ይህም ያልፋል

0
282

በየትኛውም ዘመን  የሰው ልጆች ከፈተናዎች እና መከራዎች ውጪ ደስታን ብቻ ሲያጣጥሙ የኖሩበት ዘመን የለም:: ሀዘን እና ደስታ፣  ፍቅር እና ጥላቻ፣ ማጣት እና ማግኘት፣ ሳቅ እና ለቅሶ፣ ሰላም እና ጦርነት በሰው ልጆች ኑሮ ተፈራርቀው ይመጣሉ:: የትኛው፣ መቼ፣ በምን አግባብ እንደሚመጣ ለሰው ልጅ ማወቅ አለመቻሉ ደግሞ ነገሮችን ከቁጥጥር ውጪ ያደርግበታል:: ሕይወት  ሁልጊዜም ቢሆን ሁለት አንጻሮች ወይም ገጾች አሏት:: በራሱ በሰው ልጅ ውስጥም ቢሆን ጥሩ እና መጥፎ የሚባሉ ሁለት ማንነቶች አሉ:: ብርሃን እና ጨለማ መሳይ ውስጣዊ ማንነቶች በሰው ልጅ ውስጥ አብረው ይኖራሉ::

ያፍታ አንድሪያ ሚዲየም ዶት ኮም ላይ ባስቀመጠው ጽሑፍ ነገሮች ሁሉ ሁለት አንጻሮች አላቸው የሚለውን የሚያጠናክር ጉዳይን በምሳሌት ያነሳል:: አንድ ማይክ የሚባል ተዋናይ አለ እንበል:: ቆንጆ ነው፣ ታዋቂ፣ ሀብታም፣ በትወና አቅሙ የተመሰከረለት ነው:: ሰው ሁሉ የሚወደው እና እሱን በሆንሁ ብሎ የሚቀናበት ዝነኛ ነው:: በዓለም በርካታ አድናቂዎች አሉት፤ እሱ ግን ደስተኛ አይደለም:: በርካታ ቁጥር ያላቸው ጠላቶች ደግሞ አሉት:: ለምን ጠላቶች በዙበት? ይህ ታሪክ “ዛፎች ይበልጥ ባደጉ እና ፍሬ ባፈሩ ቁጥር ነፋስ ይበረታባቸዋል” የሚለውን ያስታውሰናል በማለት  ያፍታ አንድሪያ ያስረዳል::

ሕይወት ወጀብ ነው:: የሰው ልጅም በምድር ፈተናን እንዲጋፈጥ ተፈርዶበታል:: ይህንን ወጀብ በአምላኩ የሐሳብ ጥላ ስር ሆኖ እንዲያልፍ ታዝዟል:: የሕይወት ወጀብ መምጣቱን የሜቲዎሮሎጂ ባለሙያዎች አይነግሩንም::

ኑሮ ዳገት እና ቁልቁለት ነው:: አሁን የደስታ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ብንሆንም ከደቂቃዎች በኋላ  በጥልቁ የሀዘን ሸለቆ ውስጥ ልንገኝ እንችላለን:: በሕይዎት ላለመሸነፍ የሚደረግ የበልቶ ማደር እና አሻራን በምድር ላይ የማስቀመጥ ጽኑ ጉጉት በሁለት የሕይወት አንጻሮች ውስጥ እንድናልፍ ያስገድደናል:: በአሜሪካ የሚገኘው የኢንተርኔት ትምህርቶችን የሚሰጠው ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒፕልስ ይህ ስሜት የአንተ ወይም የአንቺ ብቻ አይደለም ይላል:: ይልቁንስ የሰው ልጅ ሁሉ የሚቀበለው ገሀድ ነው እንጂ:: የሰው ልጅ ይበልጥ ለማሸነፍ በታገለ መጠን ፈተናዎች እና ወጀቦች ይበዙበታል:: ያልተፈነ ደግሞ ማለፍ አይችልም:: ፈተናውን በብቃት እና በጥንካሬ ያለፉት ሰዎች የስኬት ማማ ላይ ይደርሳሉ:: ፈተናዎችን የማያልፍ ትውልድ ውድቀቱ የከፋ ነው:: በዚህ አሸናፊዎች ጸንተው አሻራቸውን በሚያስቀምጡበት ዓለም ተሸናፊ ቦታም አሻራም የለውም:: ፈተና የማይቀር ምድራዊ እጣ ከሆነ ደግሞ ጫናውን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል የሚለውን ጉዳይ መመልከት ተገቢ ነው:: ይህም በመናወጥ ጊዜ በጽናት ለመቆም ጉልበት ይሰጣል::

ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒፕልስ ሁሉም ሰው ፈተናዎችን ሚወጣበት የራሱ ስልቶች ቢኖሩትም እንኳን ውስን ነጥቦችን ተከተሉ ይላል:: የመጀመሪያው በእቅድ መኖር ነው:: ነገሮች በማይተነበዩበት ዓለም ውስጥ በእቅድ መኖር መልካም ነው:: አቅዶ መኖር በነፈሰ ነፋስ ላለመወሰድ እና በምርጫ ለመኖር ትልቅ ሀብት ነው:: ብዙዎች ባለማቀዳቸው በሰዎች እቅድ ውስጥ ደክመው እና ተሰላችተው ያልፋሉ:: ሰዎች ለራሳቸው አኗኗር ካላቀዱ ሌሎች እንዴት እንደሚጠቀሙባቸው ያቅዳሉ:: ወይም ተመቻችተው ይጠብቋቸዋል። ብልሆች በእቅዳቸው ይመሯቸዋል:: የሚፈልጉትን ሐሳብ ይጭኑባቸው እና ሕይወታቸውን እረፍት የለሽ እና በማይታለፍ ፈተና ውስጥ ይጥሏቸዋል:: የራስህ ስሜት ማድመጥ፣ የራስን ተግባር መከወን ፈተናዎችን ለማለፍ አንዱ መፍትሔ ነው::

ስሜቶቻችሁን ተረዱ ብሎ ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒፕልስ በማስቀጠል ይመክራል:: ስሜትን በመደበቅ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም እንዲያውም የበለጠ ውስብስብ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊገኝ ይችላል:: በዝምታ የተያዘ አጥፊ የታፈነ ስሜት ጭንቀትን አሳድጎ ለበሽታ  ሊዳርግ ይችላል::

ትልቅ ማሰብ ቀጥሎ ሚመጣው ጉዳይ ነው:: ትንሽ ማሰብ በሙከራ የሚመጣን ውድቀት ላለማየት ሊጠቅም ይችል ይሆናል:: ብዙዎች ውድቀትን ስለሚፈሩ ትናንሽ ሐሳቦች ላይ ይጠመዳሉ:: ትልቅ ተግባራትን መከወን የሚፈልጉ ስዎች ስለሚመጡባቸው አደጋዎች ተዘጋጅተው መላ አበጅተው የሚታገሉ ናቸው:: ትልቅ ነገሮች ላይ ያተኩራሉ ደግሞም ያሳኳቸዋል:: የትኛውም ፈተና ሊያጋጥማችሁ ቢችል  ትልቅ አስቡ፣  ትልቅም ዓልሙ ይላል::

ሪቻርድ ገሪሃልቫ በአሜሪካ የአስተዳደር እና የሕይወት ክህሎት ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል:: ሁላችንም ፈተናዎች ቢኖሩብንም ፣ ፈተናዎችን የምንቀበልበት እና የምንፈታበት መንገድ ልዩነቱን ይፈጥራል ይላል:: ብዙዎችም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስናልፍ የበለጠ ጠንካራ እንሆናለን ብለው ያስባሉ:: እውነትም የሰውን ልጅ ጠንካራ አድርገው የሚሞርዱት የሚያልፍባቸው ጎርበጥባጣ አስቸጋሪ መንገዶች ናቸው:: የማሰብ ተፈጥሮ እንደተቸረው የሰው ልጅ ፈተናዎች እና አስቸጋሪ ጊዜያት ሲገጥሙን መውጫ መንገድ አንፈልጋለን:: ያ የማሰብ መንገድ የሕይወታችንን ቅርጽ  ይሰራዋል:: በየጊዜው አስቸጋሪ ሁኔታዎች እና ፈተናዎች ይገጥሙናል:: ያ ደግሞ  ፈተናዎችን የመቀበል፣ የመረዳት እና የመፍታት ጥንካሬታችንን ያዳብረዋል:: ለዚህ ነው ሪቻርድ ገሪሃልቫ “ፈተናዎች በተደጋጋሚ የሚገጥሟቸው ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ስኬታማዎች ናቸው” የሚለው:: ፈተናዎችን የማለፍ ክህሎት እና ችሎታን በጉዧቸው ያዳብራሉ:: “ፈተናዎች ሲገጥሟችሁ የመለወጥ እና የማደግ እድል እንደመጣላችሁ ተረዱ” ይላል ሪቻርድ ::

ደራሲት እና የስኬት መንገድ አሰልጣኟ አዊልዳ ሪቨራ ላይፍ ሃክ ድረገጽ ላይ ባሰፈረችው ጽሑፍ “በሕይወት ሁልጊዜ መሻሻል አለ፣ዓለም በቃኝ ያለው የገዳም መነኩሴ እንኳን ራሱን ለማሻሻል ይታገላል::መታገል ደግሞ የተሻለ ሰው ለመሆን ያግዛል” ስትል ትመክራለች:: ፈተናዎች ለሰው ልጆች መሻሻል የሚሰጡ እድሎች ስለመሆናቸውም ጽፋለች:: አዊልዳ  የሰው ልጆች በሕይወት የሚገጥሟቸውን ስድስት ፈተናዎች ዘርዝራለች:: ማጣት፣ ውድቀት፣  መሰናክሎች፣ የሞራል ጥያቄ፣ ታሪክን መቀበል እና አዕምሮን መቆጣጠር ዋናዎቹ የሰው ልጅ በኑሮው የሚፈተንባቸው ጉዳዮች ናቸው ትላለች:: ስራህን ብታጣ፣ ጥሩ አጋጣሚዎች ቢያልፉህ፣ ፍቅረኛሽ ቢለይሽ ወይም ሌሎች ነገሮችን  ብታጪ፣ በሕይወት ከማይቀሩ ነገሮች መካከል ማጣት አንዱ መሆኑን ያስገነዝብሻል:: በምንም ሁኔታ ውስጥ ይሁን ማጣት በህይወት ትልቁ ፈተና ነው:: ድንገቴ ዱብ እዳ ቢሆንም እንኳን ማጣት በሕይወት ወደ ፊት ይዘነው መቀጠል ያለብን ምን እንደሆነ እንድናስብ ያነቃናል:: ምናልባት በማይገባን ቦታ፣ በማይመጥነን ደሞዝ፡ በማንወደው ስራ፣ በማናመሽበት ቤትም እያረፋፈድን ሊሆን ይችላል:: “የያዝከውን ወይም የምትወደውን ስታጣ   የማንቂያ ደወል እየተደወለልህ ነው” የምትለው አዊልዳ ማጣት የነበረህ ነገር ዋጋው ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር የምትመዝንበት እናም ለእኔ የተሻለ ነገር አለ የሚለውን እንድትገነዘብ ያደርግሃል ብላለች::

በሕይወቱ አንድ ፈተና ብቻ የገጠመው አንድ ሰው ተፈልጎ አይገኝም:: የሰው ልጅ በፈተናዎች ውስጥ ነው ማንነቱ ሚሰራው:: ሰው ሲወድቅ ውሳኔው እና ድርጊቱ እንዴት እንደነበር ተመልሶ የመገምገሚያ እድል ያገኛል:: ይህም ከውድቀት በኋላ በአዲስ መረዳት እና ጉልበት የመጓዘ እድል እና ስሕተቶችን እንዳንደግም ያግዘናል::

የሰው ልጅ በሕይወቱ ሙሉ ይቅርና በቀን ውሎው ባሰበበት፣ በጀመረበት፣ በተናገረበት እንዳይጨርስ የሚያደርጉት እንቅፋቶች ያጋጥሙታል:: በዓላማችን መሐል የሚደነቀሩ፣ በሐሳባችን ጣልቃ የሚገቡ፣ በኑሯችን እንቅፋት የሚሆኑብንን ነገሮች ለይቶ መራመድ የተሻለ ሰው ለመሆን እና በልጦ ለመገኘት ያስችላል:: እንቅፋቶች እንደ መከራ ሳሆን እንደ እድል መወሰድ አለባቸው::

የሰው ልጅ ለራሱ ሕይወት የሚጠቅም እና የሚጎዳውን ለይቶ ሞራል በሚባል መርህ ውስጥ መኖር እና አለመኖሩ ሌላው የህይወት ፈተና ነው::  ዛሬ የአንድ ርዕዮተ ዓለም ደጋፊ የነበር ሰው ነገ ደግሞ የሌላ ደጋፊ ትናንትን ነቃፊ ይሆናል:: በሀገራችን ብዙዎች በተለያዩ ርዕዮተ ዓለም እሳቤዎች ውስጥ አልፈዋል:: ንጉሣዊ ስርዓት፣ ደርግ፣ ኢህአዴግ፣ ብልጽግና በሚባሉ የመንግሥት ሥርዓታት ውስጥ አንድ ሰው ሊያልፍ ይችላል:: ሐሳብን መለወጥ፣ የደገፉትን መቃወም የግለሰቦች መብት ነው:: ቁም ነገሩ ለሕይወት የሚጠቅምህ የቱ ነው የሚለው ነው:: በሕይወት መሻሻል ማለትም እውነት እና ስሕተት የሆነውን ለይቶ መራመድ ነው:: ብዙዎች በእምነታቸው እና እሴታቸው ታጥረው ይቀራሉ:: እነዚህ እሴቶች ከግለሰብ ዓላማና ግብ ጋር ተስማምተው እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል:: ካልሆነ መጨረሻው ዘመን ላይ የባከንንበትን ውጤት አልባ ዘመን እንረግማለን::

የኋላ ታሪክ የሌለው ሰው የለም:: በተለይ ልጅነት  ላይ የተፈጠሩ ክስተቶች ጥሩም ይሁኑ መጥፎ አብረው ይጓዛሉ:: የአንድ ቀን አጋጣሚዎች የታሪካችን አካል ይሆናሉ::

የስኬት መንገድ መውደቅ፣ ስሕተት መስራት እና  ፈተናዎችን በመጋፈጥ ማለፍን ይጠይቃል:: ሳትወድቅ ልታልፍ አትችልም:: የስኬትን ልምድ እና እውቀት የምታገኘው ከዚህ ነውና:: ብዙዎች ስኬታማ ሰዎች አያሌ ጊዜ ወድቀዋል:: ከውድቀታቸው ተነስተው መንገዳቸውን አስተካክለው የሚፈልጉበት የከፍታ ጫፍ ደርሰዋል:: ቤተርአፕ ዶትኮም እንደሚለው አዎንታዊ አመለካከት መገንባት ለሚገጥሙን የሕይወት ፈተናዎች መሻገሪያ ድልድይ ሆኖ  ይጠቀሳል:: በፈተና ጊዜ  ይህም ያልፋል በሚል ለማሰብ አዎንታዊ አመለካከት መገንባት ተገቢ ነው:: ራስን ተመሳሳይ መልካም ዕይታ ባላቸው ሰዎች ዙሪያ ማድረግ፤ ይሆናል እና ይቻላል በሚሉ ሰዎች መከበብ ፈተናዎችን እንድንሻገር ይረዳናል:: ነገሮችን በሚዛን የሚመለከቱ እና መፍትሔ ተኮር ሰዎች ጉልበት እና ጥንካሬን ይሰጣሉ:: በተጨማሪም ጨለምተኛ ሰዎች ሐሳባችንን እንዳይበርዙት ለመከላከልም ጠቃሚ ነው:: ሊያሣኩት የሚፈልጉትን የሕይወት ግብ መቅረጽም በፈተናዎች የማይመለስ ጥንካሬን ያላብሳል::

እ.ኤ.አ ከ1940 እስከ 1945 ታላቋ ብሪታኒያን የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርቺል ባሉት ሐሳብ የዛሬውን ጽሑፍ አበቃለሁ:: “ጨለምተኛ ሰዎች በሁሉም እድሎቻቸው ውስጥ ፈተናዎችን ያያሉ፤ ተስፈኛ ሰዎች በእያንዳንዱ ችግሮቻቸው ውስጥ እድሎችን ያያሉ”

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here