ዓለማችን በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከመጀመሪያው አጋማሽ እስከ መጨረሻዎቹ ዓመታት ድረስ ሁለት አውዳሚ ዓለማቀፋዊ ጦርነቶችን አስተናግዳለች። ከአውሮፓ እስከ ሩቅ ምሥራቅ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ በርካታ ሀገራትን በአንድም በሌላም መንገድ ያሳተፉ ከባባድ ጦርነቶች ተደርገዋል። ታዲያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተከሰተውን በቀዩ የሶቭየት ጦር እና በጀርመኑ ናዚ መካከል የተደረገውን እና የመጨረሻውን ወሳኝ ጦርነት በታሪክ አምዳችን እንዳስሳለን።
የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ለማጠናቀቅ በጀርመን እና በቀዩ ሰራዊት መካከል ተደረገውን ከባድ ጦርነት እና የጦርነቱን መቋጫ፣ የበርሊንን መሸነፍ በተመለከተ ከማውራታችን በፊት የጦርነቱን አቅጣጫ የቀየረውን አንድ ወታደራዊ ክስተት ማየት ግድ ይለናል። ይኸውም ዘመቻ ባርባሮሳ ይባላል፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሰኔ 22 ቀን 1933 ዓ.ም ላይ ጀርመን በሶቭየት ኅብረት ላይ ያደረገችው ወረራ ነው።
ጀርመን በሁለት ወራት ውስጥ ሶቭዬትን ለማሸነፍ ያቀደችው ይህ ዘመቻ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወሳኝ መታጠፊያ ሆኗል። ይህ ዘመቻ በመጀመሪያ ዘመቻ ፍሪትዝ በሚል ስም የተሰመ ቢሆንም፣ በኋላ ግን ሒትለር በአውሮፓ የጀርመንን የበላይነት ለማንገስ ይፈልግ በነበረው በሮማዊያን ንጉሥ ፍሬዴሪክ ባርባሮሳ ስም ዘመቻ ባርባሮሳ በሚል ቀይሮታል።
ጀርመን እና ሶቭየት ኅብረት በመካከላቸው የጦርነት ትንኮሳ ያለማድረግ ስምምነትን በ1931 ዓ.ም ተፈራርመው ነበር። ይህ ስምምነት አንደኛው ከሌላ ሦስተኛ አካል ጋር ጦርነት ሲያደርግ ገለልተኛ እንዲሆን የተስማሙበት ነው። በተጨማሪም ምስራቅ አውሮፓን የተከፋፈሉበት ነበር። ነገር ግን በ1932 ዓ.ም ሶቭዬት ኅብረት የባልካን ሃገራትን እና ቤሳራቢያ እና ሰሜናዊ ቡኮቪና የተባሉ አካባቢዎችን በመውረር የጀርመን ዋነኛ የነዳጅ ምንጭ ወደ ሆነው የሮማኒያውያን የነዳጅ ማውጫ አካባቢ መጠጋቷን ተከትሎ ሒትለር የሶቭየትን መንግሥት መጠራጠር ጀመረ እና ሶቭዬትን የመደምሰስ የቀደመ ፍላጎቱ እንደገና ጨመረ። ሒትለር የሶቭዬቱን ጆሴፍ ስታሊንን አካሄድ ክፉኛ ተጠራጠረው፡፡ እናም የሶቭዬቱን ጉዳይ እልባት ሳይሰጥ በፊት ምእራብ አውሮፓን የማንበርከክ የመጀመሪያ እቅዱን እስኪያጠናቅቅ መጠበቅ እንደማይችል ተሰማው። እናም ሒትለር በሙሉ አቅሙ ሶቭዬቶች ባልተዘጋጁበት እና ባልጠበቁት ሁኔታ ዘመቻ ባርባሮሳን ሲጀምር ስምምነቱ ተጣሰ።
በሶቭዬት ላይ ለሚደረገው ዘመቻ ጀርመኖች ከሦስት ሚሊየን ያላነሰ ሰራዊት ያላቸው ወደ 150 ክፍለ ጦሮች አዘጋጅተው ነበር። ከእነዚህ መካከል 19ኙ የጀርመን ብረት ለበስ ክፍለ ጦሮች የነበሩ ሲሆን በድምሩ 3000 ታንኮች፣ 7000 የከባድ መሳሪያ ምድቦች፣ እና 2500 ተዋጊ ጀቶች ነበሩበት። ይህ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቁ እና ሃይለኛው ወራሪ ሀይል ተብሎለታል። የሶቭዬት ታንኮች እና ተዋጊ ጀቶች ከጀርመኖች ሁለት ወይም ሦስት እጥፍ ቢሆንም ተዋጊ ጀቶቹ ግን ያረጁ ያፈጁ ነበሩ። የሶቭዬት ታንኮች ግን ከጀርመኖች ጋር አቻ ለአቻ ናቸው።
ጀርመኖች ለሶቭዬት የሰጡት ግምት ግን አናሳና የተሳሳተ ነበር። አስፈሪው የጀርመን ሰራዊት ድንገት የጀመረው ወረራ ለሶቭዬት ሰራዊት ዱብ እዳ ነበር። በዚህ ፈጣን ወረራ መጀመሪያ ላይ የጀርመን ግዙፍ ሰራዊት የቀዩን ሰራዊት እያሳደደ በርካታ ከተሞችን ተቆጣጠረ። የሶቭዬት ወታደሮች ፈጣን የነበረውን የጀርመን አስፈሪ ሀይል ለመቋቋም ስለተሳናቸው ለማፈግፈግ ተገደዱ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሶቭዬት ወታደሮች በጀርመኖች ተማረኩ። በወቅቱ የጀርመንን ሰራዊት የሚቋቋመው ኃይል ያለ አይመስልም ነበር።
ሞስኮን በማያጠራጥር መልኩ እንደሚቆጣጠር ተማምኖ የሚገሰግሰው የጀርመን ጦር ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለማጠናቀቅ ዘመቻውን አጣደፈው። በተሻለ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ብልጫ በድል የሚጓዘው የሒትለር ሰራዊት ከሞስኮ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እስኪደርስ በብርታት እየተዋጋ ዘለቀ። ነገር ግን እንደታቀደው ሞስኮን በአጭር ጊዜ የመቆጣጠር እቅዱ አስከፊው የሶቭዬት ክረምት ከመግባቱ በፊት መቅደም አልቻለም። ምክንያቱም ሞስኮን መቆጣጠር በሚያስችለው አካሄድ ላይ በጀርመን ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች መካከል የተነሳው ውዝግብ ግስጋሴውን አዘገየው። እናም በዚህ መካከል አስከፊው የሶቭዬቶች ክረምት ገባ። የጀርመን ጦር በጥቅምት እና በኅዳር ወራት ቀድሞ ከገባው ከባድ የክረምት በረዶ የቀላቀለ ውሽንፍር እና ሞስኮን ለመከላከል ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በገነባው ጠንካራ ምሽግ ውስጥ በተጠንቀቅ ከቆመው የሶቭዬት ጠንካራ ሰራዊት ጋር የተፋጠጠው የጀርመን ሰራዊት የጦርነቱን ከባድ ፈተና ተጋፍጧል። የሚጋረፈው የበረዶ ውሽንፍር፣ የክረምት አልባሳት ያልቀረበለትን የጀርመን አብዛኛውን የሰራዊት አባል ክፉኛ አሽመደመደው። ብርዱን ተከትሎ በተከሰቱ የጤና እክሎች ብዙ ወታደሮች ሞቱ። ይባስ ብሎ የጀርመን ሜካናይዝድ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎች፣ ታንኮች፣ ከባድ መሳሪያዎች፣ እንዲሁም ተዋጊ ጀቶች ሽባ ሆኑ። በተቃራኒው ደግሞ የሶቭዬት ወታደሮች ከጀርመኖች በበለጠ የክረምት ልብስ በመልበስ በክረምቱ በተሻለ ሁኔታ ለመዋጋት ዝግጁ ነበሩ። የጀርመን ጦር የስንቅ አቅርቦት የሚያገኝበት እድሉ መዘጋጋቱ ነገሩን በእንቅርት ላይ… እንዲሉ አድርጎታል።
ቀዩ ጦር የከፈተው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የክረምቱ ሁኔታ የከበደውን በቆፈን እጅ እና እግሩ የተሳሰረውን የጀርመን ሰራዊት አፍረከረከው። ጀርመኖች ወደፊት ለመግፋት ቢሞክሩም አቃታቸው። ብቸኛው አማራጭ የሚመጣውን ሁሉ መጋፈጥ ብቻ ነበር። ቀዩ ጦር ከጉዳቱ አገግሞ እና በአዲስ ሀይል በአዲስ መነሳሳት ተደራጅቶ አዲስ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በመክፈት ቀደም ሲል ጀርመኖች የያዟቸውን ግዛቶች ከማስመለሱም በላይ የጀርመንን ወታደር በወጣበት እንዲቀር አደረገው። የጀርመን ጦር በተሳሳተ የውጊያ ስሌት እና ለጠላት በሰጠው አናሳ ግምት የተነሳ ከባድ ዋጋ ከፈለ።
የቀዩ ሰራዊት በጀርመኖች ላይ በፊት የተወሰደበትን የበላይነት መልሶ በማግኘት የወደፊት ግስጋሴውን የሚቋቋም ምንም ኃይል ያለ አይመስልም። በክረምት ውጊያ ጥርሳቸውን የነቀሉትን የሳይቤሪያን ወታደሮች ጭምር ያሳተፈው የቀዩ ሰራዊት መጠነ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ጀርመኖቹን እየጠረገ ወደ ፊት እንዲገሰግስ መንገዱን ፍንትው አድርጎ ከፈተለት።
በዘመቻ ባርባሮሳ ወቅት ሞስኮን ለመከላከል ምንም እንኳ የሚሊዮኖችን የሶቭዬት ወታደሮች ሕይወት ያስከፈለ እንዲሁም በርካታ የሶቭዬቶችን ከተሞች ያወደመ ጦርነት የተካሄደ ቢሆንም የጀርመኖች ሶቭዬትን ማሸነፍ አለመቻል በጀርመን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ስብራት አስከትሏል።
በሰኔ ወር 1936 ዓ.ም የህብረ ብሔሩ ጦር ፈረንሳይን ከናዚ ወረራ ለማዳን ያደረገው ስኬታማ ወረራ የአሜሪካን እና የእንግሊዝን ሀይሎች የጀርመንን ይዞታዎች መቆጣጠር እና በእነ ጀርመን ወገን የተሰለፉ ሀይሎችን ወደ ኋላ እንዲመለሱ ጫና ማድረግ አስችሏቸዋል። በተመሳሳይም በጆሴፍ ስታሊን የሚመሩት ሶቭዬቶች ወደ ምስራቅ አውሮፓ ዘመቻ ጀምረው ነበር። በዓመቱ መጨረሻ ላይ ቀዩ ጦር ናዚ ጀርመንን ለማጥፋት ወደ በርሊን ዘመተ።
በሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም የጀርመን ሰራዊት የሶቭዬትን ግዛት ከወረረ ሦስት ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው፣ ቀዩ ጦር ዘመቻ ባግሬሽን የተባለ ወታደራዊ ዘመቻ ከፈተ። በዘመቻ ባግሬሽን የተሰየመው መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ በምስራቃዊ ግንባር በኩል የሚደረግ ሲሆን ዓላማው ባንድ ወቅት ከሞስኮ አፍንጫ ስር መድረስ ችሎ የነበረውን የናዚን ኃይል ማንበርከክ ነበር።
የቀዩ ጦር ወደ በርሊን ግስጋሴውን አጠናክሮ ቀጠለ። ነገሩን ያከፋው ሒትለር ሰራዊቱ ነገሩ ከማርፈዱ በፊት በጊዜ ለቅቆ ከእልቂት ራሱን እንዲያድን አለመፍቀዱ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ከባድ ዋጋ አስከፈለው። የቆዩ ጦር ወደ ሚንስክ አካባቢ እየተጠጋ በመጣበት ጊዜ አራተኛው እና ዘጠነኛው የጀርመን የጦር ክፍሎች ተደመሰሱ። እንዲሁም ሦስተኛው የብረት ለበስ ምድብተኛ ሰራዊት ከባድ የሶቭዬቶች ምት አረፈበት። ቀዩ ጦር ወደ ፊት ግስጋሴውን ጨመረ።
ቀዩ ጦር የጀርመን ሰራዊት ወርሯቸው የነበሩ አያሌ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራትን ነፃ እያወጣ ግስጋሴውን ወደ በርሊን ቀጠለ። እነ ፖላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ሀንጋሪ የመሳሰሉ ከተሞችን ነፃ በማውጣት በምስራቅ አውሮፓ የበላይነቱን እያሳየ የሒትለርን አገዛዝ እየደመሰሰ ለመጨረሻው ጦርነት ግስጋሴውን ቀጥሏል።
ይህ በእንዲህ እያለ ስታሊን ከአሜሪካው አቻቸው ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት እና ከእንግሊዙ ዊንስተን ቸርችል ጋር ክሪሚያ በምትገኘው የልታ ከተማ ውስጥ የካቲት ወር 1936 ዓ.ም ጦርነቱን በሚያጠናቅቁበት ጉዳይ ለመምከር ተገናኙ። ሶቭዬቶች እያደረጉት ያለው የድል ግስጋሴ ስኬታማ የሆነበትን ምስራቅ ጀርመንን የመቆጣጠር ኋላፊነት ተሰጣቸው። በተመሳሳይም የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ወታደሮች ምእራባዊውን የጀርመን ክፍል እንዲቆጣጠሩ ክፍፍል ተደረገ። በየልታ ክፍፍሉ ሲፈፀም የበርሊን ከተማ በሶቭየቶች ክልል ውስጥ ነበር። እናም ለሁለት እንድትከፈል ተስማሙ።
የመጨረሻው በጀርመን እና በሩሲያ መካከል የሚደረገው ፍልሚያ የተከፈተው ሚያዝያ 8 ቀን 1937 ዓ.ም ንጋት ከመግባቱ በፊት ነበር። የሶቭዬት መድፈኛ እና የታንከኛ ምድብ ከበርሊን 40 ማይሎች ርቀት ላይ ሆነው የከተማዋ መሰረት እስኪነጋነግ ድረስ ደበደቧት። የጀርመን ወታደሮች የከባድ መሳሪያ ድብደባውን ለማስቀረት ወደ ኋላ እንደማፈግፈግ አሉ እና ፀንተው በመቆም ለመከላከል ተሟሟቱ። ነገር ግን ሞስኮን እንደታደጋት የሚሞካሸው ማርሻል ጆርጂ ዙኮቭ በሚመራው ግንባር በኩል የተቃጣውን ድንገተኛ ከባድ ጥቃት መቋቋም አልቻሉም።
“በመንጋ ወደ እኛ መምጣታቸውን አላቆሙም፡፡ የሕዝብ ማዕበል ተፈራረቀብን” ሲል የተመናመነው የዘጠነኛው ሰራዊት አንድ የጀርመን አዛዥ ሲናገር፣ “የእኔ ወታደሮች ጥይት እስክኪጨርሱ ድረስ ይዋጉ ነበር” ሲል አከለ፣ “ ከዚያም ሙሉ በሙሉ ተሸነፉ።” በደቡብ በኩል በማርሻል ኢቫን ኮኔቭ የሚመራው የመጀመሪያው የዩክሬናውያን ግንባር አራተኛውን ምድብ የጀርመን ታንከኛ ጦር አዳክመው። ሁለቱ ማርሻሎች በርሊንን ቀድሞው በመያዝ ከስታሊን የተገባላቸውን ሽልማት ለማግኘት ይሽቀዳደሙ ነበር። ማርሻል ዙኮቭ አቋራጭ መንገድ ነበረው እና ቀድሞው በርሊንን ተቆጣጠረ።
ሚያዝያ 18 ቀን 1937 ዓ.ም ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የሶቭዬት ወታደሮች ሒትለር ወዳለበት ስፍራ ወደ መካከለኛው በርሊን ሀይለኛ ጥቃት ጀመሩ። የበርሊን የመጨረሻ ምሽግ ጠባቂዎች፣ ልዩ ኮማንዶውን በብዛት ታዳጊዎች እና በእድሜ የገፉትን የሕዝብ ሚሊሻ በከተማዋ ጎዳናዎች እና በየቱቦው መሽገው እስከ ሞት ተናነቁ። ብዙዎች አለቁ። ሒትለር ራሱን አጠፋ፤ በርሊን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደቀች። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አለቀ።
በመረጃ ምንጭነት፣ Office of the historians, Rayal united institutions. journal, .Britanica, .History.comnን ተጠቅመናል፡፡
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም