥም ጉዞ ተብሎ የወጣውን ታሪፍ በመተው ተመሳሳይ ክፍያ ያጠይቃሉ:: መሸት ካለም የረዥሙን ጉዞ ታሪፍ በእጥፍ ያስከፍላሉ::
ተገልጋዩ አብነት ጠቅሰው ሲያስረዱ አምስት ብር ለተተመነለት አጭር ጉዞ ረዥሙ አስር ብር ከሆነ ለመክፈል የሚገደደው አስሩን ብር ነው:: መብቱን ለማስከበር ትክክለኛውን ታሪፍ እንጅ ተጨማሪ አልከፍልም ያለ እንዲወርድ ይደረጋል:: “አልወርድም! ተጨማሪም አልከፍል!“ ያለ ደግሞ ዘለፋ፣ ፀያፍ ስድብ እና ዛቻ ይወርድበታል::
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወ/ሮ ሰናይት አዘነም የአቶ ዓለሙን ሀሳብ ይጋራሉ:: “በታክሲዎች ውስጥ ከሚለጣጠፉ ጥቅሶች ውስጥ “ሞላ የሰው ስም ነው ጠጋ ጠጋ በሉ“ የሚል እንዳለ ሁሉ እርሳቸው በሚሳፈሩበት ታክሲ በብዛት ሾፌሩ እና ገንዘብ ተቀባይ “ጠጋ ጠጋ በሉ“ በማለት ሁለት ሰው መቀመጥ ካለበት ወንበር ሦስተኛ ለማስቀመጥ የተሳፋሪው መልካም ፍቃድ እና ትብብር መሆኑን ባለመገንዘብ የሚደረገው ክብረ ነክ ስድብ ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል::
በተለይ ይላሉ ወ/ሮ ሰናይት ልጆች የያዙ እና ወፍራም ሰዎችን ሲያዩ ሦሥተኛ ሠው ለማሳፈር ስለማይችሉ ያዘኑ መስለው “ቦታው አይመችሽም“ በማለት እንዳይገቡ ይከለክላሉ:: የእነሱ ምክር የገባቸው አንዳንዶች ከገቡ በኋላ ትርፍ መጫናቸው ስለሚቀር ተሳፋሪዎችን ሲገላምጡ ይደርሳሉ::
የፀጥታ እስከባሪዎችም የስርዓት ማስከበር ሥራው ቋሚ ነገር ካልሆነ ደስ ባላቸው ጊዜ ብቻ የሚያደርጉት ቁጥጥር ተጠቃሚውን ብዙም የሚያግዝ አለመሆኑን እና ወጥ የሆነ የታሪፍም ሆነ የሥርዓት ማስከበር ሥራ አለመኖሩ ባለታክሲዎች የጠየቁትን ክፍያ ለመፈፀም መገደዳቸውን ወ/ሮ ሰናይት ጠቁመወዋል:: “የትራንስፖርት ችግሩን የሚፈታ ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልጋል፤ ለዚህም ደንቡን ተከትሎ መሥራት ይገባል” ሲሉም ወይዘሮዋ ጠይቀዋል::
በባሕር ዳር ከተማ ካሉት ሦስት የሚኒባስ ታክሲ ማህበራት አንዱ አደይ አበባ ሚኒባስ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ነው:: የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም ሙጨዬ በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል ሦስቱ ማህበራት ባሉት የታክሲ መዳረሻዎች በሦስት ቀጣና ተከፋፍሎ በየሳምንቱ ዝውውር እየተደረገ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል::
ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት በማህበር ተደራጅተው ሥራ እንዲጀምሩ ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቱ አቅሙን በኢኮኖሚ እንዲገነባ፣ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ እና ለህብረተሰቡ የተሳለጠ የጉዞ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ ነው:: ይህን ታሳቢ በማድረግም ክልሉ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያወጣውን የታሪፍ ማስተካከያ በትራንስፖርት መምሪያ በኩል ለአባላት ይበተናል:: ይህን እና ሌሎችን ተያያዥ ጉዳዮች ለማስከበር ከትራፊክ ፖሊሶች በተጨማሪ ማህበራት በየመስመሩ የራሳቸውን ደንብ ተቆጣጣሪ በማሰለፍ ሥርዓት ያስከብራሉ:: “ይሁን እንጅ ለተራ አስከባሪው ከተጠቃሚው በብዛት የሚቀርበው ጥያቄ (ቅሬታ) ‘ቅርብ ወራጅ አንጭንም ተባልን’ የሚል ብቻ እንጂ ሌላ ቅሬታ ቀርቦ አያውቅም::”
እንደ አቶ አንዱዓለም ገለጻ በተሳፋሪዎች በኩል ያለው ቅሬታ መልኩን ቀይሮ በታክሲ ባለሀብቶችም ይነሳል:: አሁን ያለው ታሪፍ ለባለንብረቱ አዋጭ አይደልም፤ የትራስፖርት ፍሰቱ ጠዋት ከሁሉም አቅጣጫ ወደ መሥሪያ ቤቶች ብዙ ተጓዥ ይኖራል:: መሥሪያ ቤቶች ደግሞ አንድ አካባቢ በመሆናቸው ተመላሽ የለም:: ይህ ደግሞ ሠርቶ ቤተሰብ ለሚያስተዳድር ባለሀብት እየከሰረ እንደሚሠራ ተገልጋዩ አይረዳም::
በባሕር ዳር ከተማ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተሸከርካሪዎች ሥሪታቸው ከ1996 እስከ 1998 መሆናቸውንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል:: በዚህ ምክንያትም ታክሲዎች ካገለገሉበት ረጅም እድሜ አንፃር ቶሎ ቶሎ ወደ ጋራጅ ይገባሉ፣ ቶሎ ቶሎ መለዋወጫ ይጠይቃሉ:: በገበያ ላይ ያለው የመለዋወጫ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ደግሞ ችግሩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዳደረገውም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል::
የገበያ ጥናቱ እና ታሪፉ ናፍጣን ብቻ ያማከለ መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው ደግሞ አቶ አንዱዓለም ጠቁመዋል:: እንደ እርሳቸው ገለጻ ከናፍጣ አንፃር እንኳን ሲታይ አንዱን ፌርማታ ከሚሊኒየም ተነስቶ አዲስ ዓለም ድረስ ያለው ርዝመቱ አራት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ነው:: አሁን ያሉት አብዛኛው መኪኖች አሮጌ ስለሆኑ በአንድ ሊትር ናፍጣ አምስት ነጥብ አምስት ኪ.ሜ ድረስ ይጠቀማሉ:: ይህ ማለት በአንድ ጉዞ ብቻ 12 ሰው ቢጭን 120 ብር ያገኛል:: በዚህ ስሌት ባለሀብቱ በአንድ ጉዞ ለረዳት እና ናፍጣ ከፍሎ ትርፉ 10 ብር ብቻ ነው::
ይህን መሰረት አድርጎም ባለሃብቱ የመኪናው የመጫን አቅም የተወሰነ ቢሆንም ገቢው አዋጭ ስለማይሆን ትርፍ ሲጭን መኪናውም ይጎዳል:: ማህበረሰቡ በራሱ ፍቃድ ትርፍ ሆኖ መሳፈሩም ሌላው ሊቀር ያልቻለ ችግር መሆኑን አቶ አንዱዓለም አረጋግጠዋል::
ባለሀብቱ ከአገልግሎት አሰጣጡ አንፃር ብዙ ችግር ቢኖርም አገልግሎት መሥጠት ስላለበት ከነችግሩም ቢሆን ሥራው ሳይቋረጥ ባለው ታሪፍ እያገለገለ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል:: ዘርፉ አዋጭ ካልሆነ እና ባለሃብቱ ከሥራው ከወጣ ሌላ ችግር ስለሚሆን በደንብ አጥንቶ መደገፍ እንደሚገባም ባለሀብቱ ጠቁመዋል:: ይህን ተከትሎም ባለሃብቶች በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረቡ ስለሆነ ሳይማረሩ አገልግሎቱን እንዲሰጡ አዋጭ ታሪፍ ለማውጣት ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን አቶ አንዱዓለም ጠቁመዋል::
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት መምሪያ ተወካይ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት ባህሩ በበኩላቸው የታክሲ ታሪፍ የሚወጣው ፌዴራል እና ክልሉ ተናቦ ነው:: በተዋረድም ወደ ዞኖች ይወርዳል::
በባሕር ዳር ከተማ ያሉት ሦስት የታክሲ እና 18 የባጃጅ ማህበራት ታክሲ አንድ በሚል ዘርፍ በወጣላቸው ታሪፍ በትክክል መሥራት አለመሥራታቸውን የመንገድ ደኅንነት ሥምሪት ባለሙያ እና ትራፊክ ፖሊስ ይቆጣጠራል::
ይሁን እንጅ ሕዝቡ በወጣው ታሪፍ መገልገል እንዳልቻለ የቀረበው ቅሬታ ልክ ነው:: ባለንብረቶቹ በበኩላቸው በከተማዋ የታክሲ ፍሰቱ አንድ መሥመር መሆኑንም የሚያቀርቡትን ቅሬታ እናውቃለን:: ናፍጣ እና ቤንዚን በጠፋበት ወቅት ያለውን ሁኔታ ተገንዝበን ተገልጋዩ ከሚንገላታ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ ሕጉ ሲጣስ ዝም ማለታቸውን ተወካይ ኃላፊዋ ወ/ሮ መሠረት አስታውሰዋል::
“አሁን ባለው ሁኔታ ግን የተረጋጋ የናፍጣ እና ቤንዚን አገልግሎት ሥላለ በአጭር መንገድ ያለታሪፉ የሚያስከፍሉትን 500 ብር ከታሪፍ ውጭ ሕግ መቅጣት ተጀምሯል:: ቀበሌ 14 እና አባይ ማዶ አካባቢ የተጠቃሚ ፍሰት ሲጨምር ኮድ ሦስት ወደ ከተማ አገልግሎት ገብተው እንዲያግዙ ቢደረግም የታክሲ ማህበራት ቅሬታ ስላነሱ እንዲያቆሙ ስለተደረገ ታክሲዎች ባለው ታሪፍ ተገቢውን አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው:: ነገር ግን ዘርፉ ለባለሃብቱ አዋጭ ካልሆነ መውጣት ይችላል!”ሲሉ አስጠንቅቀዋል::
“በቀጣም ለቁጥጥር እየተወጣ በታሪፉ የማይሠሩ እና ትርፍ በሚጭኑት ላይ ክስ መመስረታችን አይቆምም:: በዘርፉ ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ደግሞ ባለሃብቶች በትራንስፖርት አገልግሎት ተሰማሩ”በማለት ጥሪ አድርገዋል:: በአሁኑ ወቅት ከተማ አስተዳደሩም ተጨማሪ ኢንተርፕራይዞች እንዲያስገባ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም