የተስፋዉ ቀን እንዲነጋ የጠብ መንጃ ላንቃ ይዘጋ!

0
142

በሕግ ሰዎች ዘንድ “የዘገየ ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል” ይባላል። ፍትሕ በጊዜ መወሰን ይኖርበታል።  ፍትሕ በዘገየ ቁጥር የብልሹ አሠራር በር እየተከፈተ፣ ለፍረጃ እና ጥርጣሬ አጋላጭ እየሆነ ይሄዳል። ግጭትም አድሮ በዋለ ቁጥር የሰው ሕይዎት እየጠፋ፣ ሐብት እየወደመ፣ ቁርሾው እየጨመረ ጠባሳው እየሰፋ የመሄድ ዕድሉ ሰፊ ነው።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ በጥበብ፣ በአስተውሎት፣ የችግሩን ልክ እና አድማስ በመረዳት  በአሳማኝ  ሁኔታ ለመፍታት ዳተኝነቶች ተስተውለዋል። እስካሁን የተሞከረው ሰላምን በጠብ መንጃ አፈሙዝ ለማምጣት ነው። በዚህ መንገድ ደግሞ ማንም አሸናፊ አይሆንም። ምክንያቱም ጦርነቱ የርስ በርስ ነውና።  ሟችም ገዳይም፣ ተሸናፊም አሸናፊም፣ አሳዳጅም ተሳዳጅም እኩል ወገን ናቸው። ልዩነቱ የፖለቲካ አረዳድ እና አሰላለፍ ብቻ ነው። ዛሬ በጥላቻ ምክንያት እውነት፣ ምክንያት እና ጥበብ  የተሸፈኑ ቢመስሉም፣ ነገ ሁሉም ወገን ወደ ቀልቡ ሲመለስ ግን ይሄ ጦርነት ባደረሰው ጥፋት መቆዘሙ አይቀርም።

ሀገራችን  የኢትዮ ኤርትራውን ጦርነት ጨምሮ እስከ ሰሜኑ ጦርነት ትርጉም አልባ ጦርነቶችን አድርጋለች። በእነዚህ ጦርነቶች ሀገር እና ሕዝብ ምን አተረፉ? ቢባል ከትርፉ ይልቅ ኪሳራውን መጥቀስ ይቀላል። በአማራ ክልልም እየተካሄደ ያለው ትጥቅ አዘል ግጭት ንፁሃንን ከማሰቃየት፣ ኢኮኖሚን ከማውደም፣ በመንግስት እና በሕዝብ መካከል ተቃርኖን ከማስፋት፣ ተቋማትን ከማውደም የዘለለ ትርጉም አይኖረውም።  የተሻለ መፍትሄ የነበረው ከልብ እና በሀቀኝነት ነገሩን ሳያቃልሉ እና ሳያጣጥሉ መነጋገር፣ መደራደር፣ ይቅር መባባል፣ ጠንካራ አመራር መስጠት፣ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ነበር። ያ ሳይሆን ቀርቶ አሁን ግጭቱ አስረኛ ወሩን ሊደፍን የቀረው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ናቸው።

ከዚህ በኋላስ?  ውጊያውን ማስቀጠል ወይስ መነጋገር?  በአስቸኳይ አዋጅ መቀጠል ወይስ ወደ መደበኛ መንግሥታዊ አስተዳደር መመለስ? አሁንም ውጊያውን አፋፍሞ መቀጠል ወይስ የጠረጴዛ ፖለቲካ መጀመር? በውጊያስ  ሰላምን ማዝለቅ ይቻላል ወይ? የሚሉት እና መሰል ጥያቄዎች በሕዝቡ ዘንድ የሚጠየቁ ጥያቄዎች መሆናቸው አይቀርም።  በአማራ ክልል  ከከተማ ከተማ፣ ከገጠር ከተማ፣ ከከተማ ገጠር ለመንቀሳቀስ  የሰላሙ ሁኔታ አስቸጋሪ ከሆነ  ወራት ተቆጥረዋል። ወደ ወረዳ ቀበሌዎች መውረድ ደግሞ ይብስ ከባድ ሆኗል። ትልልቅ ከተሞችም ሳይቀሩ ከስጋት ነፃ አይደሉም። በትክክል የስጋቱን ሁኔታ ለተመለከተው ነገሩ በንግግር ካልተቋጨ  ነገም አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸው የሚቀር አይመስልም።  ደመሰስኩት! አጠፋሁት፣ ማረክሁት! እንዲህ ሆነ! እንዲያ ሆነ!… የሚለው ፖለቲካዊ ንግግር  የዘላቂ ሰላም መሰረት አይሆንም። ሀገር እንዲህ ዓይነት ነገር ባጋጠማት ጊዜ  ጥበብ የተሞላበት ንግግር፣ ውይይት፣ ሁሉንም ወገን ያካተተ ድርድር እና እርቅ እንጅ ቁርሾ አዋላጅ መግለጫ እና ተግባር ለሕዝብም አይጠቅምም።  በመሆኑም  አሁንም ሳይዘገይ አቀራራቢ፣ አግባቢ እና ተስፋ ሰጭ ንግግሮች፣ ድርድሮች፣ ውይይቶች፣ መሸማገሎች ያስፈልጉናል።

ሕዝባችን በጦርነት ሞራሉ ዝሏል፤ ቅስሙ ተሰብሯል።  ከራስ ወደ ራስ በሚተኮስ ጥይት ታሪክ በሚፈርደው ሁኔታ ብዙዎች ሕይዎታቸውን አጥተዋል። ይህ እንዳይደገም የፖለቲካ ችግርን በጠብ መንጃ ሳይሆን በሐሳብ የመፍታት ልማዱ አሁኑኑ ገቢራዊ ሊሆን ይገባል።  መወጋገዝ፣ መፈራረጅ፣ በእልህ መራኮት ለሕዝብ አይጠቅምም። የትኛውም ሕዝብ የመልማት፣ ሰላም የመሆን እና ፍትሕ የማግኘት መሰረታዊ ፍላጎት እና መርህ አለው። ለእነዚህ መርሆች በመገዛት የሕዝብ ሰላሙ ይመለስለት።  ግጭቱ ውሎ አይደር፤ የግጭቱ ዕድሜ በንግግር ይጠር! የመሳሪያ ድምፅ የሞት ድሞፅ በመሆኑ በውይይት ይዘጋ!   ለሕዝቡ ተስፋው እንዲነጋ፣ የመሳሪያ ላንቃ ይዘጋ! በመሳሪያ ላንቃ መከፈት የሚጠፋ ሕይዎት እንጅ የሚፋፋ ሀገር ስለማይኖር ለንግግር ጊዜ ይሰጥ!

 

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here